1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፣ የፖለቲከኞች እስጥ አገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2011

ተስማማን አሉ-አመንናቸዉ።ኢትዮጵያ ገቡ- የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀበላቸዉ።በሠላም እንታገላለን አሉ-ሕዝብ  ፈቀዳቸዉ።ደጋፋቸዉ።ተባበራቸዉም። ያ ሕዝብ ከእምነት፣አቀባበል፣ ድጋፍ፣ ትብብሩ ያተረፈዉ፣ ቢያንስ እስካሁን የዘመድ ወዳጅ-ዉላጁን አስከሬን መቁጠር ነዉ።በሐዘን እራሮት መትከን፣ ተራዉን በሥጋት መጠበቅ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3AbEr
Äthiopien Bevölkerung begrüßen OLF-Führungskräfte
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ይወቃቀሳሉ፤ሰው ይሞታል

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ከኦነግ ጋር ያደረገዉን ስምምነት ጥሷል።የኦነግ ታጣቂዎችም  «እራሳቸዉን እንዲከላከሉ» ታዘዋል።ደግሞ በተቃራኒዉ ኦነግ ከመንግስት ጋር የገጠመዉን ዉዝግብ ለማስወገድ «ይደራደራል» ብለዋል።ወቀሳ፣የዉጊያ ትዕዛዝ እና ድርድር።ግራ አጋቢ አንድነት።ኦነግን ጨምሮ በአብዛኛዉ ኤርትራ የነበሩ የቀድሞ አማፂ ቡድናት «በሰላም ለመታገል» ኢትዮጵያ የገቡት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት እንደሆነ መንግስትም፣ድርጅቶችም በየጊዜዉ አስታዉቀዋል።ወትሮም መንግሥት አማፂያኑን አሸባሪ፣ ገንጣይ፣ ፅንፈኛ ሲል ሕዝብ አልመከረም፤ አልወሰነም የቀረበለት መረጃም የለም።ከስድት-አራት ወር በፊትም እኒያ ቡድናት ከመንግሥት ጋር ተስማሙ ሲባልም-መባሉን እንጂ  ስምምነቱን ሕዝብ አያዉቀዉም፣ አልተቸበትም።አሁን ቢያንስ አንዱ ስምምነቱ ተጣሰ አሉት።እንዴት? ላፍታ እንጠይቅ።

                      

ተስማማን አሉ-አመንናቸዉ።ኢትዮጵያ ገቡ- የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀበላቸዉ።በሠላም እንታገላለን አሉ-ሕዝብ  ፈቀዳቸዉ።ደጋፋቸዉ።ተባበራቸዉም። ያ ሕዝብ ከእምነት፣አቀባበል፣ ድጋፍ፣ ትብብሩ ያተረፈዉ፣ ቢያንስ እስካሁን የዘመድ ወዳጅ-ዉላጁን አስከሬን መቁጠር ነዉ።በሐዘን እራሮት መትከን፣ ተራዉን በሥጋት መጠበቅ ነዉ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር  አቶ ዳዉድ ኢብሳን ከሁለት ሳምንት በፊት በስልክ አነጋሬያቸዉ ነበር።የየአካባቢዉን ግጭት፣ ግድያ፣ ስደትን «ጊዚያዊ እና አላፊ» ብለዉት ነበር።የሕዝቡ ሥጋትም ብዙ አያሰጋቸዉም።

 

ኦሮሚያ-ሶማሌ ድንበር የተገደለዉ ተቀብሮ፣ የቆሰለዉ ተቆጥሮ፣ የተፈናቀለዉ ሠፍሮ ሳያበቃ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ጉጂ-አማሮ፣ሲዳማ-ወላይታ፣ ገሪ-ቦረና፤ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኒ ሻንጉል-ኦሮሞያ፣ መሐል ኢትዮጵያ ቡራዩ-ጋሞ-ኦሮሞ፣ አዲስ አበበ፣ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ራያ፣ ምዕራብ ጎንደር ቅማንት-አማራ፣ ምስኪን ነዋሪዎች ይገደሉ፣ ይቆስሉ፣ ይፈናቀሉም ያዙ።ሆስፒታል በሞርታር ይጋያል።ሞያሌ። የደካማ ገበሬዎች ደካማ ጎጆ፣ ሰብል በእሳት ይነዳል።አማሮ፣ የሕዝብ ማመላለሻ አዉቶቡስ በተቀበረ ፈንጂ ይነጉዳል።ቶንጎ።የዋሑ ኢትዮጵያዊ ያለፈዉ ስርዓት ያደርስበት ከነበረዉ ግፍ መገላገሉን በቅጡ ሳያጣጥም ዕለት በዕለት ይገደላል።ይቆስላል፣ ይሰደዳልም።

 Logo Oromo Liberation Front

መንግሥት የሕዝቡን ሠላም እና ፀጥታ ለምን አያስከብርም የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ ብዙዎቹ የመንግሥት ደጋፊዎች የሚሰጡት መለስ በ1983 የመንግስት ሥልጣንን የተቆጣጠረዉ ኃይል ይሰጡት የነበረዉ ዓይነት።«ያለፈዉ ሥርዓት ናፋቂ» የሚል ስድብ ነዉ።ሕዝብ ግን የአማሮዉ ነዋሪ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ይጠይቃል።«መንግስት አለ?  ካለስ ጆሮ አለዉ?» እያለ

ለዉጥ አራማጁ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት ባደረገዉ ምሕረት፣ ጥሪ እና ስምምነት መሠረት በሺሕ የሚቆጠሩ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ አቀንቃኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች ከእስር ቤት ተለቅቀዋል።ዉጪ የነበሩ፣ የአማፂ ቡድናት ታጣቂ እና መሪዎች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የመገናኛ ብዙሐን ሠራተኞች፣ የፖለቲካ አቀንቃኝ፣ ምሕራንና ጋዜጠኞች አዲስ አበባ ዉስጥ ይርመሰመሳሉ።

ሕዝብ በአደባባይ ሠልፍ  በጭፈራ፣ ደስታ እልልታ ሲቀበላቸዉ፣ ፌስታ ደስታዉ፣ ከአስፈሪዉ ሥርዓት የመላቀቁ እፎይታ ዉጤት ብቻ አልነበረም።ለወደፊት ሠላም፣ ደሕንነት ብልፅግናዉ ዋስትና ያገኘ መስሎት፣ ለዋስትናዉ ፅናት ይሰሩልኛል የሚል ተስፋ ነፀብራቅም ጭምር ነበር እንጂ።

የሞያሌ፤የአማሮ፣ የማረቆ፣የመስቃን፣ የበኒ ሻንጉል፣ የወለጋ፣ የጭልጋ፣የአላማጣ ሕዝብን የድረሱልኝን ጥሪ ጠጋ ብሎ ለማድመጥ ወደየአካባቢዉ የተጓዘ የቀድሞ ዲያስፖራ ቢያንስ እስካሁን የለም።ካለም አልሰማንም።የሰማነዉ ባደደባባይ ሠልፍ በድስታ፤ ደስታ ተስፋ ለተቀበላቸዉ ወይም እንወክልሐለን ለሚሉት ሕዝብ «ከመንግስት ጋር ተስማምተን መጣን» ያሉት ፖለቲከኞች ለዚያዉ ህዝብ፣ ያንኑ መንግሥት መዉቀስ-ማዉገዛቸዉን ነዉ።

                                  

አቶ ዳዉድ ኢብሳ። የኦሮሞ ነፃት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር ባለፈዉ አርብ።አቶ ዳዉድ እንዳሉት መንግስት ከድርጅታቸዉ ጋር ያደረገዉን ስምምነት ጥሶ አንድ ቦታ የሰፈሩት የግንባሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን ሳይቀር ያንገላታል።የኢትዮጵያ መንግሥት ከኦነግ፣ከኦብነግ፤ ከደምሒት፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ይሁን ከሌሎች ጋር ያደረገዉን ስምምነት በሚስጥር የያዘበትን ምክንያት ከዚሕ ቀደም ጠይቀናል።ዛሬም እንጠይቃለን።

ስምምነቱን የፈረሙ ቡድናት ወይም መሪዎቹ «በሰላማዊ መንገድ ለመታገል» ከማለታቸዉ ዉጪ የፈረሙትን ስምምነት ዝርዝር ይዘት በሚስጥር ይዘዉ ሥለሠላም ዴሞክራሲ፤ ሥለሰብአዊ መብት፣ በተለይ ሥለ ፕረስ ነፃነት የሚደሰኩሩትን ማመን ላስተዋይ ተንታኝ ሲበዛ ከባድ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ እና አቀንቃኝ አቶ ገረሱ ቱፋም ምን አዉቀን ምን እንበል ዓይነት ይላሉ።

አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ድርጅታቸዉ ወደ ጦርነት እንደማይመለስ ቃል ገብተዉ ነበር።

ባለፈዉ አርብ ግን መንግሥት ስምምነቱን «ጥሷል» ነዉ ያሉት።ሥለዚሕ መፍትሔ ማግኘት የነበረበት መፍትሔ አላገኘም ማለት ነዉ።እንዲያዉም አቶ ዳዉድ ሠራዊታቸዉ ይፈፀምበታል ያሉትን ጥቃት እንዲከላከል መታዘዙን አስታዉቀዋል።ሠራዊቱ እራሱን ይከላከላል ማለት ታጥቋል ማለት ነዉ።አንድ ሠፈር ወይም ካምፕ አልሠፈረም ማለት ነዉ።ስምምነቱ የኦነግ ሠራዊት ሲታዘዝ የሚተኩሰዉ፣ ሳይታዘዝ የሚንተራሰዉ ጠመንጃ እንደታጠቀ እንዲቆይ ይፈቃዳል ማለት ይሆን? የኦነግም፣ የመንግሥት ሹማምንት መልስ እንዲሰጡን ካለፈዉ አርብ ጀምሮ በተደጋጋሚ ደዉለን ነበር።አልተገኙም።

Karte Äthiopien AM

የፖለቲካ አቀንቃኝ ገረሱ ቱፋ እንደሚሉት ኦነግ ከመንግሥት ጋር ያደረገዉ ሥምምነት ዝርዝር ይዘት ምንም ሆነ ምን በአንድ ሐገር ዉስጥ ከመንግሥት ሌላ ሌላ ታጣቂ ኃይል የሚኖረዉ ሐገሪቱ ከፈረሰች አለያም ጦርነት ዉስጥ ከሆነች ብቻ ነዉ።

                                     

አቶ ዳዉድ ባለፈዉ አርብ ያሉትን ከማለታቸዉ በፊት ምዕራብ ኦሮሚያ ሰፍሯል የሚባለዉን የኦነግ ሸማቂ ኃይል ያዛሉ የተባሉት ግለሰብ ያስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ ዉስብስብ፣ አስጊ፣ አስፈሪም አድርጎታል።አዛዡ የሚመሩት ሸማቂ ኃይል ከመግሥት ጦር ጋር የገጠመዉን ዉጊያ እንደሚቀጥል አስታዉቀዋል።

አቶ ገረሱ እንደሚሉት የአዛዡ መግለጫ ምዕራብ ኦሮሚያ የሠፈረዉ የኦነግ ተዋጊ ኃይል ለግንባሩ ሊቀመንበር ለአቶ ዳዉድ ኢብሳ ለራሳቸዉ የሚታዘዝ እንዳልሆነ ጠቋሚ ነዉ።

አቶ ዳዉድ ኢብሳ የጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤ እንዳበቃ የኦሮሚያ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ዴምክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣዉ መግለጫ ትዕግስት ፍራቻ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል።መግለጫዉ  በስም የጠቀሰዉ ድርጅት ወይም ፓርቲ የለም።ይሁንና «ሲዘርፉን፣ ሲያስጨንቁን---የነበሩ፣ ከስልጣን የተባረሩ» የሚላቸዉ ኃይላት «በዘረፉት ገንዘብ ኦሮሚያን የጦር ሜዳ ለማድረግ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ነዉ» ይላል።ጠንካራ ነዉ።

አቶ ገረሱ ቱፋ እንደሚገምቱት መግለጫዉ የቀድሞ የሕወሐት ባለሥልጣናትም፤ ኦነግንም፤ ሌሎች ለዉጡን የማይፈልጉ ወይም ለዉጡ በሚፈልጉት መንገድ ባለመሔዱ የሚቃወሙትንም በሙሉ የሚነካ ነዉ።ኦዴፓ፣ «የለዉጡን ሒደት ለአንድ ሴኮንድም ሳይደናቀፍ ወደ ድል ምዕራፍ ለማሸጋገር» ማንኛዉንም  እርምጃ ለመዉሰድ ወስኗል» ይላል።የእርምጃ-ዉሳኔዉን ምንነት አናዉቅም።ኦነግ ከኦዴፓ፣ ኦዴፓ ከሕወሐት የቀድሞ መሪዎች ጋር የገጠመዉ አተካራ ደም እያራጨ መቀጠሉን ግን ጠቃሚ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ