ዛሬም የሚያሳስበው የTB ስርጭት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ዓለምን ያዳረሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንድ ሚሊየን ሰዎችን መፍጀቱ ብዙዎችን አስደንጓጧል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን ለበርካታ አስርት ዓመታት በየዓመቱ በTB ምክንያት ከ1,5 እስከ ሁለት ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ያልቃሉ። ኢትዮጵያ TB በሰፊው ተስፋፍቶ ከሚገኝባቸው 30 ሃገራት አንዷ ናት። የጤና ሚኒስቴር የTBን ስርጭት ለመግታት ጊዜው አሁን መሆኑን ከሳምንታት በፊት የዓለም የTB ቀን ሲታሰብ ይፋ አድርጓል። ዶክተር አንዳርጋቸው ኩምሳ በፌደራል ጤና ሚኒስቴር መድኃኒት የተላመደ TB ከፍተኛ አማካሪ ናቸው። ኢትዮጵያ የTB ተሐዋሲ በከፍተኛ ደረጃ ከተሰራጨባቸው 30 ሃገራት አንዷ ናት ሲባል በተጨባጭ ያለው ይዞታ ምን እንደሚመስል እንዲህ ያስረዳሉ።
«የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ነው ስንል አሁን ያለው የTB በሽታ ስርጭት ሁኔታ ከ100 ሺህ 140 ሰዎች ላይ TB እንዳለባቸው ነው የሚያሳየው። ከዚያም አልፎ ግን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከእያንዳንዱ መቶ ሺህ ሰው ውስጥ 19 ሰዎች በTB ምክንያት ይሞታሉ። ይኼ ማለት በዓመት ውስጥ ቁጥሩ የሚያሳየው 21 ሺህ አካባቢ በTB ብቻ ይሞታሉ፤ ይኼ ማለት በየአንዳንዱ ቀን ወደ 57 ሰዎች በTB ይሞታሉ ማለት ነው።»
ባለሙያው እንደሚሉት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ የነበረው የTB በሽታ ስርጭት መጠኑ ከጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓ,ም ወዲህ ቀንሶ የታየ ለውጥ መሆኑ ነው። ቀድሞ ከነበረውም ወደ ከ20 እስከ 27 በመቶ መቀነሱን ቢገልጹም አሁንም ቁጥሩ በጣም ትልቅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ከዚህም ሌላ መድኃኒት የተላመደው የTB በሽታን አስመልክቶም ኢትዮጵያ አሁንም ችግሩ በሰፊው ከሚታይባቸው ሃገራት አንዷ መሆኗንም ገልጸዋል።
TB ለመላው ዓለም የራስ ምታት ሆኖ የከረመ አደገኛ ተሐዋሲ ቢሆንም በተለይ በሕንድ፤ ኢንዶኔዢያ፤ ደቡብ አፍሪቃ፤ ባንግላዴሽ፣ ቻይና፤ ፊሊፒንስ፣ ናይጀሪያ፣ ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን እጅግ የተስፋፋ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። እነዚህ ሃገራት ከመላው ዓለም ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የበሽታውን ስርጭት የተሸከሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባው ያድምጡ፤
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ