1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታ ለኮሮና ክትባት ፍለጋ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2012

ለኮሮና ቫይረስ ክትባትና ፈዋሽ መድኃኒት ፍለጋ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ግን ኮሮና ከ69 ሺህ በላይ ሰዎች የገደለባት እና ከአንድ ሚሊዮን 181 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና የተያዙባት ዩናይትድ ስቴትስ አልተካፈለችም።ለምን በጉባኤው ላይ እንዳልተገኘችም አላሳወቀችም።

https://p.dw.com/p/3bopk
Still DW-Interview EU-Kommissionspräsidentin von der Leyen
ምስል DW

ዓለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታ ለኮሮና ክትባት ፍለጋ

«አሳክተነዋል!ይህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወሳኝ ወቅት ነው።ከተለመደው ውጭ ተራርቀን በምንገኝበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአንድ ላይ ተቀራርቦ መቆሙን አሳይቷል።በጥቂት ሰዓታት ውስጥም በጋራ 7.4 ቢሊዮን ዩሮ ለክትባት፣ለምርመራ እና ለመድኃኒት ቃል ተገብቷል። ይህ ሁሉ ገንዘብ እስከዛሬ ተደርጎ ለማያውቀው ዓለም ዓቀፍ ትብብር በመነሻነት ያግዛል።»
የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላፎን ዴር ላየን ትናንት ከሰዓት በኋላ ለ3 ሰዓታት በመሩት የለጋሽ ሃገራት የቪድዮ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ስለ ውጤቱ የተናገሩት ነበር።ፎን ዴር ላየን እንዳሉት የጉባኤው ውጤት ኮሮና ከመቼውም በበለጠ ዓለምን አንድ የማድረጉ ምልክት ተደርጎ ነው የተወሰደው።መንግሥታት በሽታውን ለመከላከል በጋራ መቆማቸውን ባሳዩበት በዚህ መርሃ ግብር ላይ ታዋቂ ሰዎችም የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።ከመካከላቸው ታዋቂዋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማዶና ለዓለም አቀፉ ጥረት አንድ ሚሊዮን ዶር ለግሳለች። እስከዛሬ እኩለ ቀን ድረስ በዓለማችን በኮቪድ 19 የተያዘው ህዝብ ቁጥር 3,607,469 ደርሷል።በሽታው የገደለው ደግሞ ከ252 ሺህ በልጧል።ከነዚህም ከ140 ሺ በላይ የሞቱት በአውሮጳ ነው ። ፎን ዴር ላየን ለጉባኤው እንዳሳሰቡት ኮሮናን ለማሸነፍ የተሻለው አማራጭ ክትባት መፈለግ ነው።ትናንት ቃል የተገባው ገንዘብም በዋነኝነት ለኮሮና ተህዋሲ ክትባት እና መድኃኒት ፍለጋ የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት የሚውል ነው።ገንዘቡም ለዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች እና የምርምር ማዕከላት ይሰጣል ነው የተባለው።ዓላማውም በተቻለ ፍጥነት ለኮሮና ክትባትና ፈዋሽ መድኃኒት ማግኘት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ከዓለም ዙሪያ የማሰባሰብ እና ክትባቱንም ሆነ መድኃኒቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ማዳረስ ነው።ለዚሁ ዓላማም 40 ሀገራት እንዲሁም  የተመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።ከግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ መካከል በዓለም ዙሪያ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ማቃለያ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ይገኝበታል። 
የድርጅቱ ተባባሪ ሊቀመንበር ሜሊንዳ ጌትስ ለጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት ወረርሽኙን በሁሉም ስፍራ እንጂ በተወሰነ አገር ወይም አህጉር ደረጃ ለመከላከል መሞከር ዋጋ የለውም ብለዋል።ስርጭቱን ለማስቆም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ክትባት ማግኘት መቻሉ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት።
«ኮቪድ 19፣ ተህዋሲዎች ለድንበር ወይም ለጉምሩክ ደንቦች እንደማይታዘዙ አስታውሶናል።የየትኛውም ሃገር ዜጋ ብትሆንም ደንታ አይሰጣቸውም።ኮቪድ 19 አንድ ቦታ ላይ ከተከሰተ በየትኛውም ስፍራ ይዛመታል።ስለዚህ ወረርሽኙን ለማስቆም ምንድንነው የሚያስፈልገው?አዎ ክትባት ብዙ ገንዘብ ለሰጠው ወይም ለባለጸጋዎቹ ሃገራት ህዝቦች ከማቅረብም በላይ ሊሆን ይገባል።የትም ቦታ ያሉ ሰዎች የመከላከያ ክትባት ካላገኙ ወረርሽኙ አይቆሙም።»
ይህ የሜሊንዳ ጌትስ መልዕክት የብዙዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎችም አቋም ነበር።ለክትባት ፍለጋው ጥረት 500 ሚሊዮን ዩሮ ለማዋጣት ቃል የገባችው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ የትናንቱ የለጋሽ ሃገራት ጉባኤ ዓላማ ክትባቱ ሲገኝ ለሁሉም ማዳረስ ሊሆን ይገባል ብለዋል። 
«በዚህ ጥረት ሁላችንም በጋራ መወሰን ያለብን ጉዳይ አለ።ክትባቱ  ጥቅም ላይ ሲውል የዓለም የጋራ ንብረት ይሆናል ።ማለትም የአንድ ወገን ብቻ አይሆንም ይልቁንም የሁሉም ነው የሚሆነው።እርግጥ ነው የፈለሰፉት ተገቢውን ክፍያ ያገኛሉ።ሆኖም እኛ በምንመርጠው ድርጅት አማካይነት ለዓለም ህዝብ እንዲደርስ ይደረጋል።»
ማክሮ እንዳሉት አሁን ሩጫው ከጊዜ ጋር ነው።የሰዎች ሕይወት ለማዳንም ስራው ሊፋጠን ይገባል    
በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ሃገራት ክትባቶችን የመስራት ሙከራ እየተደረገ ነው። እንደውም የኮሮና ክትባት ምርምር የሚያካሂዱ የአሜሪካንና የቻይና ድርጅቶች በሰዎች ላይ መደረግ ያለበት ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይጠናቀቅ ክትባት ለማምረት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋልም እየተባለ ነው። እናም እነዚህን የተናጠል ጥረቶች ወደ ፉክክር ከመቀየር ይልቅ በትብብር መንፈስ እንዲካሄዱ በለጋሽ ሃገራቱ ጉባኤ ላይ ጥሪ ቀርቧል።ከኮቪድ 19 አገግመው በቅርቡ ሥራ የጀመሩት የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለጉባኤተኞቹ በሽታውን የመከላከሉ ጥረት በተናጠል ሳይሆን በጋራ ሊካሄድ እንደሚገባ ነው አሳስበዋል። 
«እውነታው ማናችንም ብቻችን የትም እንደማንደርስ ነው። ይህን ትግል ለማሸነፍ ለህዝባችን የማይሸነቆር ከለላ ለመስራት  በአንድ ላይ መስራት አለብን።ይህን ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ክትባት በመስራት እና በስፋት በማምረት ነው።ባለሞያዎቻችን አንድ ላይ አሰባስበን ልምድ እንዲለዋወጡ ባደረግን ቁጥር ሳይንቲስቶቻችን ክትባቱን የማግኘት እድላቸው ይፋጠናል።»
ሆኖም ጆንሰን ክትባት ለመስራት የሚደረገውን እሽቅድምድ ግን ፉክክር አላሉትም።ይልቁንም አሰፈላጊ ጥረት እንጂ።
«በበሽታው ላይ ድል ለመቀዳጀት የሚስችል ክትባት ለመስራት የሚደረገው ሩጫ በሃገሮች መካከል የሚካሄድ ፉክክር አይደለም። ይልቁንም በህይወት ዘመናችን የምንጋራው እጅግ አንገብጋቢ ጥረት ነው።የሰው ልጅ በተህዋሲስ ላይ በጋራ መነሳቱን የሚያሳይ ነው።በዚህ ውስጥ አንድ ላይ ነን። አንድ ላይም እናሸንፋለን።» 
በቪድዮ በተካሄደው ጉባኤው ላይ የተካፈሉት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጀርመን ለዚህ በጎ ዓላማ የ525 ሚሊዮን ዩሮ ቀጥተኛ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል ገበተዋል።ሃገሪቱ ከዚህ ቀደም ለዓለም ጤና ጥበቃ የምትዋጣውን ገንዘብ እንደምትቀጥልም በዚሁ አጋጣሚ አስታውቀዋል።ሜርክል በሽታውን ለመዋጋት ከዚህም በላይ ጥረቶች ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
«ይህ በዚህ ወቅት ላይ አስፈላጊ ምልክት ነው።ምንም እንኳን እኔ የምፈልገውን ያህል በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ሁሌም አንድ ላይ ባንሰራም ጊዜው የተስፋ ጊዜ ነው።በዚህ የተሳተፉትን ሁሉ አመሰግናለሁ።ጀርመን የበኩልዋን ድርሻ ትወጣለች።የሚሆነው ሁሉ እንከታተላለን።ይህ የመጨረሻው ጉባኤ አይሆንም።ተጨማሪ ጥረቶች ማድረግም ያስፈልጋል።በጣም አመሰግናለሁ።»
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬስ ለስብሰባው ተካፋዮች እንደተናገሩት ግን አሁን ቃል የተገባው ገንዘብ ብቻውን የተሳበተለትን ዓላማ ያሳካል ብለው አያስቡም። ጉተሬስ ክትባቱን ለሁሉንም በያለበት መዳረስ እንዲችል አሁን ከታሰበው 5 እጥፍ የሚሆን ገንዘብ ሳያስፈልግ እንደማይቀር አስገንዝበዋል።
«በመጀመሪያ ለታለመው 7.5 ቢሊዮን ዩሮ ዛሬ ቃል የተገቡትን ብዙ መዋጮዎች በደስታ ተቀብያለሁ።እርዳታው በፍጥነት ለሚያስፈልገው የበሽታው መከላከያ እንደ መነሻ ገንዘብ ነው የሚቆጥረው።ሆኖም ለሁሉም በያለበት እንዲደርስ አሁን ቃል ከተገባው 5 እጥፍ ያህል ገንዘብ ሳያስፈልገን አይቀርም።የጋራ ራዕይ አለን።እስቲ አሁን በሁሉም ቦታ ለሰዎች ቅድሚያ እንስጥ።»
የዓለም የጤና ድርጅት በምህጻሩ WHO ዓለም አቀፍ ትብብር በእጅጉ አድንቋል።የድርጅቱ ሃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም አቀፉ ትብብር ውጤቱ ሌላውንም የሚያነቃቃ ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ይህን የለጋሾች ጉባኤ ካዘጋጁት መካከል የአውሮጳ ህብረት አባል ያልሆኑት ብሪታንያ ኖርዌይ እና ሳዑዲ አረብያም ይገኑበታል።በቪድዮ ጉባኤው የጃፓን የካናዳ የደቡብ አፍሪቃ እና የሌሎችም በርካታ ሃገራት መሪዎች ተካፍለዋል።ቻይናም በጉባኤው በአውሮጳ ህብረት አምባሳደሯ ተወክላለች። ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የለጋሽ ሃገራት ጉባኤዎች አስተባባሪ እና ዋናኛ ተዋናይ ዩናይትድ ስቴትስ ነበረች።ትናንት ለኮሮና ቫይረስ ክትባትና ፈዋሽ መድኃኒት ፍለጋ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ግን ኮሮና ከ69 ሺህ በላይ ሰዎች የገደለባት እና ከ አንድ ሚሊዮን 181 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና የተያዙባት ዩናይትድ ስቴትስ አልተካፈለችም።ዋሽንግተን ለምን በጉባኤው እንዳልተካፈለች አላሳወቀችም።ሆኖም አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካን ባለሥልጣን የአውሮጳ ህብረት ኮሮናን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመዋጋት የሚያደርገውን ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረት እንደግፋለን ማለታቸው ተዘግቧል።የዋሽንግተን በጉባኤው ላይ አለመገኘት ያሳዘናቸው እንዳሉ ሁሉ ወደፊት ትብብሩን መቀላቀሏ አይቀርም ሲሉ ተስፋ ያደረጉም አሉ።አሜሪካን ወደፊት የዚህ ጥረት አካል መሆንዋ አይቀርም ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ተስፋቸውን ገልጸዋል። የአውሮጳ ህብረት አስቀድሞ ባቀደው መሠረት 7.5 ቢሊዮን ዩሮ ቃል ቢገባለት ፣4 ቢሊዮኑን ክትባት ለመስራት ፣2 ቢሊዮኑን ለፈዋሽ መድኃኒት ፍለጋ የቀረውን 1.4 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ ለበሽታው ምርመራ ለማዋል ነው ያሰበው።

Petersberger Klimadialog
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler
Coronavirus Impfstoffforschung Geberkonferenz Frankreich Präsident Macron
ምስል picture-alliance/dpa/AP/Reuters/G. Fuentes
Petersberger Klimadialog
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ