1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ1ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ መቶኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2011

በዚህ ጦርነት ያለቁት አፍሪቃውያን ሲብሎች እና ወታደሮች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ነው የሚገመተው። የተዋጉትም ባለቡት በአፍሪቃ እንዲሁም በአውሮጳ ጭምር ነበር። ፈረንሳይ ከምዕራብ እና ሰሜን አፍሪቃ ቅኝ ግዛቶቿ  450 ሺህ ወታደሮች መልምላ በውጊያው አስልፋለች። ብሪታንያም አፍሪቃውያን ወታደሮችን ከጎኗ አሰልፋ ነበር።

https://p.dw.com/p/38AYu
Paris feiert 100-jähriges Ende des Ersten Weltkriegs
ምስል picture-alliance/TASS/M. Metzel

የ1ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ መቶኛ ዓመት እና አፍሪቃ

በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ ያለቀበት አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ባለፈው እሁድ 100 ዓመት አስቆጠረ። እለቱ ከትናንት በስተያ ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ የዓለም መሪዎች በተገኙበት ታስቧል። በዚህ ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ህይወታቸውን አጥተዋል። 
«ሠራተኞች እና ወታደሮች! ጦርነት የተካሄደባቸው አራቱ ዓመታት እጅግ አስከፊ ነበሩ። ህዝቡ ከባድ መስዋዕትነት ነው የከፈለው። እድለ ቢሱ ጦርነት ቆሟል። ግድያው አብቅቷል። የጦርነቱ መዘዞች መከራ እና ስቃዩ ግን ለሚመጡት ብዙ ዓመታት ከኛ ጋር ይዘልቃሉ። በተቻለን አቅም ሁሉ ልንከላከለው የፈለግነውን ሽንፈት ልናስቀረው አልቻልንም።»
ጀርመን በጎርጎሮሳዊው 2014 የለኮሰችው አንደኛው የዓለም ጦርነት በራስዋ ሽንፈት ሲያበቃ በያኔው የጀርመኑ የቫይማር ሪፐብሊክ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ፖለቲከኛ ፊሊፕ ሽናይደርማን የተናገሩት ነበር። ከትናንት በስተያ እሁድ ከ70 በላይ የሀገራት መሪዎች የአንደኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜን ያበሰረው የተኩስ አቁም የተደረገበትን መቶኛ ዓመት ፓሪስ ውስጥ በተካሄደ ስነ ስርዓት አስበዋል። በስነ ስርዓቱ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ባሰሙት ንግግር ጦርነቱ ሲያበቃ የነበረውን ደስታ እና ትቶት ያለፈውን ጠባሳ አስታውሰዋል። ብሔረተኝነት ባቆጠቆጠበት በዚህ ወቅት ላይ «አሮጌዎቹ እኩዮች እያንሰራሩ ነው ያሉት ማክሮ መጪው ጊዜ ሰላማዊ እንዲሆን ወዳጅነት እና ውይይት እንዲተኮርበት ጥሪ አስተላልፈዋል። ያኔ ለ4 ዓመታት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ ለ6 ዓመታት የተዋጉት ፈረንሳይ እና ጀርመን ዛሬ የቅርብ ወዳጆች ናቸው። የፓሪስዋ ወኪላችን  ሃይማኖት ጥሩነህ  ያነጋገረቻቸው ታዳሚዎች እየጠበቀ የሄደው የሁለቱ ሀገራት የቅርብ ግንኙነት ከምንም በላይ የሚያስደስታቸው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። 
በወታደራዊ ታሪክ አጠናቃሪዎች ግምት፣ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ጠፍቶበታል። አስከፊ የሚባለው ይህ ጦርነት የበላው ህዝብ ቁጥር 17 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። በጦርነቱ የተገደሉት ወታደሮች ቁጥር ብቻ 10 ሚሊዮን ይሆናል ። በአውሮጳ ምድር በተካሄደው በዚህ ጦርነት ከተሰለፈው 56 ሚሊዮን ወታደር በየቀኑ 6ሺህ የሚሆነው ያልቅ እንደነበር ነው ታሪክ የሚያስረዳው ። 21 ሚሊዮኑ ደግሞ ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከመካከላቸው ሰውነታቸው በድን የሆነ፣ መስማት የተሳናቸው እና ዓይነ ስውር የሆኑ በርካቶች ነበሩ። ከተሰዉት እና ከቆሰሉት መካከል ደግሞ ብዙም የማይወራላቸው አፍሪቃውያን ወታደሮች ይገኙበታል። በዚህ ጦርነት ያለቁት አፍሪቃውያን ሲብሎች እና ወታደሮች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ነው የሚገመተው። አብዛኛዎቹ በቅኝ ገዥዎቻቸው አስገዳጅነት ነው ወደ ጦርነቱ የተመሰጉት። የተዋጉትም ባለቡት በአፍሪቃ እንዲሁም በአውሮጳ ጭምር ነበር ፈረንሳይ ከምዕራብ እና ሰሜን አፍሪቃ ቅኝ ግዛቶቿ  450 ሺህ ወታደሮች መልምላ ከጀርመን ጋር በተካሄደው ውጊያ አስልፋለች።ብሪታንያም ከጀርመን ጋር የተዋጋችው አፍሪቃውያን ወታደሮችን ከጎኗ አሰልፋ ነበር። አፍሪቃውያን እቃ በማጓጓዝ እና ምግብ በማብሰልም አገልግለዋል። የደቡብ አፍሪቃ የአርበኞች ማህበር አባል ጆን ዴል ሞንድ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ከ10 ሺህ በላይ ደቡብ አፍሪቃውያን በቤልጂግ በፈረንሳይ በፓኪስታን በሰሜን አፍሪቃ እና አፍሪቃ በሚገኙ የቀድሞዎቹ የጀርመን ቅኝ ግዛቶች ሞተዋል። ጦርነቱ ሲጀመር ይሰጣችኋል የተባለው ደሞዝ ያማለላቸው አንዳንድ አፍሪቃውያን በፈቃደኝነት ተሰልፈው ነበር። ጦርነቱ በጎርጎሮሳዊው 1914 አውሮጳ ውስጥ ሲፈነዳ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ወታደሮች አፍሪቃ የሚገኙትን አራት የጀርመን ቅኝ ግዛቶች ማለትም ፣ ምሥራቅ አፍሪቃን ፣ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃን ቶጎላንድን እና ካሜሩንን ለመያዝ ተዘጋጁ። ያኔ ጀርመን ቅኝ ግዛቶችዋን ላለማጣት አልተሳካላትም እንጂ ኢትዮጵያን ከጎኗ ለማሰለፍ ሞክራ ነበር።  በወቅቱ በተለይ በምሥራቅ አፍሪቃ በደፈጣ ውጊያ ስልት የተካሄደው ውጊያ ጭካኔ የተሞላበት እንደነበር ይነገራል። በወቅቱ ከ200 ሺህ በላይ አፍሪቃውያን ለወታደሮቹ መሣሪያ ጥይት እና ምግብ በማመላለስ ያገለግሉ ነበር። በጦርነቱ አሁን ታንዛንያ ከሚባለው አካባቢ ህዝብ ሀያ በመቶው ህይወቱን አጥቷል ይባላል።ከጦርነቱ በኋላ የገባው የስፓኝ ጉንፋን የተባለው በሽታ ደግሞ ከ50 እስከ 80 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ገድሏል። ይሁን እና ጦርነቱ ከሰለባዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት ታሪክ ውስጥ እየጠፋ ነው። ይህ ብቻ አይደለም የታሪክ ምሁሩ ዮርን ሊዮናርድ እንደሚያስረዱት  በጦርነቱ ለተካፈሉ በርካታ አፍሪቃውያን ባለውለታዎች በአውሮጳ የተሰጠው ትኩረትም አናሳ ነው። በርሳቸው አስተያየት ህይወታቸው ያለፈው ወታደሮች የሚገባቸው ክብር አልተሰጣቸውም። መቃብራቸው እንኳን አልታሰበበትም።
«በብሔራዊ ደረጃ የሚካሄዱ ጦርነቱ የሚታሰብባቸው ስነ ስርዓቶች እና የጦርነቱ መታወሻዎች መለያየታቸውን በግልጽ ታዝቤያለሁ። ለምሳሌ ፈረንሳይ ውስጥ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች የመጡት  የሴኔጋል የቬይትናም እና የኢንዶኔዥያ ወታደሮች የሚገባቸውን ያህል ክብር አግኝተዋል አላገኙም የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው።በምዕራብ አውሮጳ በርካታ ነጭ መስቀሎች የሚታዩባቸው ስፍራዎች አሉ። ይሁን እና በምዕራብ ግንባር ለሞቱት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ከሴኔጋል ለመጡ ወታደሮች የታለ የሙስሊሞች የመቃብር ስፍራ።»
በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 11 1918 አንደኛው የዓለም ጦርነት ቢቆምም ጀርመን ውስጥ ግን መከራው  አላበቃም። የከፋው ድህንነት እና የማይገፋው ችግር ህዝቡን እግር ከወረች አሰረው። የተዋጋነው የተሰቃየነው በከንቱ ነበር የሚለው ቁጭት ነገሰ ፤ንዴት ተንሰራፋ።ይህ መርዘኛ አስተሳሰብ ጀርመናውያንን ተቆጣጠረ። ይህም ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ለቀሰቀሰው ለአዶልፍ ሂተለር ምቹ መደላድል ሆኖ አገልግሏል ።

Deutschland Novemberrevolution 1918 Soldaten mit Roter Fahne
ምስል picture-alliance/akg-images
Die "Schwarze Armee" - Afrikaner im 1. Weltkrieg
ምስል picture -alliance/Everett Collection
Deutschland Novemberrevolution 1918
ምስል picture-alliance/akg-images

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ