1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም፤ ኮሮና በርካቶችን ገደለ፤ስራ አጥም በዝቶአል

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2012

በጀርመን የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት እጅግ እየጨመረ መሆኑ ተመለከተ። ኮሮና ባስከተለዉ ቀዉስ የአዉሮጳ ሃገራት የሚወስዱዋቸዉ የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃዎች በየሃገራቱ የነበረዉን የዴሞክራሲ ቀጣይነት ስጋት ላይ የሚጥል ነዉ ሲሉ  13 የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ስጋታቸዉን ገለፁ። በዩናይትድ ስቴትስ በኮሮና የተያዘ ሰዉ ከ 200 ሺህ መብለጡ ተዘገበ።

https://p.dw.com/p/3aNjY
Coronavirus erschöpfter Mitarbeiter in Südkorea
ምስል picture-alliance/Yonhap

በጀርመን የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት እጅግ እየጨመረ መሆኑ ተመለከተ። በሃገሪቱ እስካሁን ከ 77 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ተኅዋሲ መያዛቸዉ በምርመራ ተረጋግጦአል ሲል  በሃገሪቱ የተላላፊ ተኅዋሲ ጥናት ቢሮ  ሮበርት ኮሆ ተቋም አስታወቀ። ተቋሙ እንደገለፀዉ በ 24 ሰዓታት ዉስጥ የሟቾች እና በተኅዋሲዉ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ በጀርመን አሁንም ተኅዋሲዉ እየተዛመተ መሆኑን  አመላካች ነዉ ሲል  አስጠንቅቆአል።  የጀርመኑ ሮበርት ኮህ ተቋም ዛሬ ከቀትር በፊት ይፋ ባደረገዉ መረጃ በጀርመን 77,980 ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል።  ይህ ቁጥር ከትናንት ረቡዕ ጋር ሲነፃፀር በ 6156 ጨምሮአል ብሎአል። በጀርመን የሟቾች ቁጥር 872 መድረሱንም ሮበርት ኮህ ተቋም አስታዉቋል። የዩናይትድ ስቴትሱ የተዘማች ተኅዋሲ አጥኝ ቢሮ ጆንስ ሆፕኪን ተቋም፤ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት በጀርመን ከ 78 ሺህ ሰዉ በላይ በተኅዋሲ ተይዞአል። 931 ሰዎች ደግሞ በኮሮና ሞተዋል ሲል ይፋ አድርጎአል። ተኅዋሲዉ በተለይ በባቫርያ፤ የራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በኖርዝ ራይን ዌስት ፋልያ እንዲሁም በባድን ቩተንበርግ እና ሃምቡርግ እጅግ መዛመቱን የአሜሪካኑ ተቋም አስታዉቋል።      

BdTD Obdachlose schlafen auf markierten Flächen Coronavirus Nevada USA
ምስል Reuters/S. Marcus

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኮሮና ባስከተለዉ ቀዉስ የአዉሮጳ ሃገራት የሚወስዱዋቸዉ የአስቸኳይ ጊዜ ርምጃዎች በየሃገራቱ የነበረዉን የዴሞክራሲ ቀጣይነት ስጋት ላይ የሚጥል ነዉ ሲሉ  13 የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ስጋታቸዉን ገለፁ። ሃገራቱ በጋራ በፈረሙበት መግለጫቸዉ  የኮሮና ቀዉስን በተመለከተ የሚወሰደዉ ርምጃ ተመጣጣኝ እና ዉስን ሊሆን ይገባል ፤ ከዚህ በተጨማሪ ርምጃዎቹ የዴሞክራሲ ርምጃዎችን እና የሕግ የበላይነትን ማክበራቸዉን በየጊዜዉ መገምገም ያስፈልጋል ብለዋል። የኮሮና ቀዉስን አስመልክቶ የሚወሰዱት ርምጃዎች ያሳስበናል ሲሉ መግለጫ ያወጡት  ጀርመን፣ ቤልጂግ፣ ዴንማርክ፣ ፊላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ አየርላንድ፣ ኢጣልያ ሊክሰምበርግ ፖርቱጋል ስፔን እና ስዊድን ናቸዉ።    

በሌላ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰዉ ቁጥር ከ 200 ሺህ መብለጡ ተዘገበ። የተኅዋሲ ጥናት ተቋም ጆንስ ሆፕኪንስ ዩንቨርስቲ ይፋ እንዳደረገዉ ዩናይትድ ስቴትስ በዓለማችን በኮሮና በርካታ ሕዝብ የተያዘባት ሃገር ሆናለች። እስካሁን 215 ሺህ  ሰዉ  በኮሮና ተኅዋሲ ተይዞአል። ዛሬ ቀትር ላይ ይፋ እንደሆነዉ በዩናትድ ስቴትስ እስካሁን 5112 ሰዎች ኮሮና ባስከተለዉ ሕመም ሞተዋል።  የሃገሪቱ መንግሥት 240 ሺህ ሰዉ በኮሮና ተኅዋሲ ምክንያት ሊሞት ይችላል ሲል ስጋቱን ገልፆአል። የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትና የሚያስከትለዉ አደጋ በተለይ በመጭዎቹ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ ሳይሆን እንደማይቀር ተነግሮአል። 
በኢጣልያ በኮሮና የሟቾች ቁጥር ከ 13 ሺህ በልጦአል።  በስፔን ትናንት በኮሮና ተኅዋሲ የሞተዉ ሰዉ ቁጥር 950 መድረሱኑ ተዘግቦአል።በስፔን የሟቾች ቁጥር ከ 10 ሺህ በላይ መድረሱ  ተዘግቦአል። በፈረንሳዊ የሟቾች ቁጥር   ከ4000 መብለጡ ዛሬ ተዘግቦአል። በኢራንም ባለፉት 24 ሰዓታት ዉስጥ በኮሮና ተኅዋሲ 124  ሰዉ መሞቱ 52922959ተገልፆአል ።ይህም በኢራን እስካሁን በኮሮና ተኅዋሲ 3160 ሰዎች መሞታቸዉ ተነግሮአል። ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፤ በስደተኛ ጣብያ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ስደተኞችን ከመጠለያ ጣብያ ማዉጣት ያስፈልጋል ሲል አሳስቦአል።   የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮሮና ቀዉስን ተከትሎ ትናንት የጀመረዉ የፈረንጆቹ አፕሪል ወር ለሰራተኞች ከክፍያ ጋር የረፍት ጊዜ ወር ሲሉ ዛሬ አዉጀዋል። እንደ ጆን ሆፕኪንስ ተቋም በሩስያ ከ 30 ሰዎች በላይ በኮሮና ሞተዋል ፤ ከ 3500 በላይ ሰዉች ደግሞ በኮሮና ተይዘዋል።  

 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ