የCDU ጉባዔ
ዓርብ፣ ኅዳር 12 2012ማስታወቂያ
የጀርመን ገዢ ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ሕብረት (CDU-በጀርመንኛ ምሕፃሩ) መሪ ወይዘሮ አነግሬት ክራምፕ-ካረን ባወር የፓርቲ ጓዶቻቸዉ ድጋፍ ካልሰጧቸዉ ሥልጣን እንደሚለቁ አስጠነቀቁ። የCDUን የረጅም ጊዜ መሪ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን የሚተኩት ክራምፕ ካረን ባወር በሊቀመንበርነት ከተመረጡ ካለፈዉ ዓመት ወዲሕ አንጋፋዎቹ የፓርቲዉ ፖለቲከኞች የአመራር ብቃታቸዉን እየተቹ ነዉ። ክራምፕ ካረንባወር ዛሬ ላይፕዚሽ-ምሥራቅ ጀርመን ዉስጥ ለተሰየመዉ የፓርቲዉ ጉባኤ እንደነገሩት ተቺዎቻቸዉ አደብ ካልገዙ ሥልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ ናቸዉ።«ዛሬዉኑ።» አሉ።«እኔ የምፈልጋት ጀርመን እናንተ እንድትሆን ከምትመኟት የተለየች ናት ብላችሁ ካሰባችሁ። ከናንተ ጋር ልጓዝበት የምፈልገዉ መንገድ እናንተ ትክክል ነዉ ብላችሁ ከምታስቡት የተለየ ነዉ ካላችሁ፤ ዛሬዉኑ እንናገረዉ፣ ዛሬዉኑ እናቁመዉ፣ እዚሁ፣ አሁኑኑ።ይሁንና ዉድ ወዳጆቹ፣ ይችን ጀርመንን ከፈለጋችኋት፣ይሕን መንገድ አብረን እንድንጓዝበት ከመረጣችሁ፣ ጀርመንን ለማነፅና ኃላፊነት ለመቀበል ከፈለጋችሁ እጅጌአችንን እንጠቅልል።እዚሁ፣ አሁኑኑ እና እንጀምር።»የ57 ዓመቷ ፖለቲከኛ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2021 በሚደረገዉ ምርጫ ወይዘሮ አንጌላ ሜርክልን ተክተዉ ለመራሔ መንግስትነት ይወዳደራሉ።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ