1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዜጎቻቸዉን ከዩክሬን ለማውጣት እየተጣደፉ ያሉ የአፍሪቃ መንግሥታት

ቅዳሜ፣ የካቲት 26 2014

የአፍሪቃ ሀገራት ዜጐቻቸውን ከዩክሬይን ለማስወጣት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል። አፍሪቃዉያን ተማሪዎች ከዩክሬይን በመሸሽ ላይ ሳሉ ድንበር ላይ በቆዳ ቀለም ምክንያት መድሎ  መታየቱ እንደሚያሳስባቸው ከተናገሩ በኋላ መንግሥታት ዓለም አቀፉን ሕግ እንዲያከብሩና ከዩክሬይን ጦርነት የሚሸሹትን ሁሉ እንዲያግዙ የአፍሪቃ ኅብረት አሳስቧል። 

https://p.dw.com/p/483To
Ukraine-Konflikt | Afrikanische Studenten aus der Ukraine in Rumänien
ምስል Cristian Ștefănescu/DW

ዩክሬን ዉስጥ ከሚኖሩ አፍሪቃዉያን መካከል በቁጥር ናይጀርያዉያን ይበልጣሉ

 

የአፍሪቃ ሀገራት ዜጐቻቸውን ከዩክሬይን ለማስወጣት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል። በዩክሬይን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የነበሩ የአፍሪቃ ተማሪዎች ከዩክሬይን በመሸሽ ላይ ሳሉ ድንበር ላይ በቆዳ ቀለም ምክንያት መድሎ  መታየቱ እንደሚያሳስባቸው ከተናገሩ በኋላ መንግሥታት ዓለም አቀፉን ሕግ እንዲያከብሩና ከዩክሬይን ጦርነት የሚሸሹትን ሁሉ እንዲያግዙ የአፍሪቃ ኅብረት አሳስቧል። 

ምንም እንኳ አንዳንድ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ትዉልድ ሃገራቸዉ በደስታ ቢመለሱም ብዙዎቹ በዩክሬንና  አጎራባች ሃገራት መቆየትን መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ በዩክሬይን ከመሰረቱት ቤተሰብ ጋር እዝያዉ ዩክሬይን መሆንን  መርጠዋል።  

ከ400 የሚበልጡ ናይጄሪያውያን በዩክሬን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ሸሽተው በዚህ ሳምንት አርብ አገራቸው ተመልሰዋል። የናይጄርያ መንግሥት ወደ ሩሜንያ በላከዉ ልዩ በረራ ከዩክሬይን ሸሽተዉ ሩሜንያ፤ ፖላንድ፤ ስሎቫኪያ እና ሃንጋሪ የገቡ ዜጎቹን ነዉ ወደ ሃገር ሰብስቦ መልሶአል። ዜምባቤም በዩክሬይን የነበሩ እና ጦርነቱን ሸሽተዉ ወደ ሩሜንያ፤ ሃንጋሪ፤ ስሎቫኪያ እና ፖላንድ የገቡ 118 ተማሪዎችን ወደ ሃገር መልሳለች።

ከኬንያ የመጡ 79 ተማሪዎች ደግሞ የዩክሬይንን ጦርነት ሸሽተዉ በጎረቤት ሃገራት ማለትም በፖላንድ፤ ሩሜንያ፤ ሃንጋሪ ጥገኝነት ጠይቀዋል። አንድ ኬንያዊ ግን ወደ ሃገሩ መመለሱን የኬንያ ባለሥልጣናት መግለፃቸዉ ነዉ የተዘገበዉ። ይሁንና አሁንም ሌሎች በርካታ ኬንያዉያን ተማሪዎችን ከዩክሬን የተለያዩ ከተሞች እንዲወጡ የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግስት በማስተባበር ላይ መሆኑ ተነግሮአል። 

Ghana | Studenten wurden aus der Ukraine evakuiert
ምስል Isaac Kaledzi/DW

የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ በዩክሬይን 38 ተማሪዎች ወደ ጎረቤት ፖላንድ መሻገራቸዉን ገልፆአል።  በጀርመን እና በስዊድን የሚገኙ የታንዛኒያ ኤምባሲዎች ባለስልጣናት አሁንም በዩክሬይን ዉስጥ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚገኙ ዜጎችን በሙሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየሰሩ መሆኑ ተገልፆአል። የአይቮሪ ኮስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንዲያ ካማራ እንደተናገሩት ዜጎቻቸዉን ከዩክሬይን ለመውጣት ዩናይትድ ስቴትስን  እና የአዉሮጳ ህብረትን ድጋፍ ለመጠየቅ ስብሰባ ማካሄዳቸውን የአቢጃን ዜና ድረ-ገጽ አስነብቦአል።

ጋናውያን፣ ናይጄሪያውያን፣ የዚምባብቤ ዜጎች ፣ ኢትዮጵያውያን፣ ግብጻውያን፣ እና ህንዶች ጨምሮ በርካታ የዉጭ ተማሪዎች አሁንም ዩክሬን ዉስጥ እንዳሉ ይገመታል። የናይጀርያ መንግሥት ከ 400 በላይ ተማሪዎችን ወደ ሃገሩ መመለሱ ቢነገርም ፤ ከ 2000 በላይ የሚሆኑ ናይጀርያዉያን ጦርነት ዉስጥ ካለችዉ ዩክሬይን በሰላም ወጥተዉ በዩክሬን አጎራባች ሃገራት ዉስጥ እንዳሉ ነዉ የገለፀዉ።

ዩክሬን ዉስጥ ከሚኖሩ አፍሪቃዉያን መካከል በቁጥር ናይጀርያዉያን ይበልጣሉ ያለን ኢትዮጵያዊዉ ወልጫፎ  ነጋሽ ገብሬ በዩክሬይን መዲና ኪይቭ ዉስጥ ሲኖር 35 ዓመት ሆኖታል። ወደ ዩክሬን የመጣዉ ለትምህርት ነበር ትምህርቱን ጨርሶ ትዳር ይዞ እየኖረ ነዉ ። የአንዲት የ 20 ዓመት ሴት ልጅ አባትም ነዉ። 

በዩክሬይን እስር ላይ መሆናቸዉን ለአንዳንድ የዉጭ ሚዲያ እና የድረገፅ ሚዲያ የተናገሩ ወጣት ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ ብንሰማም ያሉበትን አድራሻና ስልክ ቁጥር ማግኘት አልቻልንም።

ሙሉ ጥንቅሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

 

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ