1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ዝግጅት

ዓርብ፣ ጥቅምት 26 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ሊሰጥ ጥቂት ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል። ለመሆኑ ተፈታኞቹ ራሳቸውን ምን ያህል አዘጋጅተዋል?ያነነጋገርናቸው ተማሪዎች የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ። ስጋት ያላቸውም አሉ። ከፈተናው ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ደግሞ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲንም ምላሽ ሰጥቶናል። 

https://p.dw.com/p/42Zwc
Äthiopien Lidya Meles und Abiturientin
ምስል M.Teklu/DW

ጤና ይስጥልኝ የተከበራችሁ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤ የሰማችኋቸው ወጣቶች ሰሞኑን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ናቸው። ተማሪዎቹ አምና መፈተን የነበረባቸው ሲሆን፤ የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ጫና ምክንያት እና ሌሎች የሀገሪቱ ችግሮች ፈተናውን ለረዥም ወራት ሳይወስዱ እስካሁን ቆይተዋል። ሰሞኑን ደግሞ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እያየለ መጥቷል። በዚያው መጠን በተለያዩ ቦታዎች በተለይ በአማራ ክልል በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የማይፈተኑ መሆኑም እየተነገረ ነው። መፈተን የሚችሉትስ ተማሪዎች ምን ያህል ፈተናቸው ላይ ያተኩሩ ይሆን? ፈተናውስ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይሰጣል? 
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳሬክተር ተፈራ ፈይሳ «አዎ ፈተናው ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ባለው ጊዜ ውስጥ ይሰጣል» ይላሉ። ይህ ግን ግጭት ያለባቸው አካባቢዎችን አያካትትም እንደሳቸው ገለጣ።« ተማሪዎቹም ቀድሞ ተነግሯቸዋል ያውቁታል» ይላሉ።  የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ትናንት ሐሙስ እንዳስታወቀው «ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡ 164 ሺህ ተማሪዎች መካከል ጦርነቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት 33 ሺህ ያህል ተማሪዎች» ፈተናውን እንደማይወስዱ ይፋ አድርጓል። 
አቤል ኢሳያስ መፈተናቸውን ከሚያውቁ ተማሪዎች አንዱ ነው። «ዛሬ ዓርብ ስለፈተናው ገለፃ ሊደረግልን በቴሌግራም ቻናላችን ጥሪ ደርሶናል መታወቂያም ወስደናል» ይላል የሀዋሳ ከተማ ተማሪው። « አምናም ካቻምናም የተማርነውን እየከለስኩ እየተዘጋቸው ነበር። ግን ቢያንስ አሁንን ያረፍንበትን ጊዜያት ተምረን ቢሆን ጥሩ ነበር» 
ሜሮን መኩሪያም የሀዋሳ ከተማ ተማሪ ናት። እሷም በግሏ ለፈተና እየተዘጋጀች ነው። ይሁንና ብዙ ስጋቶች አሏት። « ሀገር ውስጥ ያለው ችግር ቢረብሸንም በግሌ እየተዘጋጀሁ ነው። በሽታውም አለ። ከብዙ ጭንቀት ጋር ነው እየተፈተንን ያለነው።» የምትለው ሜሮን ሁለት የትምህርት ዓይነቶች ሳይሰጣቸው እንደቀሩ ትናገራለች። 
ዮሐንስ ከበደ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ነው። እሱም የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሆነ፤ ነገር ግን በአጥጋቢ ሁኔታ ትምህርት እንዳላገኘ ይናገረራል። « ለፈተና የተቻለኝን ያህል እያጠናሁ ነው። »
በበቂ ሁኔታ አልተማርንም የሚለውን የተማሪዎቹን ወቀሳ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳሬክተር ተፈራ ፈይሳ ያጣጥላሉ። « አሁን የሚሰጠው ፈተና ግንቦት መሰጠት የነበረበት ነው። እንደውም ተማሪዎቹ ለመፈተን ሰፊ ጊዜ አግኝተዋል። » ይሁንና የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት በሙሉ ተምረዋል አልተማሩም የሚለውን የሚመዝነው ተማሪዎቹ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው ይላሉ  አቶ ተፈራ። 
የድሬደዋ ቤተ መዛግብት እና መጻሕፍት አስተባባሪ ኤርሚያስ ታደሰ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት በተለይ «በርካታ ሴት ተማሪዎች ከቤት የሚገጥማቸውን ጫና ተቋቁመው «ወደ ቤተ መጻሕፍት በመሄድ ሲያጠኑ ቆይተዋል። « በተለይ በዚህ አመት ያለው ነገር ከኮሮና በኋላ ትምህርት ተዘግቶ ስለተከፈተ ይሁን  የወጣቶች የማንበብ ፍላጎት ልቆ ነው ያየሁት እኛ አገልግሎት እንኳን መስጠት እስኪያቅተን ድረስ። » ይላሉ።
ንፁህ፣ ፌቨን እና በአምላክ የዚህ ቤተ-መጻሕፍት  ተጠቃሚዎች ናቸው። ለፈተናም በቂ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ከዶይቸ ቬለ ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል። « የራሴ ጥረት አለ የአስተማሪዎቼ፣  ያልገባኝን ነገር ትምህርት ቤት ስሄድ እየይቃለሁ» ትላለች ንፁህ » ለፈተና በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁ የምትለው ፌቨን ደግሞ « ቀደም ያሉ ፈተናዎችን በመስራት እና በመከለስ ዝግጅት እያደረኩ ነው» በአምላክ ደግሞ« ሰዓቴን ከፋፍዬ አጠናለሁ። ቤተሰቦቼን ማገዝ ባለብኝ ሰዓት አግዛለሁ።» ትላለች።
«ፈተናው በተለመደው መንገድ ይሰጣል» ያሉን  የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳሬክተር ተፈራ ፈይሳ በመጨረሻ « በጊዜ መፈተን ሲገባን ረዥም ጊዜ ነው የወሰደው የዘገየነው ለእነሱም ጥቅም መሆኑን ተገንዝበው በተረጋጋና በጥሩ ስነ ልኖና ለጥሩ ውጤት በሚያበቃቸው ሁኔታ ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ነው መልዕክት የምናስተላልፈው» ይላሉ። 

Äthiopien Lidya Meles und Abiturientin
የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ በአምላክ ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊዲያ መለስ ጋርምስል M.Teklu/DW
Internally displaced Persons in Dessie
ተፈናቃዮች በደሴ ከተማምስል Alemnew Mekonnen/DW

 ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች