1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዘካተል ፈጢርን የሚያዘው የረመዳን ወር ሲጠቃለል

ኢሳያስ ገላው
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2018

ዘካተል ፈጢር በረመዳን ወር ማጠቃለያ ላይ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ የሆነ የምጽዋት አይነት ነው። ይህ ዘካ ጾመኛው በጾም ወቅት ለፈጸማቸው ጥቃቅን ስህተቶች ማሰረያና ለድሆች ደግሞ የባዕል ቀን ደስታን መጋሪያ እንዲሆን ታዝዟል።

https://p.dw.com/p/5Alse
የደሴ ከተማ ምዕመናን በዒድ ስግደት ላይ
ዘካተል ፈጢርን የሚያዘው የረመዳን ወር ሲጠቃለልምስል፦ Esayas Gelaw/DW

አቅመ ደካሞችን መርዳት አንዱ ኃይማኖታዊ ግዴታ ስለመሆኑ

ዘካተል ፈጢር  በረመዳን ወር ማጠቃለያ ላይ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ የሆነ የምጽዋት አይነት ነው። ይህ ዘካ ጾመኛው በጾም ወቅት ለፈጸማቸው ጥቃቅን ስህተቶች ማሰረያና ለድሆች ደግሞ የባዕል ቀን ደስታን መጋሪያ እንዲሆን ታዝዟል።

እድሜ፣ ጾታና የጤና ሁኔታ ሳይለይ በሁሉም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው።ለራሱና ለቤተሰቡ የዕለቱን ቀለብ አትርፎ የተረፈው ሰው ሁሉ ለራሱና ለሚያስተዳድራቸው ቤተሰቦቹ ማውጣት ይኖርበታል። ዘካ ተልፊጥር አቅም ያለዉ ሙስሊም ሁሉም ከኢድሶላት በፊት   ለድሆች  ምፅዋት የሚሰጥበት ስርአት ነዉ

የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ደሃው ከሀብታሙ እንደቤቱ በዓሉን እንዲያከብር ከፈጣሪ የላቀ ምንዳ ለማግኘት የረመዳን ጾም ሊገባደድ ሁለት ቀን ሲቀረው ጀምሮ ህዝበ ሙስሊሙ ከእምነቱ ትእዛዛቶች መካከል ቀዳሚ የሆነውን ዘካተል ፊጥርን ይከውናሉ። ይህ የዘካ አይነትም የረመዳን የጾም ወቅት ሲፈጸም የሚወጣ ነው ይላሉ ሸሁ መርአሊ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የደሴ አረብ ገንዳ መስጊድ ምክትል ኢማም።

 "ዘካተል ፊጥር ማለት ረመዳን ሲፈጸም፣ ረመዳንን ስንጨርስ የምናወጣው ዘካ ነው። የምናወጣው የመልካም ስራ አይነት ነው። ለደሃዎች ሁለት ምክንያቶች አሉት እሱ የተደነገገበት፤ ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የደነገጉት። አንደኛ በጾም ውስጥ አንድ ግድፈቶች ጎደሎዎች ካሉ ለነዛ ጎደሎዎች ማሽማር ወንጀል ያስምራል ይሄ ዘካ። ሌላኛው ለደሃዎቹ ጉርሻ ነው ብለዋል። እኛ በጾሙ ቀን ገንዘብ ያለን ሰው ተደስተን ስንውል እነሱ ተርበው ቀልባቸው ተሰብሮ ተቸግረው እንዳይውሉ፣ ብሎም ልመና እንዳይሰማሩ ለዛ ተብሎ የተደነገገ የዘካ አይነት ነው።"

በተለያዩ የኑሮ ሁኔታ የተቸገሩን መርዳት ዋነኛ አላማ ያደረገው ዘካተል ፊጥር የሚከውኑ ሰዎች የላቀ የህሊና እርካታ ያገኛሉ የሚሉት ወይዘሮ ሱመያ አንድሪስ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ዘካ በመሰብሰብ በዓሉን ሁሉም እኩል እንዲያከብረውም እንደሚሰሩ ነው የሚናገሩት።

"ስሜትና ደስታን ይፈጥራል። የእኛ ቤት ሞልቶ ተደስተን ልጆቻችንን አልብሰን ምናምን ስንወጣ ሌላ ቤት አለ ደግሞ ያ ቤትም እንደ እኛ መሆን አለበት በአቅም በተፈቀደ መልኩ። ስለዚህ እኛ አሁን የምንሰበስበው የእኛን ብቻ አይደለም፤ ዘመዶቻችንን፣ የጎረቤቶቻችንን፣ የጓደኞቻችንን ሁሉ እንሰበስብና እንደ እኛ ተደስተው እንዲያሳልፉ የማድረግ ነው።"

ዘካተል ፊጥርን ለ24 ሰአት የሚበላው ኑሮት ትርፍ ያለው ሁሉ ሊያካፍል ህጉን ሊተገብር ይገባል የሚሉት ሸህ ዑመር አሊ በማህጸን ውስጥ ለተረገዘ ልጅ እንኳ ቤተሰቦቹ የማውጣት ግዴታ እንዳለባቸው ነው የሚገልጹት።

የደሴ ከተማ ምዕመናን በስግደት ላይ
ስሜትና ደስታን ይፈጥራል። የእኛ ቤት ሞልቶ ተደስተን ልጆቻችንን አልብሰን ምናምን ስንወጣ ሌላ ቤት አለ ደግሞ ያ ቤትም እንደ እኛ መሆን አለበት በአቅም በተፈቀደ መልኩ።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

 "የሚበላው ኑሮት ትርፍ ካለው ያንን ያካፍላል። ሁሉም በትልቅም በትንሽም ላይ ነው የሚወጅበው። በወንድም በሴትም ላይ ነው የሚወጅበው። ሰውየው በተሰጠው ሰዓት ለእሱም ለልጆቹም ለሚስቱም ያወጣል። ካላቸው ሚስትና ልጆች ገንዘብ ከእነሱ ቢወጡም ይቻላል። የተረገዘ ልጅ እንኳ ቢያወጡለት ይወደዳል፤ ዋጅብ ባይሆንም እንኳ የተወለደማ አባትየው ላይ ይወጅባል።"

ዘካተል ፊጥር የኢድ በዓል ከመውጣቱ በፊት ነው መሰጠት ያለበት የሚሉት የደሴ የአረብ ገንዳ መስጂድ ምክትል ኢማም የሆኑት ሸህ ዑመር አሊ ደሃዎች በዓሉን ተደስተው እንዲያከብሩ ዘካተል ፈጢር  ከኢድ ሰላት በፊት መጠናቀቅ እንዳለበትም ነው የሚናገሩት።

"ከኢዱ በፊት ሁለት ቀን ሲቀረው ጀምሮ ማውጣት ይቻላል። የሚወጅበው ጾሙ መጨረሻ ፀሃይ ሲገባ የኢደል ፊጥሩ ሌሊት ማታ ፀሃይ ሲገባ ጀምሮ ነው የሚወጅበው። ከዚያ በስተፊት ግን ሁለት ቀን ቀድሞ መስጠት ይቻላል። ኢድ ከመውጣቱ በፊት መሆን አለበት። ለምን የሚፈለገው እነሱም ደርሷቸው እንደኛው ተዘጋጅተው እንዲጠብቋቸው፣ ሲመጡ ቤታቸው ባዶ እንዳይገቡ ስለሚፈለግ ሸሪዓዊ የደነገገው ከሰላት በፊት መጨረስ አለበት። ከዚያ በኋላ ያለው እንደ ማንኛውም ሰደቃ ነው የሚሆነው።"

ዛሬ 1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሚከበርበት ወቅትም የሙስሊም እምነት ተከታዮች ሆነው ለበዓሉ እርድ ላላረዱ ሰዎችን በመደገፍም የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ የደሴ ከተማ ወጣቶች በፒያሳ አደባባይ በሬ በማረድ በነጻ ስጋ ሲያቃርፁ  ውለዋል።

 "ወሎ ስንባል እንግዲህ ያው ፍቅራችንም ሙስሊሙም ክርስቲያኑም አንድ ነን። እኔ አሁን ፍላጎቴ  ምንድን ነው ያው ለክርስቲያኑንም እናደርጋለን ሙስሊሞችንም በጎ አድራጎት ነው የምንሰራው። ሁልጊዜም በየአመቱ ኢድ አልፈጥር በሚመጣበት ሰአት ክርስቲያንም ብንሆን ሰው በመሆናችን ብቻ ግን ያው ሰውን ለመርዳት ሰውን ነው ፤ ሃይማኖት ምናምን አንልም። እኛ ክርስቲያን ስለሆንን ሙስሊሙን አንተውም፤ ሙስሊም ደግሞ እንደዚህ ቢያደርግ እንደኛ ቢያደርግ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።"
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ