1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረመላቸው የተለወጠ ምግቦች በምዕራቡ ዓለም

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7 2012

 በመላው ዓለም ዘረመላቸው የተለወጠ እህሎች በምድራቸው እንዲበቅል የፈቀዱ 26 ሃገራት ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ በተለይ በምዕራቡ ዓለም በተፈጥሮ መንገድ የበቀሉ አዝርዕት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚሸጡባቸው መደብሮች እየተበራከቱ ነው።

https://p.dw.com/p/3fJ9V
Symbolbild Genfood Mais Labor
ምስል Fotolia/igor

«ጤናና አካባቢ»

በአሁኑ ጊዜ በተለይ በምዕራቡ ዓለም በተፈጥሮ መንገድ የበቀሉ አዝርዕት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚሸጡባቸው መደብሮች እየተበራከቱ ነው። እንዲህ ያለው ምልክት ያላቸው ምርቶች ዋጋቸው ውድ ከመሆኑም ሌላ ጣዕማቸው የተለየ በመሆኑ የተጠቃሚዎቻቸው ቁጥር ጥቂት አይደለም። እንደውም እንዲህ ያሉትን ምርቶች የሚጠቀሙ ለጤናቸው ትኩረት የሚሰጡ ተደርገው ይወሰዳሉ።  በመላው ዓለም ዘረመላቸው የተለወጠ እህሎች በምድራቸው እንዲበቅል የፈቀዱ 26 ሃገራት ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዓለም ዘረመላቸው የተለወጡ እህሎችን ማምረት የፈቀዱ 26 ሃገራት ብራዚል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ አውስትራሊያ፣ ቦሊቪያ፣ ፊሊፒንስ፣ ስፔን፣ ቪየትናም፣ ባንግላዴሽ፣ ኮሎምቢያ፣ ሁንዱራስ፣ ቺሊ፣ ሱዳን፣ ስሎቫኪያ፣ ኮስታሪካ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ አርጀንቲና፣ ፓራጓይ፣ ዑራጓይ፣ ሜክሲኮ፣ ፖርቱጋል፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፓኪስታንና ማያንማር ናቸው። ቀሪዎቹ አርሶ አደሮቻቸው እነዚህን ሰብሎች እንዳያመርቱ በሕግ አግደዋል።  በተለይም በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓ,ም የአውሮጳ ሕብረት አብዛኞቹ አባል ሃገራት እንዲህ ያለው ዘር በመሬታቸው እንዳይበቅል ሲያግዱና በሩሲያ ደግሞ ማምረቱም ሆነ ምርቶቹ ወደሀገር እንዳይገቡ በማገዷ በወቅቱ ጉዳዩ የዓለምን ትኩረት መሳቡ ለታሪክ ተመዝግቧል። ሩሲያ ውስጥ ዘረመሉ የተለወጠ እህል ለምርምር ብቻ ነው የሚፈቀደው። የሀገሪቱ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም ፤«አሜሪካ ዘረመላቸው የተለወጠ ምርቶችን መመገብ ከፈለገች ራስዋ ትብላው። እኛ ያንን ማድረግ አንፈልግም፤ እኛ ተፈጥሯቸው ያልተለወጡ ምግቦችን ለማምረት በቂ ቦታና ዕድሎች አሉን።» ማለታቸውም ይጠቀስላቸዋል።  

ዘረመላቸው የተለወጡ ምርቶችን ተቃውሞ በዩናይትድ ስቴትስ 2013ዓ,ም
ምስል Reuters

ይህም ሆኖ በመሬታቸው ዘረመሉ የተለወጠ እህል እንዳይመረት ካገዱት ሃገራት  ብዙሃኑ  በዚህ መልኩ የተመረተውን ግን ለእንስሳት ቀለብነት ፈቅደዋል። ለምሳሌም ይህን የሚፈቅዱ የአውሮጳ ሕብረት ሃገራት  በየዓመቱ 30 ሚሊየን ቶን ዘረመሉ የተወጠ እህል በእንስሳት መኖነት ያስገባሉ። ዘረመላቸው የተለወጠ ሰብሎችን እናመርታለን አናመርትም የሚለው ውዝግብ ዓመታት የዘለቀ ቢሆንም መከራከሪያቸው መሠረቱ ሳይንሱም ሆነ ፖለቲካው እንደየሃገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚመዘን ነው። የአንዳንዶቹ አቋም በንግዱ ዓለም ራስን ከመከላከል ሌሎቹ ደግሞ ኅብረተሰቡ ለእነዚህ ምርት ካለው አስተሳሰብ የሚመነጭ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

አውሮጳ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የኖሩ ወገኖች ተፈጥሮውን ጠብቆ የተመረተ ለምግብ የሚሆን ሰብልም ሆነ አትክልትና ፍራፍሬ በውድ የሚሸጥባቸው ሱቆች ብቅ ብቅ ያሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያሉ መደብሮች እየተበራከቱ ሲሆን በምግብ ሸቀጥ መሸጫዎችም በተፈጥሮ መንገድ የተገኙ ምርቶች ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው። ጣዕማቸውም ይለያል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይህን ያስተዋሉት አቶ ዓለሜ ሰዎች ይህን ግንዛቤ እንዲያገኙ በሚል መረጃዎችን በቪዲዮ በማቀናበር በማኅበራዊ መገናኛው ማጋራት ጀምረዋል። እሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳ አሜሪካ ዘረመሉ የተለወጠ ሰብል የምታመርትና ምግቦችንም ለተጠቃሚ የምታቀርብ ብትሆንም ብዙሃኑ አሜሪካዊ  የሚመገበው ተፈጥሮውን የጠበቀ ምርት ነው።

ዘረመሉ የተለወጠ የድንች ምርት
ምስል AP

በዚህ ርዕስ ላይ ያቀረቡት የመጀመሪያው መልእክት የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ይመስላል። አስተያየት ከሰጧቸው መካከልም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያሉ ዘሮች እንዲመረቱ መንግሥት መፍቀድ እንደሌለበት የሚያሳስቡ፤ እንዲሁም እንዲህ ያለው አስተማሪና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መረጃ በማቅረባቸው ምስጋና የሚያቀርቡም ይገኙበታል።

አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት የንቦች ቁጥር ቀንሷል። እንደጀርመን ባሉ ሃገራት ደግሞ የንብ ዘር እየጠፋ ነው በሚል ልዩ ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው ነው። አቶ ዓለሜ አሁን ወደተፈጥሮ ለመመለስ እየታገለች ነው በሚሏት አሜሪካ ሰዎች የራሳቸውን የጓሮ አትክልት እንዲያበቅሉ የሚደረግ ማበረታቻ መኖሩም ያም እንደንብ ያሉ ፍጥረታት በተፈጥሮ ሂደት እንዲገኙ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታስቦ የሚደረግ መሆኑን እንዳስተዋሉ እንዳስተዋሉ ገልጸውልናል።

በተፈጥሮ የበቀሉ አትክሎች
ምስል imago stock&people

በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል ጂኤምኦ በመባል የሚታወቀውን በቴክኒዎሎጂ ዘረመሉ የተለወጠ ምርትን በተመለከተ እየሠሩ የሚገኑት ቀጣይ ቪዲዮ አሜሪካን ሀገር ኅብረተሰቡ ያለውን አጠቃቀም እና በተፈጥሮ መንገድ የበቀሉ ምግቦች የሚሸጡባቸው መደብሮችም እየተበራከቱ መሄዳቸውን እንደሚያሳይ ገልጸውልናል። አሜሪካውያን ከአስርት ዓመታት በፊት ሲያወዛግባቸው የነበረው ይህ ጉዳይ ዛሬ ፈር ይዞ ኅብረተሰቡ የመረጠውን ከገበያው ገዝቶ እንዲመገብ ምንነቱ በግልጽ እንደሚጻፍበት የገለጹት እኝህ የተፈጥሮ ተቆርቋሪ፤ ሌላው ሀገር ሞክሮ አይጠቅምም ብሎ የተወውን ወደኢትዮጵያ ማስገባት አይገባምም ባይ ናቸው።  እናንተስ ምን ትላላችሁ?  አስተያየታችሁ በማኅበራዊ መገናኛ ገጾቻችንን አካፍሉን። 

 ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ