1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የአፍሪቃዉያን ባህል ቀን

ሐሙስ፣ ጥር 19 2014

«ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት ብዙ ችግሮች አሉብን። ይሁንና የጋራ ራዕይ እንዲኖረን ብንጥር ጥሩ ነዉ።  የነበሩንን ሁሉን ነገሮች አጥፍተን ብሔርተኝነት ላይ ብቻ በማተኮር ነጋችንን ማጥፋት የለብንም። የሚያራርቁንን ነገሮች ገታ እያደረግን የጋራ ራዕይ መፍጠር አለብን። መጓተቱን ቀንስ አድርገን ካለንበት ቀፎ ወጣ ብለን መመልከት መቻል አለብን።»  

https://p.dw.com/p/46Aoi
Still Thee 77 Percent | A history book for Africans
ምስል DW

ኢትዮጵያዉያን ሥነ-ጽሑፋቸዉን ወደ ዓለም መድረክ ማምጣት አለባቸዉ


የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» ከጎርጎረሳዉያኑ 2019 ጀምሮ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት በገባ በ 24 ኛዉ ቀን የአፍሪቃ እና የአፍሪቃ ባህል ቀን ሲል ማክበር ጀምሮአል። ቀኑ በዓለም ዙርያ የሚገኙ አፍሪቃዉያን እና የአፍሪቃ ዝርያ ያላቸዉ ሕዝቦች ሁሉ ባህላቸዉ ቱፊታቸዉ  ብሎም እዉቀታቸዉ እንዲያብብ እንዲተጉ ለማሳሰብ ነዉ። በቅኝ አገዛዝ ዘመን በብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ባህሎችና ወጎችን ነቅሎ አውጥቶ የምዕራቡ ዓለም ባህል የበላይነት እንዲኖር መንገድ ከፍቷል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በተጨማሪም የባሪያ ንግድ በዘመኑ፤ አፍሪቃውያንን ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች አስገድዶ በመላክ ከእናት አህጉራቸዉ በማላቀቅ ትልቅ ጉዳት ማድረሱም ይጠቀሳል። አቶ ዳዊት ሳሙኤልም ስለአፍሪቃ ባህል ታሪክ ብሎም የአፍሪቃ ቀን ተብሎ ሲወሳ የሚያስቡት ይህንኑ እንደሆን ተናግረዋል።  
የአፍሪቃ ሥነ-ጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ቋንቋና፣ ሥነ- ጽሑፍ- ለሌሎች ባህላዊ ዓለም ብዙ አስተዋጾ ቢኖረውም፣ የአፍሪቃ ታሪክ አሁንም በዋናነት ከቅኝ ግዛትና ከባሪያ ንግድ ብሎም ከድህነት አንፃር ይታያል፤ በሚለዉ አስተያየት ላይ ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህ ትረካ ወይም አባባል የተበሳጩ አንዳንድ የአፍሪቃ አቀንቃኝ ምሁራን አፍሪቃ ለቀሪው ዓለም የምታበረክተውን አልያም እስካሁንም ያበረከተችዉን የሥነ-ጽሑፍ የባህል አስተዋፆ ለማወቅ ወደ አፍሪቃ ታሪክ በጥልቀት ምርምር ለማድረግ መወሰናቸዉ ይጠቀሳል። የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» የአፍሪቃ እና የአፍሪቃ ባህል ቀን የሚል ስያሜ የሰጠዉ ቀን ስለመኖሩ አላዉቅም ነበር ያለን ደራሲ እና ጋዜጠኛ ሰለሞን ሞገስ በበኩሉ፤ ይህን ቀን በመጠቀም አፍሪቃዉያን ታሪካቸዉን በዓለሙ መድረክ ማጉላት እንደሚችሉ ገልፆአል። 
እንደ ግብፅ፣ ኑቢያ እና የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጥንት የአፍሪቃ ሥልጣኔ ታሪክ መሆናቸዉን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ከዚሁ አካባቢ ብዙ ጥንታዊ ግኝቶችንም ይጠቅሳሉ። የጥንቷ ግብፅ ለፒራሚዶች ግንባታ ባደረገችው ውስብስብ ማህበራዊ ስርዓት ታዋቂ ነች። አንዳንድ አፍቃሪ አፍሪቃዉያን ተመራማሪዎች የጥንቷ ግብፅን የአፍሪቃ ታሪክ ዋና ይዘት አድርገው ሲያስቀምጡ ሌሎች የሰዉ ዘር መገኛ የሆነችዉን ኢትዮጵያን በዋንኝነት ይጠቅሳሉ። የሰዉ ልጆች ማኅበራዊ አኗኗር ማለትም የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርትን የቀሰሙት አቶ ዳዊት ሳሙኤል እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ እምቅ ሃብትዋን ገና አልተጠቀመችበትም። 
የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ባህሎች በዓለም አቀፉ መድረክ ከፊልም እስከ ከሙዚቃ እና እስከ ሥነ-ጽሁፉ ዓለም ድረስ ብሎም በደህንነት መረጃ አሰባሰብ ሳይቀር፤ ዋና አካል ሆኖ ትልቅ ሚና መጫወቱን ምሁራን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ አገር በቀል የበለጸገ ባህል በአፍሪቃ ብሎም በዓለም ደረጃ እንዲታይ መረሃ ግብር አዉጥቶ መስራት የኛ የዜጎች ፈንታ መሆኑን ደራሲና ጋዜጠኛ ሰለሞን ሞገስ ይናገራል። 

 African Roots + Shaka Zulu
Äthiopien Alem Getachew ist ein äthiopischer Maler und Autor
ምስል Privat

የእምቅ ጥሪ ሃብት ባለፀጋዋ አፍሪቃ በተለያዩ ባህልና ቋንቋ የተዋበችዉ አፍሪቃ በረሃብ ልጆችዋ በእርስ በርስ በጦርነት በስደት መታወቃቸዉ ግን ዝም ብሎ የመጣ ይሆን? ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ በሰፊዉ መልስ ሰጥቶአናል።

«ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት የራሳችን ብዙ ችግሮች አሉብን፤ ይሁንና የጋራ ራዕይ እንዲኖረን ብንጥር ጥሩ ነዉ።  የነበሩንን ሁሉን ነገሮች አጥፍተን ብሔርተኝነት ላይ ብቻ በማተኮር ነጋችንን እንዳናጠፋ። የሚያራርቁንን ነገሮች ገታ እያደረግን የጋራ ራዕይ መፍጠር አለብን። መጓተቱን ትንሽ ብንቀንስ እና ለምሳሌ ስለ እድገት ስለ አብሮነት፤ ነገ ስለምንደርስበት አላማ ፤ ለትዉልድ ስለምናስቀምጠዉ እሴት፤ ማሰብ ብንችል  ጥሩ ነዉ። ካለንበት ቀፎ ወጣ ብለን መመልከት መቻል አለብን።»  

በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 24 የዋለዉን የአፍሪቃ ባህል ቀንን አስመልክቶ ባሰናዳነዉን ዝግጅት ላይ ቃለ- ምልልስ የሰጡን አቶ ዳዊት ሳሙኤል እና ገጣሚ እና ጋዜጠኛ ሰለሞን ሞገስን በማመስገን ሙሉ ስርጭቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ