1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2021 ትዉስታ-ክፍል II

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2014

2021 ጋዜጠኞች ከ1935 ወዲሕ የሰላም ኖቤል የተሸለሙበት፣ ኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጦር ሜዳ የዘመተበት፣ ምያንማር ዉስጥ ከስልጣን የተወገዱ፣ ወሕኒ የተወረወሩበት፣ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ካንድም ሁለት የሰላም ጀግኖች ያረፉበት ዓመት ነበር።

https://p.dw.com/p/455um
Afghanistan Kabul Flughafen Evakuierungen Chaos
ምስል AP Photo/picture alliance

የ2021 ሁለተኛ መንፈቅ ቅኝት

በግጭት፣ጦርነት ጥፋት ዉድመት፣በተፈናቃይ፣ ተመፅዋች ብዛት ኢትዮጵያና አፍቃኒስታን ሶሪያን፣የመንንና ኮንጎን ቀድመዉ፣ ምያንማርን አስከትለዉ፣ ከዓለም የአንደኝነቱን ስፍራ የተፈራረቁበት የጎሪጎሪያኑ ዓመት ላይ መጣ ሔደ።ኢድሪስ ዴቢ ጦር ሜዳ የወደቁበት፣ ሒስኒ ሒብሬ ወሕኒ ቤት፣ የሞቱበት፣ ዦቪኔል ሞይሴ ቤታቸዉ ዉስጥ የተገደሉበት፣የሰላም ኖቤል ተሸላሚዉ ዓብይ አሕመድ ጦር ሜዳ አዋግተዉ ድል የነሱበት፣ የሰላም ኖቤል ተሸላሚዎቹ ኤፍ ዳብሊዉ ዴክላርክና ዴዝሞንድ ቱቱ ያረፉበትም ዓመት ነበር።2021።ኮቪድ 19 ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መግደሉ የተረጋገጠበት፣ ኮሮና መልክ ባሕሪዉን እየለዋወጠ ዓለምን እንዳራወጠ ዓመቱ ሔዶ፣ ዓመት ተተካ።በ2021 ሁለተኛ መንፈቅ ከአዉሮጳ በመለስ በተቀረዉ  ዓለም የተከናወኑ ዓበይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ባጫጭሩ ቃኝተን እንዘክረዉ።

                                     

የኮሮና በጣሙን ኦሚክሮን የተሰኘዉ ልዉጥ ተሕዋሲ ፈጣን ስርጭት ያሰጋ፣ ግንኙነት እንቅስቃሴዉን የገደበዉ ዓለም አንድም በየቤቱ፣ ሁለትም ፈንጠርጠር፣ በተን፤ ቀዘዝ፣ ፈዘዝ፣ ባለድግስ፣ አዲሱን ዓመት ተቀበለ።2022።በየዓመቱ እንደሚሆነዉ ከትላልቅ ከተሞች ቀዳሚዋ ሲድኒ ናት።

አርብ እኩለ ሌት የተሰናበተዉ 2021 ሁለተኛ መንፈቁን እንደያዘ ኃምሌ፣ ኮቪድ 19 የገደለዉ ሰዉ ከ4 ሚሊዮን በልጦ ነበር።ይሁንና ዓለም በአንድ ደዌ፣በሁለት ዓመት ከመንፈቅ ከ4 ሚሊዮን በላይ ወገኑን በማጣቱ ከመደንገጥ ይልቅ፣በመከላከያ ክትባቱ ተፅናንቶ ኃያሉ ዓለም አፍቃኒስታን ላይ የገጠመዉን ሽንፈት እንዴትነት ሲያስተነትን ሰሜን አሜሪካ በከባድ ሙቀት ነፈረ።

Afghanistan Kabul Flughafen Evakuierungen Chaos
ምስል AP Photo/picture alliance

ለረጅም ዘመናት ታይቶ የማይታወቀዉ ሙቀት፣ወበቅና ቃጠሎ ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ 600 ሰዉ ገደለ።ኃምሌ 3።ካናዳን  የገለበዉ እሳት 130 አካባቢዎችን አነደደ።

                                

«የአየር ንብረት ለዉጥ አብሮን እንዳለ የሚያስታዉስ ስዕላዊ መረጃ ነዉ።»ይላሉ የዓየር ንብረት ባለሙያዉ።ብቻ ኃምሌ 5 አለ።የአፍቃኒስታን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የታሊባንን ጥቃት መቋቋም ያቃታቸዉ ከአንድ ሺ በላይ የመንግሥት ወታደሮች ወደ ታጂክስታን ሸሹ።

የወታደሮቹ ሽሽት በአሜሪካኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ የተመሠረተዉ የአፍቃኒስታን መንግስት ጦር ጨርሶ የመበተኑ ምልክት፣የፕሬዝደንት አሽረፍ ቃኒ መንግሥት የመጨረሻ-መጀመሪያ፣ ከሁሉም በላይ 20 ዓመት አፍቃኒስታንን ያተራመሱት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ የመሸነፋቸዉ ግልፅ ማረጋገጪያ ነበር።

ዓለም የኮቪድ 19ን መቅሰፍት፣የሰሜን አሜሪካን ቃጠሎ፣ የኢትዮጵያን ጦርነት ችላ ብሎ የአፍቃኒስታንን ትርምስ እያነሳ ሲጥል፣ በዓለም ተረስታ ቁል ቁል የምትዳክረዉ የሐይቲ ፕሬዝደንት ዦቬናል ሞይሴ መኖሪያ ቤታቸዉ ዉስጥ በወረቦሎች በጥይት ተደብድበዉ ተገደሉ።ባለቤታቸዉ ቆሰሉ።ኃምሌ 7።

Äthiopien | Binnenvertriebene
ምስል Privat

የደሐይቱ የካረይቢክ ሐገር ጥቁር ሕዝብ ለመሪዉ ሞት የለበሰዉን ከል ሳያወልቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ያርገፈግፈዉ ገባ።2100 ሰዉ ሞተ።ነሐሴ 14።ግሎባል ሜዲክ የተሰኘዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ራሁል ስንጌሕ የተረፉትን እንርዳ ይላሉ።«በሕይወት በተረፉት ላይ ማተኮር አለብን።በዚሕ የመሬት መንቀጥቀጥ 500,000 ሺሕ ሰዎች ተጎድተዋል።በሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት አልቦ ሆነዋል።የሚተኙት በየፍርስራሹ ስር ነዉ።»

 

ተፈጥሮም-ፍጡርም ሁሌም የሚጨክንባት ሐገር መቅሰፍት ለዓለም መገናኛ ዘዴዎች ከዕለታት ዜና በላይ ብዙ ትኩረት የሚስብ አልነበረም።የቱኒዚያዉ ፕሬዝደንት ካይስ ሰዒድ ተቃዋሚዎቻቸዉ የሚበዙበትን ምክር ቤት አግደዉ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን ሽረዉ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።ኃምሌ 25።የአደባባይ ሰልፍ፣ ተቃዉሞ፤ ዉዝግቡ ቀጠለ።

                                           

«ከኃምሌ 25 በፊትም ቢሆን ጀነት አልነበረም።ግን ቢያንስ የሕግ መዋቅር ነበር።አሁን ሕዝባዊ አብዮቱ ሞቷል።ሕግም የለም።»

ሰልፈኛዋ።የአብዛኛዉ ዓለም ትኩረት ግን አንድም ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የታቀፈችዉ ኢትዮጵያን አለያም ኃያል፣ሐብታሙን ዓለም 20 ዓመት ያባከነችዉ አፍቃኒስታንን ከሚንጥ፣ከሚያሻምደዉ ጦርነት  ላይ ነበር።

ሰኔ ማብቂያ፣  መቀሌን ጨምሮ አብዛኛዉን የትግራይ አካባቢዎች ከኤርትራ፣ከኢትዮጵያ መንግሥታት ጦርና ከአማራ ክልል ልዩ ልዩ ኃይሎች እጅ ያስለቀቁት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተዋጊዎች ኃምሌ ላይ ወደ ደቡብ ይንደረደሩ ገቡ።

Sudan Khartum | Demonstration & Protest gegen Militärjunta
ምስል AFP/Getty Images

ኃምሌ 22 ሕወሓት የቆቦ ወልዲያን መስመር ተቆጣጥሮ፤ ጨርጨር-ሚሌ ግንባር አዲስ ጥቃት ከፈተ።ሕወሓት አዲስ አበባን እንደሚይዝ መሪዎቹ ሲፎክሩ፣ ታሊባን ከሰሜን ኩንዱዝ፤ፑሊ ኹማሪ፣ ከመሐል ዳማን  ተቆጣጥሮ  ርዕሰ-ካቡልን ለመያዝ ወደ ምስራቅ ይገሰግስ ገባ።ኃምሌ ግን አበቃ።

ነሐሴ 5 ሕወሓት ታሪካዊቱን የላሊበላ ከተማን ያዘ።ነሐሴ 6 ታሊባን ሸበርጋንና ሌሎች አካባቢዎችን ተቆጣጠረ።ነሐሴ 13።ታሊባን የአፍቃኒስታንን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ካንዳሓርንና ስልታዊቱን ከተማ ሔራትን ተቆጣጠረ።ነሐሴ ሲጋመስ የታሊባን ተዋጊዎች ካቡል ደጃፍ ላይ ደረሱ።

                                      

ዩናይትድ ስቴትስ መስከረም 2001 ኒዮርክና ዋሽግተንን ያሸበረዉን አልቃኢዳንና የታሊባን ተባባሪዎቹን ለማጥፋት አፍቃኒስታንን ስትወር 29ኙን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ተሻራኪዎችዋን አስከትላ ነዉ።

20 ዓመት ግድም በፈጀዉ ጦርነት ከ64 ሺሕ በላይ የአፍቃኒስታን መንግሥት ጦር ባልደረቦች፣3449 የተባባሪዎቹ ሐገራት ወታደሮች፣ከ3800 በላይ የወታደራዊ ኮንትራት ሰራተኞች፣72 ሺሕ የታሊባን፣ ከ2400 በላይ የአልቃኢዳ ተዋጊዎች፤45 ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ከ10 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል።ከ2.3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈስሷል።ዉጤት?

Äthiopien Tigray-Konflikt | Armee übernimmt wieder Kontrolle
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የአፍቃኒስታን መንግስት ጦር ተበተነ።ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ ሸሹ።ታሊባን ካቡልን  ተቆጣጠረ።ነሐሴ 15።

ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ዜጎቻቸዉን ከአፍቃኒስታን ለማስወጣት ሲራኮቱ፣ አፍቃናዉያን አስተርጓሚ፣ ሰላይ፣ የፕሮፓጋንዳ ሰራተኞቻቸዉና ሌሎች ተቀጣሪዎቻቸዉ በሚበርር አዉሮፕላን ሲጠለጠሉ እየተፈጠፈጡ ሞቱ።

                                   

«እዚሕ እንኳን አፍቃናዉያን እገዳዉን እየጣሱ አዉሮፕላን ማረፊያዉ እየደረሱ ነዉ።እዚሕ ከመቆየት በሚያኮበኩብ አዉሮፕላን ላይ ይንጠላጠላሉ።አሜሪካኖች ከአፍቃኒስታን ማዉጣት የሚፈልጉት ዜጎቻቸዉን ብቻ ነዉ ይላሉ።»አለ ጋዜጣኛዉ።ነሐሴ 16 ነበር።

ዓለም ሐሚድ ካርዛይ አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚከወነዉን ዘግናኝ ትርዒት ለመመልከት በየቴሌቪዥን መስኮቱ ላይ ዓይኑን እንደተከለ የአዉሮፕላን ማረፊያዉ መዳረሻ በቦምብ ጋየ።ሌላ ሽብር፣ሌላ ጥፋት፣ ሌላ ዋይታ።ነሐሴ።26።ከታሊባን አገዛዝ  ለማምለጥ ከሚተራመሰዉ ሕዝብ 182ቱ ሞተ።13ቱ የአሜሪካ ወታደሮች ነበሩ።ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለብቀላ ዛቱ።«ምሕረት የለንም።አንረሳዉም።እናድናችኋለን።እንበቀላችኋለን።»

አሜሪካ ጥቃቱን ያቀናበረ የእስላማዊ መንግሥት አባል ያለችዉን ሰዉዬ ከነቤተሰቦቹ በሰዉ አልባ በራሪ ገደለች።ነሐሴ 27።ኋላ ሲጣራ ግን ሟቹ አሜሪካኖች ያሉት አልነበረም።ነሐሴ 30 የመጨረሻዎቹ የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍቃኒስታን ወጡ።

የታሊባኖች ጥብቅ አገዛዝ፣ እገዳ፣ የምዕራቦች ማዕቀብ የዋሁን አፍቃናዊ እንዳስራበ፣በመድሐኒት እጦት እንዳሰቃየ፤ እንዳሰደደ ዓመቱ አስረኛ ወሩን ሲያጠናቅቅ ሕወሓት ሥልታዊቱን፣ ጥንታዊቱን ሰፊይቱን ደሴን፣ የኢንዱስትሪና የንግድ ከተማይቱን ኮምቦልቻን ተቆጣጠረ።የሕወሓት ተዋጊዎች አዛዥ የጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ ዛቻ አስፈሪ ነበር።ጥቅምት አበቃ።

Südafrika Kapstadt Trauer um Desmond Tutu
ምስል AP/picture alliance

የሕወሓት ጦር ባቲ፣ከሚሴ፣ ሸዋ ሮቢትን እየተቆጣጠረ አንድም የአዲስ አበባ-ጅቡቲን መስመር ለመቁረጥ ሁለትም በቀጥታ አዲስ አበባ ለመግባት መቃራቡ ያሰጋዉ ዓለም ዜጎቹን እያፈሰ ከኢትዮጵያ ያስወጣ፣አልወጣ ያሉትን ያስጠነቅቅ ገባ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ግን ጦራቸዉን በገፅ ለማዋጋት ጦር ግንባር ዘመቱ።ሕዳር 22።የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ጦር ሜዳ ሲዘምት ምናልባት ዐብይ የመጀመሪያዉ ሳይሆኑ አይቀሩም።የጠቅላይ ሚንስትሩ ዘመቻን፣ ግንቦት 1991 ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ሐራሬ የገቡበትን ሰበብ ባልዘነጉት ዘንድ ጥርጣሬን፣ ሚዚያ ላይ የኢድሪስ ዴቢን አወዳደቅ ለሚያዉቁት ደግሞ ሐዘንን ፈጥሮ ነበር።ሰዉዬዉ ግን ሁለቱንም እንዳልሆኑ አረጋገጡ።

                                         

ባጭር ጊዜ ዉስጥም የኢትዮጵያ መንግስት ጦር፣የአፋርና የአማራ ልዩ ልዩ ኃይላት የአፋርና የአማራ ክልሎችን ከሕወሓት ቁጥጥር አስለቀቁ።ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ መንግስት ታላቅ ድል።ጦርነቱ ግን አላበቃም።

መስከረም 5፣ የጊኒ የክብር ዘበኛ ጦር አዛዥ ሌትናንት ኮሎኔል ማማዴይ ዶዉምቡያ የሐገሪቱን ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴን አስረዉ የመሪቱን ስልጣን ያዙ።መፈንቅለ መንግስት።

መስከረም 14፣ ሰሜን ኮሪያ ያወነጨፈችዉ የአጭር ርቀት ተምዛግዛጊ ሚሳዬል ጃፓን የዉኃ ግዛት አጠገብ የሚገኘዉን ባሕር አምቦጫረቀዉ።ደቡብ ኮሪያ ባፀፋዉ ከባሕር ሰርጓጅ መርከቧ ላይ የመጀመሪያዉን ሚሳዬል ተኮሰች።

ሁለቱ ኮሪያዎች የሚሳዬል ጉልበታቸዉን ሲፈታተሹ ዩናይትድ ስቴትስ፣ብሪታንያና አዉስትሬሊያ «የሶስትዮሽ» እና «የፀጥታ» ያሉትን ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረሙ።መስከረም 15።ዉሉ ለሰሜን ኮሪያ የምታዳላዉን ቻይናን ለማዳከም ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተንታኝ አላስፈለገም።

Sudan Khartoum | Premierminister zurückgetreten | Abdalla Hamdok
ምስል Mahmoud Hjaj/Anadolu Agency/picture alliance

መስከረም የምርጫ ወር ነበር።የሩሲያ፣የካናዳ፣የአይስላንድና የጀርመን ሕዝብ የየምክር ቤት እንደራሴዎቹንና መሪዎቹን መርጧል።

ጥቅምት6፣ በኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ግራ-የተጋባዉ ዓለም የመጀመሪያዉን የወባ መከላከያ ክትባት አፀደቀ።ክትባቱ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለዉ በሚሊዮን ለሚቀጠር አፍሪቃዊ ጤና ሲበዛ ጠቃሚ ነዉ።

ጥቅምት 23፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚታገዘዉ የኮሎምቢያ ጦር አደገኛዉን የአደንዛዥ ዕፅ ቱጃር ዳሪዮ አንቶኒዮ ዑስጋን ያዘ።ጥቅምት 25 ሱዳን እንደገና መፈንቅለ መንግስት።ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ።

ከስልጣን የተወገዱት የሲቢሉ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክና የካቢኔ አባሎቻቸዉ በቁም ታሰሩ።ሕዝባዊዉ አመፅ፣የአደባባይ ተቃዉሞዉ ቀጠለ።

የሱዳን ሕዝብ ጮኾም፣ ተሰልፎም፣ ወገኖቹ ተገድለዉ፣ ተደብድበዉበትም ጄኔራሎቹን አንበረከከ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ስልጣናቸዉ ተመለሱ።ሕዳር 22።ይሁንና ስትበጠስ-ስትቀጠል የሳሳችዉ የአብደላ ሐምዶክ የሥልጣን ገመድ ትናንት ጨርሶ ተጎመደች።ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን በቃኝ አሉ።

ሕዳር ኮቪድ 19 የገደለዉ ሰዉ ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን በለጠ።

ታሕሳስ 9ና 10፣ ዩናይትድ ስቴትስ «የዴሞክራሲ ጉባኤ» ያለችዉን የመሪዎች ስብሰባ ጠራች።በርቀት (ኢንተርኔት) በተደረገዉ ጉባኤ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሐገራት መሪዎች ተካፍለዋል።ሐቻምና ትግራይ ላይ በተጀመረዉ ጦርነት ሰበብ ከዋሽግተን ጋር አይና ናጫ የሆነችዉ አዲስ አበባ ግን አልተጋበዘችም።

ታሕሳስ አጋማሽ፣ 3ኛዉ የቱርክና የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ  ኢስታንቡል- ቱርክ ዉስጥ ተደረገ።በጉባኤዉ ላይ የኢትዮጵያን ጨምሮ 16 ሐገራት መራሕያነ መንግስታትና ርዕሰነ-ብሔራት፣ ከ100 በላይ ሚንስትሮች ተካፍለዋል።

ዓመቱ ለፍፃሜዉ ሲያዘግም ታሕሳስ ኦሚክሮን የተባለዉ ልዉጥ የኮሮና ተሕዋሲ ዓለምን ማዳራሱ ተዘገበ።

ዓመቱ ቻድን ከ1990 ጀምሮ የገዙት ኢድሪስ ዴቢ በምርጫ ባሸነፉ ማግስት ጦር ሜዳ የወደቁበት፣ ዴቢ ከስልጣን ያስወገዷቸዉ ሂስኔ ሒብሬ ሴኔጋል ወሕኒ ቤት ዉስጥ የሞቱበት ነበር።አፍሪቃ ሌላ አንጋፋ መሪም አሰንብታለች የዛምቢያዉ የነፃነት አባት ኬኔት ዴቪድ ካዉንዳ።ዕድሜ ግን ጠግበዋል።97 ዓመታቸዉ ነበር።መስከረም 17፣ የቀድሞዉ የአልጄሪያ ፕሬዝደንት አብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃ አረፉ።84 አመታቸዉ ነበር።

2021 ጋዜጠኞች ከ1935 ወዲሕ የሰላም ኖቤል የተሸለሙበት፣ ኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጦር ሜዳ የዘመተበት፣ ምያንማር ዉስጥ ከስልጣን የተወገዱ፣ ወሕኒ የተወረወሩበት፣ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ካንድም ሁለት የሰላም ጀግኖች ያረፉበት ዓመት ነበር።

Äthiopien | Premierminister nimmt an Offensive gegen Rebellentruppen Teil
ምስል Ethiopian Prime Minister's Office//AA/picture alliance

የመጨረሻዉ የደቡብ አፍሪቃ ነጭ መሪ ፍሬድሪክ ዊሊያም ደ ክላርክ ሕዳር 11 ሞቱ።85 ዓመታቸዉ ነበር።ታሕሳስ 26፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዴዝሞንዱ ቱቱ  ሞቱ።90 ዓመታቸዉ ነበር።ፕሬዝደንት ሲርያል ራማፎዛ እንዳሉት ቱቱ ፅዕኑ የመብት ተሟጋች ነበሩ።

«በደብራቸዉ፣የዘር መድሎ ስርዓትን በሚታገሉበት ወቅት፣የዕዉነትና የዕርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነዉም፣ ሰዉ ሌሎችን ለመጨቆን ምን ያሕል ጥልቀት እንደሚወርድ አይተዋል።ይሁንና በፈጣሪያቸዉ ላይ እንዳላቸዉ ፅኑ ዕምነት ሁሉ በሰብአዊነትና በሰዎች ላይም የማይናወጥ ዕምነት ነበራቸዉ።»

እና አዲስ ዓመት።2022።በዘመኑ ለምታሰሉ መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ