1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ12ኛ ክፍል ውጤት እና የኦጋዴን እስር ቤት

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2011

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዕለቱ የሚያነሷቸው እና በርካቶችም አስተያየት የሚሰጡባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ጥቂት አይደሉም። በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ የሆነው የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በተፈታኞች እና ቤተሰቦቻቸው ዘንድ በጉጉት የተጠበቀውን ያህል መነጋገሪያ ለመሆን ብዙም አልቆየም።

https://p.dw.com/p/3NydR
Äthiopien Schüler mit Behinderungen besuchen den Unterricht an einer inklusive Schule in Addis Abeba
ምስል Elena del Estal

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በፈተናው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት አካባቢ አንዱ ትኩረት ሲሆን፣ ዋናው እና ብዙዎችን ግራ ያጋባ የመሰለው በተወሰኑ ትምህርቶች ውጤት ላይ ተፅዕኖ አሳደረ የተባለው የመልስ ቁልፍ ስህተት በሚል በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች የተነገረው ይመስላል። በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ የሰጡት የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረ እግዚአብሔር «ሁለት ኮዶች ላይ የመልስ ቁልፎች የምንለው ተዛብቶ ነው የገባው፤» ካሉ በኋላ «ይኽ  ትክክል አይደለም» ብለው በተጓዳኝ አብሮ ለሚሠራው አካል በማቅረብ የማስተካከያ ርምጃ ተወስዶ በእነዚህ ተሳሳቱ ባሏቸው የትምህርት አዕነቶች ላይ ብቻ የሚገኘውን ውጤት በቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የፈተናው የአንድ አካባቢ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ጥያቄ እንደሚያስነሳ አስተያየት ሲለዋወጥ የነበረው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ የባለሥልጣኑን ማብራሪያ ተከትሎ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ቢኒ ኑሩ አንዱ ነዉ።ቢኒ በፌስቡክ ፣ «የእያንዳንዱ /subject /ትምህርት/  መልስ ይፋ ይሁን ። ይህ ነው የአብዛኛው ተማሪ ጥያቄ። አሁን ለምሳሌ እኔ በውጤቴ አላመንኩበትም። ማረጋገጥ ግን እንዴት ልቻል?» በማለት አስተያየቱን በጥያቄ ሲደመድም፤ ኢብሮ ሀስ ሮብ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «በጣም አሳፋሪ ነው! መንግሥት በዚህ አሳፋሪ ተቋም ላይ በአስቸኳይ ርምጃ መውሰድ አለበት።» ብለዋል።  አያናስ ቱሩራ በዚሁ በፌስ ቡክ፤ «በታዳጊ ትውልድ ከባድ ጠባሳ ጥሎ ማለፍ ዛሬ ሳይሆን ነገ አገርን ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ ጥልቅ ማብራርያ እና ማስተካከያ እንጠብቃለን። » ነው ያሉት።  ታደለ ታዱ ፤ «መፈንቅለ ፈተናም ተጀምሮ ነበር እንዴ?»  ብለው ሲሳለቁ፤ ጀግና እንደ አባቴ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ «አይ አንቺ  አገር !! የፈተና ጥያቄ ተሰረቀብሽ  አሁን  ደግሞ  የፈተና  ውጤት?» ብለዋል።

kleine Mädchen in einer Schule in Tigray
ምስል DW

ዶክተር ጥላዬ ጌጤ አምባዬ የትምህርት ሚኒስትር በትዊተር በፈተና ውጤት ከፍተኛ ስኬት ላገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ፤ «በስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና ውጤት ላይ ቅሬታ እየቀረበ በመሆኑ ብሔራዊ የፈተና እና ምዘና ተቋም ጉዳዩን ዳግም ይመለከተዋል» ካሉ በኋላ  ለሚያሳዩት ትዕግሥት አመስግነው መልካም ዕድል ተመኙ።

ቶለማርያም ፉፋ በትዊተር «ከዚህ የከፋ የትምህርት ውድቀትም የአመራር ውርደትም የለም።» ሲሉ፤ ዮናስ መኮንን እና አርሰናል ፎርኤቨር ደግሞ «አፕቲቲዩድ ብቻ አይደለም ሁሉ የትምህርት አይነት ሊታይ ይገባል።» በማለት ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል። በዚሁ በሚኒስትሩ መልእክት ስር የማጣራቱ ሥራ በሌሎች ትምህርቶች ላይም መደረግ እንዳለበት የሚያሳስቡ በርካታ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል። ድሪባ መገርሳ፤ «የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ለትምህርት ሥርዓታችን ሥርነቀል ለውጥ ማድረግ ምን ያክል አጣዳፊ የቤት ሥራችን እንደሆነ ማሳያ ነው። እየተባለ ያለው ፍኖተ ካርታውም ቢሆን በጣም ጥንቃቄ እና ጥልቅ ውይይት የሚፈልግ መሆኑም ጭምር ነው። » የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰፋ ምስጉን ሀጎስ ደግሞ፣ «በሁሉም ትምህርቶች ላይ ነው ቅሬታው ያለው፤ አጠቃይ ስርዓቱ ቢፈተሽ የሚሻል ይመስለኛል።» የሚል ምክራቸውን አቅርበዋል።

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ውጤት በመልስ ኮድ ምክንያት ተሳሳተ ከሚለው ውጤት ባሻገር የየትኛው ክልል ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ የሚለውም የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።በክልል ደረጃም ጭምር የውጤቱ ተቀባይነት ጥያቄ ላይ መውደቁ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ መስሏል።

Instagram-Icon
ምስል picture-alliance/xim

ይህን የታዘቡ የሚመስሉት አቤል አስራት በትዊተር፤ «በ12ኛ ክፍል ውጤት ቅሬታ ያላቀረበ ክልል ካለ ሲዳማ ብቻ ነው። እነሱም ቢሆን የክልልነት ደረጃቸውን እየተጠባበቁ ነው።» ሲሉ፤ ጌታቸው ግርማ  ደግሞ በፌስቡክ፤ «ብሔራዊ ፈተናም ተማሪዎች ለየደረጃቸው የሚመጥን እውቀት የማግኘታቸው መመዘኛ መሆኑ ቀርቶ ክልሎች ፍትሀዊ የውጤት ክፍፍል የሚጠይቁበት አጀንዳ ለመሆን በቃ ??? ዝቅጠታችን ወደር አልባ እየሆነ ነው?» ብለዋል። እውዱ አምበሉ ደግሞ፤ «የትምህርት ውጤት በፌድሬሽን ምክር ቤት ቀመር አይከፋፈልም። በትምህርት የተሻለ ውጤት የሚመዘገበው በግል ትጋት፣ በቤተሰብ እገዛ፣ በመምህራን ሙያዊ ድጋፍ ነው። በጥረታችሁ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገባችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ! ኮርተንባችኋል!» የሚል ሃሳባቸውን በፌስቡክ አካፍለዋል።

ጃዋር መሐመድ በትዊተር፤ «የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተመለከተ የሆነ ነገር በከፍተኛ ሁኔታ ሳይዛባ አይቀርም። የፈተናው ኤጀንሲ ግልፅነት እና ኃላፊነት የተሞላበት የእርምት ርምጃ እንዲወስድ ይጠበቃል። » ማለቱን ተከትሎ፤ ሲቲና ኑሪ፣ «ተመስገን አንቺ ማርያም! ሁሉ ተረስቶ ኃላፊነት እና ግልጥነት የሚጠየቅበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ግን እኛስ እንርሳ ግድየለም ኤጀንሲው ያንተን እና የተባባሪዎችህን ሥራ ይረሳዋል?» ሲሉ ጠይቀዋል። ኪዳኔ ደግሞ በዚሁ በትዊተር፤ «ኢትዮጽያ ውስጥ በሚሠራው ነገር ሁሉ ኅብረተሰቡ  እምነት እያጣ ነው ሙያዊ  ስነምግባር ሕጋዊ  አሠራር  የሚባል ነገር የለም የኅብረተሰቡን እምነት ለማግኘት ልዩ ሥራ ሊሰራ ይገባል ሁሉም ነገር በፖለቲካ በዘር ዓይን የሚታይ ከሆነ የአገሪቱ እጣ የከፋ ነው።» ሲሉ መክረዋል።

Burundi, Symbolbild Folter
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

በሶማሌ ክልል ለዓመታት እስር ላይ የቆዩ የአካባቢው ተወላጆች ጄል ኦጋዴን በመባል በሚታወቀው እስር ቤት ደረሰብን ያሉትን አስፈሪ ሰቆቃ ምስክርነት የሰጡበትን መረጃ የተከታተሉ ወገኖች የየበኩላቸውን አስተያየት ሰንዝረዋል። ቀድሞ በእስረኝነት የቆዩት ወገኖች ከጅብ ጋር፤ ከነብር አጠገብ፤ አልፎ አልፎም እባብ በታሰሩበት ቦታ ሆን ተብሎ እንዲገባ ይደረግ እንደነበር በመግለጽ ታሪካቸውን ማጋራታቸውን ያደመጡት አበባው በትዊተር፤ «ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይደገም ርግጠኛ መሆን አለብን» ሲሉ፤ ያምራል ሀገሬ የሚል ስም ያላቸው የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «እኔን በጣም የሚያስፈራኝ የዛሬዎቹም አብዛኛዎቹ እንዲህ አይነት ግፍ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ጋር አብረው ይሰሩ የነበሩ ናቸው እና አሁንስ እስር ቤቶቻችን እንዴት ናቸው? ማንንም የማይፈሩ የማንም ጥገኛ ያልሆኑ በህዝብ እምነት የሚጣልባቸ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ እንዲሁም ግለሰቦችንየያዙ ኮሚቴዎችን በየቦታው በማቋቋም በየግዜው ፍተሻ ሊደረግባቸው ይገባል ሰምተ ዝም ማለት የለብንም።» ብለዋል።

ቹቹ የመሲ እህት የተባሉ በዚሁ በፌስቡክ፤ «ወይ ጉድ ሴይጣን እራሱ ይሄን ቢሰማ በተንኮል በለጡኝ ብሎ ይከሳቸው ነበር። ሴይጣን የሚቀናባቸው የሴጣን አለቆች አሉ ማለት ነው እረ ወይኔ እኔ እኮ ፈጣሪዬን ሁሌ እንዳሳዘንኩት ነው ብዬ እራሴን እወቅሳለሁ ስሞት የት ነው የምገባው እላለው አሁን እነዚ ሰዎች ሲሞቱ ወዴት ሊገቡ ነው ጋሃነብ እራሱ ቦታ የላቸውም» ሲሉ አውግዘዋል። ሙሉጌታ አብራሃ ደግሞ፤ «ህወሓት ተጠያቂ. ሊሆን ኣይችልም አማራ፣  ክልል አዴፓ ፣  ኦሮሞ ክልል ኦዴፖ ሲሆን. የሶማሌ. ክልል ደግሞ የክልሉ መስተዳደር ነዉ ።  በአሁን ሰሰዓት. ሰው በጠራራ ፀሃይ በቁሙ. እየታረደ. ተዘቅዝቆ እየተገደለ ንብረት እየተዘረፈ ባንኮች እተዘረፉ የወያኔ እጀ አለበት. ልትሉ ነወ::» በማለት ረዘም ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ