1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2021 ዓለምአቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊው ኢትዮጵያዊ

ዓርብ፣ ሰኔ 24 2014

በግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብት እና አፈር ጥበቃ ከ250 በላይ የምርምር ፅሑፎች በዓለምአቀፍ ደረጃ በታወቁ ጆርናሎች አሳትመዋል። የምርምር ውጤቶቻቸው፣ መፅሐፍቶቻቸው እና የትግበራ ሰነዶቻቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ሆነው ለውጥ ፈጣሪ ስራዎች ፈፅመዋል። የ2021 ዓለምአቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊው ፕሮፌሰር ምትኩ ሀይለ።

https://p.dw.com/p/4DWgi
Äthiopischer Professor Mitku Haile
ምስል Million Haileselasse/DW

የ2021 ዓለምአቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊው ኢትዮጵያዊ፥ ፕሮፌሰር ምትኩ ሀይለ

ባለፊት 30 ዓመታት በተለይም በትግራይ በአጠቃለይ ደግሞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በግብርናው መስክ፣ የተፈጥሮ ሀብት ማዳን እና አስተዳደር ተግባራት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የምርምር ተግባራት አከናውነዋል። በግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብት እና አፈር ዙርያ ከ250 በላይ የምርምር ፅሑፎች በዓለምአቀፍ ደረጃ በታወቁ ጆርናሎች አሳትመዋል። የምርምር ውጤቶቻቸው፣ መፅሐፍቶቻቸው እና የትግበራ ሰነዶቻቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ሆነው ለውጥ ፈጣሪ ስራዎች ፈፅመዋል። የ2021 ዓለምአቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊው ፕሮፌሰር ምትኩ ሀይለ። 

መጀመርያ ላይ በሀረማያ ዩኒቨርስቲ በግብርና ዘርፍ በአስተማሪነት እና ተመራማሪነት የሰሩት፣ ቀጥሎም መቐለ ዩኒቨርስቲ በማቋቋምና በመምራት የማይተካ ሚና የተወጡት ፕሮፌሰር ምትኩ ሀይለ፤ ዓለምአቀፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሕብረት ኮንፌደሬሽን ለግብርናና ስነ ሕይወት ወይም በኢንግሊዘኛ ምህፃሩ GCHERA ይህን ዓለምአቀፍ የሎሬትነት መዓርግ ያጎናፀፋቸው ለሶስት አስርት ዓመታት በግብርና ምርምር፣ የግብርና ትምህርት ማስፋፋት፣ አርሶአደሮች መሰረት ያደረገ የምርምር ስራ በመከወን መሆኑ ገልጿል። 
ፕሮፌሰሩ ሽልማቱ "የዓመታት ልፋት፣ የበርካቶች ጥምር ጥረት ውጤት" ብለው ይገልፁታል።

ባለፈው ሳምንት ቻይና በተደረገ ስነ-ስርዓት እውቅናው የተሰጣቸው የግብርና ዘርፉ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ምትኩ፣ አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ የሽልማት ስነ ስርዓቱ መቐለ ሆነው በርቀት ተከታትለዋል። በተለይም በትግራይ በአጠቃላይ ደግሞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሳይንሳዊ ጥናቶች በማድረግ ለረዥም ዓመታት የተሰራው ተፈጥሮ ሀብት የማዳን ስራ፣ በተግባር ከፍተኛ ለውጥ የፈጠረ መሆኑ የሚናገሩት የ2021 ዓለምአቀፍ የግብርና ሎሬት ፕሮፌሰር ምትኩ ሀይለ ይህን ተከትሎ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮች ሕይወት መቀየሩ ያስረዳሉ። ለዓመታት በተደረገ ልፋት፣ በከፍተኛ ሀብትና ጉልበት፣ በአርሶአደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች ጥረት የሚታይ ለውጥ ፈጥሮ የነበረ የአካባቢ ሁኔታ በወቅቱ ጦርነት ምክንያት ዳግም አደጋ ላይ መውደቁ ግን ያሳስባቸዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሕር
አዜብ ታደሰ