1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ6 ክልሎች ውይይት በባሕር ዳር

ዓርብ፣ ጥር 21 2013

ክልሎች ራሳቸውን እንደ ሉዓላዊ አገር በመቁጠር የህዝቦችን ትስስርና አብሮነት እየናዱ እንደሆነ ተገለፀ፣ በብሔርና በጎሳ ታጥረን ታላቁን አገራዊ ራዕይ ማደብዘዝ እንደማይገባም ትናንት በባሕር ዳር ተካሄደው የምዕራብና የሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ተመልክቷል

https://p.dw.com/p/3oaED
Äthiopien Regionalstaaten-Gespräche zur Verbesserung  der sozialen und wirtschaftlichen Beziehungen
ምስል Alemenew Mekonne BaharDar/DW

የ6 ክልሎች ውይይት በባሕር ዳር

የፌደሬሽን ምክር ቤት ባዘጋጀውና 6 ክልሎችን ያካተተው የምዕራብና የሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ትናንት በባህር ዳር ተካሂዷል፡፡ 
በእለቱ የተገኙት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት ቀደም ሲል በክልል መንግስታት መካከል ሲካሄዱ የነበሩ ውይይቶች መልካም እንደነበሩ አስታውሰዋል፣ ግን ደግሞ ያልተፈቱ ችግሮች እንደነበሩም በዝርዝር እቀምተዋል፡፡ 
የክልል መንግስታት በክልሎቻቸው የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ደህንነት መጠበቅ፣ ችግር ሲደርስባቸውም አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ አደም ፋራህ 
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የአማራ ክልል ተወላጆች በየትኛውም ክልል የሚኖሩ መሆኑን ጠቁመው በየጊዜው የሚደርስባቸውን ጥቃት የክልል መንግስታት እንዲታደጉት ጠይቀዋል፡፡ 
ኢትዮጰያን ታላቅ አገር ለማድረግ ተባብሮ መስራት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ አገኘሁ፣ አመራሩ ጠንክሮ በመስራት ውጤት ማስመዘገብ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ 
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ “በየክልሎቹ የሚደረጉ ቅስቀሳዎች ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ ሉዓላዊ አገር አስመስሏቸዋል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው በብሔር “መሸበብና የራሴ ክልል” ማለት ታላቋን ኢትዮጵያ እንዳናይ የሚያደርግ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም በትግራይ ሲደረግ የነበረው ህግ የማስከበር ዋናው ዘመቻ የተጠናቀቀ ቢሆንም ሌሎች በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ አመልክተው ለዚህም ሁሉም ክልሎች ሊያግዙ ይገባል ብለዋል፡፡ 
ትናንት በተዘጋጀው የ6 ምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያ ክልሎች የጋራ መድረክ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የጋምቤላ ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የቤኒሸንጉልና የአፋር ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ 
 ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ማምሻውን የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ አፈ ጉባኤዎችና ሌሎች የክልልና የፌደራል ባለስልጣናት በተገኙበት የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የአሁኑ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የሽኝት ስነስርዓት ተዘጋጅቶላቸዋል፣ በትግራይ ህግ ለማስከበር ለአደረጉት አስተዋፅኦም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 
 

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ