1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2021 የጀርመን ምርጫ ከቀደሙት በምን ይለያል?

እሑድ፣ መስከረም 16 2014

የዛሬው ምርጫ የጀርመናውያንን ትኩረት ብቻ አይደለም የሳበው።የተቀረው ዓለምም የጀርመንን ምርጫ በንቃት እየተከታተለ ነው።ጀርመን ከፍተኛ ተሰሚነት ባላት በአውሮጳ ኅብረትና በሌላውም የዓለም ክፍል ምርጫው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።ማን ሜርክልን ይተካል የሚለው ጥያቄ የጀርመናውያን ብቻ አይደለም።

https://p.dw.com/p/40sx0
Bundestagswahl 2021 | Briefwahl Auszählung in München
ምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance/dpa

የ2021 የጀርመን ምርጫ ከቀደሙት በምን ይለያል?

ጀርመውያን ዛሬ የምክር ቤት እንደራሴዎቻቸውን መርጠዋል ፣ይወክሉናል ለሚሏቸው ፓርቲዎችም ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ጀርመንን ለ16 ዓመታት በመራሄ መንግሥትነት የመሩት አንጌላ ሜርክል ያልተወዳደሩበት ይህ ምርጫ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ከከዚህ ቀደሞቹም የተለየም ተብሏል። 
በጀርመን ድኅረ ጦርነት ታሪክ አንድ ሥልጣን ላይ ያለ መሪ ዳግም በምርጫ አልወዳደርም ሲል ሜርክል የመጀመሪያዋ ናቸው። በብዙዎች አስተያየት መራኂተ መንግሥት ሜርክል የማይሳተፉበት 20ኛው የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ምርጫ ከከዚህ ቀደሞቹ ይለያል። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የአፍሪቃ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ሃላፊ ዶክተር ኦሉሚዴ ፣የሜርክል በምርጫው አለመሳተፍ በራሱ አንዱ ምርጫውን ልዩ የሚያደርገው ምክንያት ነው ይላሉ ።አቢምቦላ ሌሎች ምክንያቶችንም ጠቅሰዋል። 
«እንደሚመስለኝ በግልጽ የሚታየው ልዩነት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አለመወዳደራቸው ነው ።ስለዚህ ይህ ዋናው ልዩነት ነው።ከዚያም በላይ ግን ምርጫው በወረርሽኝ ወቅት የሚካሄድ ምርጫ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።በዚህም ምክንያት ብዙዎች አስቀድመው በደብዳቤ መርጠዋል።ስለዚህ መጨረሻው ምን እንደሚሆን እናያለን።በአጠቃላይ ግን ከቀደሙት ምርጫዎች መለየቱ አይቀርም።»
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ጋዜጠኛ አቶ ክፍለ ማርያም ገብረ ወልድ የዘንድሮው  የጀርመን ምርጫ ከሌሎቹ የሚለየው ህዝቡ ለማን ድምጹን እንደሚሰጥ አስቀድሞ ማወቅ አለመቻሉ ነው ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ በተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሰረት ከመራጩ አብዛኛው ማንን እንደሚመርጥ ይወስናል የተባለው ድምጽ በተሰጠበት በዛሬው እለት ነው።የዚህ ምክንያቱ አቶ ክፍለማርያም እንዳሉት ለመራሄ መንግሥትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ቁጥር ዘንድሮ መጨመሩ አንዱ ነው። ለውጥ የሚፈልገው ህዝብ ፣ከሜርክል በኋላ ሀገሪቱን የሚመራውን በጥንቃቄ ለመምረጥ ማሰብም ሌላው ምክንያት መሆኑን ነው አቶ ክፍለማርያም ያስረዱት።
ከዚህ ሌላ 16 ዓመት ጀርመንን የመሩት ወይዘሮ ሜርክልና ተጣማሪያቸው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በአመራር ዘመናቸው በሀገር ውስጥ መሠረታዊ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ጥያቄ ይቀርብባቸው በነበሩትና ሲንከባለሉ በቆዩት የጀርመን የጡረታ ስርዓትና የቀረጥ አከፋፈል ላይ ምንም ለውጥ አለማድረጋቸው በስፋት ያስተቻቸዋል። ማሻሻያዎቹ መደረግ እንዳለባቸው ህዝቡ ቢያምንም ፣እንዴትና በማን ይካሄዳል  ምን ዓይነት ለውጥስ ይመጣል የሚሉት ጥያቄዎች ከስጋት ጋር እያነጋገሩ ነው።አቶ ክፍለማርያም እንዳሉት እነዚህ ምርጫውን በሀገር ውስጥ እንዲተኮርበት ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ናቸው ። 
የዛሬው ምርጫ የጀርመናውያንን ትኩረት ብቻ አይደለም የሳበው።የተቀረው ዓለምም የጀርመንን ምርጫ በንቃት እየተከታተለ ነው።ጀርመን ከፍተኛ ተሰሚነት ባላት በአውሮጳ ኅብረትና በሌላውም የዓለም ክፍል ምርጫው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።ማን ሜርክልን ይተካል የሚለው ጥያቄ የጀርመናውያን ብቻ አይደለም።
ከአሁኑ የጀርመን ምርጫ በኋላ ሦስት ዓይነት  መንግሥት ሊመሰረት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል ። የመጀመሪያው  ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ፣የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲና፣ ግራዎቹ የሚጣመሩበት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ይህ ሊሆን የሚችለውም የሜርክል ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት የመራሄ መንግሥት ዋናው እጩ ፣ህዝቡንም ሆነ መገናኛ ብዙሀንን እምብዛም ባለመማረካቸው ነው ተብሏል ።ሁለተኛው አማራጭ የሶሻል ዴሞክራቶች የSPDና ፣የነጻ ዴሞክራቶቹ የFDP ፓርቲዎች እና የአረንጓዴው ፓርቲ ጥምረት ነው።ሶስተኛው ደግሞ እስካሁን እንደነበረው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የሶሻል ዴሞክራቶቹና ፓርቲ ተጣምረው መንግሥት ሊመሰርቱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

BTW 2021 Deutschland Wahllokal
ምስል Thomas Kienzle/AFP/Getty Images
DW Quadriga - Kiflemariam Gebrewold
ምስል DW
BTW 2021 Deutschland Wahllokal Berlin Frank-Walter Steinmeier
ምስል Focke Strangmann/Getty Images

ኂሩት መለሰ