1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር ማሳሰቢያ

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2015

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር መንግሥት በጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ እየፈጸመ ይገኛል ያለው እስርና እንግልት እንዲቆም ጠየቀ። በዞኑ አንድ የደቡብ ክልል ምክር አባልን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መታሠራቸውን ነዋሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4KC8F
Äthiopien Logo International Gurage Association

የጌራጌ ዞን ወቅታዊ ጉዳይ

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር መንግሥት በጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ እየፈጸመ ይገኛል ያለው እስርና እንግልት እንዲቆም ጠየቀ። በዞኑ አንድ የደቡብ ክልል ምክር አባልን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መታሠራቸውን ነዋሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦች ገልጸዋል። በዞኑ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ አካባቢው በጸጥታ ዕዝ ወይም ኮማንድ ፖስት እንዲመራ የወሰነው የክልሉ መንግሥት በበኩሉ « ኢ መደበኛ» ሲል የጠራቸው አካላት በክልል ጥያቄ ሽፋን ግጭት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል ወንጅሏል። 
አድማና እሥር በጉራጌ   

በደቡብ ክልል እየተነሳ የሚገኘው የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በተለይ እንደ ጉራጌ ባሉ ዞኖች ላለመረጋጋት ምንጭ እንደሆነ ይገኛል። የዞኑ ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳን በማካተት ሊመሠረት የታቀደው አዲስ ክልላዊ መንግሥት አካል እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ካደረገ ወዲህ ጉዳዩ የበርካቶችን ትኩረት እንደሳበ ነው። በተለይም ምክር ቤቱ ቀደም ሲል በክላስተር ላለመደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔ መንግሥት ዳግም ሊያስመክርበት ነው የሚሉ መረጃዎች በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መሠራጨታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ከሰሞኑ ዳግም እንደ አዲስ እንዲቀሰቀስ አድርጎታል። በተለይ ባለፈው ሳምንት በወልቂጤ ከተማ ይህን የሚቃወም በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መካሄዱ የደቡብ ክልል መንግሥትንና የክልልነት ጥያቄን የሚያቀነቅኑ አካላትን እያወዛገበ ይገኛል።   
የቀጠለው የጅምላ እሥር   
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን ተከትሎ በወጣቶች ላይ የጅምላ እስር እየተፈጸመ እንደሚገኝ የከተማው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በከተማው ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ  አሁን ድረስ የፀጥታ አባላት አድማውን በማስተባበር ይጠረጠራሉ ያሏቸውን እያሰሩ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተለይም በከተማው በተለምዶ አይሪሽ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙና አንዳንዶቹም ወደ ሐዋሳ መወሰዳቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል። ለእስር ከተዳረጉት መካከል የተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ አባልና በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሕዝብን በመወከል የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ይገኙበታል። የአቶ ታረቀኝ ጓደኛ አቶ በቀለ ሽኩር እና ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ መርሻ እንደሚሉት አቶ ታረቀኝ የደህንነት አባላት ነን በሚሉ ሰዎች የተያዙት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ዕለት ነው። አባላቱ እንደመጡ «ትፈለጋለህ» በሚል በያዙት ተሽከርካሪ ጭነው መውሰዳቸውን ለዶቼ ቬለ DW የገለጹት የአቶ ታረቀኝ ጓደኛና ባለቤታቸው «ሌላው ቀርቶ የምክር ቤት አባል መሆኑንና የሕግ ከለላ እንዳለው  መታወቂያውን ቢሳያቸውም ሊቀበሉት አልቻሉም። ወደየት እንደወሰዱት መረጃው ስለሌለን ላለፉት ሁለት ቀናት ሥጋት ላይ ወድቀን ነው የቆየነው። ዛሬ ጠዋት ግን ወደ ሀዋሳ እንደተወሰደ በሰዎች አስደውሎ ከነገረን ወዲህ ተረጋግተናል » ብለዋል።   
የመንግሥት ሥጋትና የአስቸኳይ አዋጁ ድንጋጌ ተቃውሞ እና እስር በወልቂጤ
የደቡብ ክልል መንግሥት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የተካሄደውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተከትሎ ዞኑ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ በኮማንድ ፖስት አንዲመራ ደንግጓል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አሁን ላይ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በመደበኛ አሠራር ለማስተዳደር ባለመቻሉ መሆኑን  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። አቶ አለማየሁ «ኢ መደበኛ» ሲሉ የጠሯቸው ቡድኖች የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ሽፋን በማድረግ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ በማለት ወቅሰዋል። 
እነኝህ ቡድኖች ለግጭት የሚጋብዙ ቅስቀሳዎችን በማሠራጨት፣ መንገድ በመዝጋት፣ የንግድ እና የመንግሥት እንቅስቃሴዎችን አያወኩ እንደሚገኙ የጠቀሱት ኃላፊው «ይህን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ መንግሥት በዝምታ አያልፍም። ስለዚህ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ዞኑ ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት በተዋቀረ ኮማንድ ፖስት እየተመራ ይገኛል። እስካሁን ንጹሐን ዜጎችን ጉዳት ላይ በማይጥል መልኩ  ፀጥታውን መቆጣጠር ተችሏል። በድርጊቱ በቀጥታ ተሳታፊ የነበሩ 70 የሚደርሱ ሰዎችን ይዘን እያጣራን እንገኛለን » ብለዋል።
 የተቃውሞ ድምጾች 
 በጉራጌ ዞን በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መካሄዱን ተከትሎ እየተፈጸመ ይገኛል የተባለውን እስር የክልል አደረጃጀት ጥያቄን የሚያራምዱ ሊህቂንና የተለያዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። በተለይም መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር ትናንት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ መንግሥት በዞኑ እየተፈጸመ ይገኛል ያለውን እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል። ድርጊቱ የጉራጌ  ህዝብ በወከላቸው የዞን ምክር ቤት አባላት አማካኝነት ባለፈው ነሐሴ ወር ያሳለፈውን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ለማፈን የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ነጃ ሐሊል ለዶቼ ቬለ DW ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት መንግሥት የክልል አደረጃጀትን በመደገፍ ከሕዝቡ ጎን ቆመዋል ያላቸውን አመራሮች እያሰረ ይገኛል፤ አንዳንዶቹንም ከሹመት አሰናብቷል ያሉት አቶ ነጃ «በተለይ  ከኅዳር 9 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ የክልልነት ጥያቄን አስመልከቶ የተጠራውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ሌላ ቀለም በመስጠት በርካቶችን ያለአግባብ አስሮ ይገኛል። በመሆኑም የፌዴራል የፍትህና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል እንዲቆም የበኩላቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን»› ብለዋል።    
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ

Äthiopien Gurage Streik
ምስል privat
Äthiopien Gurage Streik
ምስል privat