1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2019 ሁለተኛ መንፈቅ ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዉኖች

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2012

ሞዲ የደልሒ መንበራቸዉ ድድር ምድር መቆንጠጡን  እንዳረጋገጡ፣ ጃሙና ካሽሚር ለሚባለዉ ግዛት በሕገ-መንግስት የተደነገገዉን የልዩ አስተዳደርነት መብት ገፈፉ።ነሐሴ 5። የግዛቲቱ ሕዝብ ባደባባይ ሲቃወም ጠቅላይ ሚንስትሩ በጦር ኃይል  ያስቀጠቅጡት ያዙ። ስልክ፤ ኢንተርኔት፣ የገንዘብ ዝዉዉርና የባንክ አገልግሎትን ሳይቀር ዘጉ።

https://p.dw.com/p/3VW3E
USA | Demonstration in Washington | Impeachment
ምስል Getty Images/MoveOn.org/L. French

የ2019 ሁለተኛ መንፈቅ ዓበይት ክንዉኖች


2019 ሊጠናቀቅ ዕለት ቀረዉ።በዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ ከአዉሮጳ በስተቀር ባለዉ ዓለም የተከናወኑ ዓበይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ባለፈዉ ሳምንት ቃኝተን ለሁለተኛዉ መፈንቅ ቅኝት ለዛሬ ቀጥረን ነበር። እነሆ መጣን። 

ሰኞ፣ ለእስከ ዛሬ ሰኞ ቀጥረን የተለያየነዉ  ጥንት የአስከሬን ማስጫ መሆኑን ለመቀኘት «---ምንዉ አይታረስ----» የተጠየቀለት ሞጣ ቤንዚን እየዘነበበት መሳጂድ፣ በእሳት የመታረሳቸዉ ዘግናኝ ሐቅ አብዛኛ ኢትዮጵያዉያንን እንዳስደገጠ፣ በተለይ ሙስሊሞችን እንዳስቆጣ ነበር።
የኢትዮጵያ መሪ የ2019ኝን ታላቅ የሰላም ሽልማት ኖቤልን የመቀበላቸዉ ልዕልና አስደስቶ ሳያበቃ፣ የኃይማኖት ጥላቻ ፣የዕኩያን ቅርሻት፣ የደናቁርት ግሳት ሞጣን ሲያጋይ የዝቅጠቷ ቅርናት ድፍን ሐገሪቱን ቆነሰ። የኖቤሉ ተስፋም በርግጥ ረከሰ።
ዓመቱም ከፍፃሜዉ ደረሰ። በጥፋት፣ ለጥፋት ኖረዉ ጥፋት ያወጁት ጥፉዎች ባንዲት ትንሽ ከተማ፣ ባንድ ቀን  4 መሳጂዶችን፣ 111 የሙስሊሞች መደብሮችን፤ ሆቴሎችን፣ምግብ ቤቶችንና ሕንጻዎችን ሲያጋዩ፣ እርስ በርስ መገዳደሉ ሰኔ ላይ ያማረባቸዉ የአማራ ገዢዎች « ኃይ» ማለት ያልፈለጉበት ምክንያት ግን ዘንድሮ አይደለም ከርሞ፣ ምናልባትም አሰላሹ ዓመትም እየመጣ ይሔዳል እንጂ  ማጠያያቁ አይቆምም። ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ቁጣ፤ ድንጋጤ፣ ሥጋት ቁጭታቸዉን በአደባባዩ ሲገልጡ ዘመኑን በጎርጎሪያኑ ቀመር የሚያሰላዉ ዓለም ክርስቶስ የተወለደበትን 2019ኛ ዓመት አከበረ።ገና።
 «ዉድ ወንድሞቼና እሕቶቼ።መልካም ገና።የሰዎች ልቡና በጨለማ ተሞልቷል።ይሁንና የክርስቶስ ብርሐን አሁንም ትልቅ ነዉ።በኤኮኖሚ፣በጂኦ ፖለቲካና በተፈጥሮ ሐብት ግጭት ዉስጥ ጨለማ ነግሷል።ይሁንና የክርስቶስ ብርሐን አሁንም ትልቅ ነዉ።»
በመልከዓ ምድር ግጭት፣ግድያ ዉዝግብ ለዝንተ ዓለም የተመሰቃቀለችዉ የክርስቶስ የልደት ሥፍራ ቤተልሔምም እንደገና ገናን አከበረች።
ለሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ የገና ስጦታዉ  ግድያ ነበር። የቡርኪናፋሶ መንግሥት አሸባሪ ያላቸዉ ታጣቂዎች አርቢዳ በተባለች ከተማና በአንድ የጦር  ሠፈር ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች ገደሉ።የመንግሥት ጦር 80 አማፂያን መግደሉን አስታዉቋል።
ፈረንሳይ የምታስተባብር፣ ፈረንሳይ በጦር ኃይል የምትደግፋቸዉ የቀድሞዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢዎች የቡርኪናፋሶ፣የማሊ፣የኒዠርና የቻድ መንግሥታት «አሸባሪ» የሚሏቸዉን አማፂያን ለማጥፋት  ጦራቸዉን ካዘመቱ ከ2015 ወዲሕ ቡርኪና ፋሶ ብቻ ከ700 በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሎባታል።
ከግማሽ ሚሊዮን  በላይ ሕዝብ ተፈናቅሎባታል።
ተወዳጁ የቡርኪናፋሶ የቀድሞ መሪ ተማስ ሳንካራ እንደነገረን ቡርኪና ፋሶ- የሐቀኞችና የታማኞች ሐገር ማለት ነዉ። ሐቀኞቹ ከዕልቂት የሚድኑበት ሐቅ ዉሉ እንደጠፋ ዘንድሮ አምና ሊሆን አንድ ማዓለት ወሌት ብቻ ቀረዉ። ሳንካራን ያስገደለዉ ማንነበር?
የዓመቱ ማብቂያ ለሞቃዲሾም ከ2006 ማብቂያ ጀምሮ እንደኖረችበት የሽብር ግድያ ጊዜ ነበር። የአሸባብ አባላት ናቸዉ የተባሉ ሰዎች በጭነት መኪና የከመሩትን ቦምብ መሐል መቃዲሾ አፈነዱት። ቅዳሜ ታሕሳስ 28። አንድ መቶ ሰዉ ተገደለ።
ወደ ኋላ መለስ ወደ። ሰሜን አፍሪቃ ቅና እንበል። ሊቢያ። የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር የሚያዙት ጦር ታጁራ የሚገኘዉን የስደተኞች ሰፈር በአዉሮፕላን ደበደበ።ኃምሌ 3።53 ስደተኞች ተገደሉ። 130 ቆሰሉ።
ሚያዚያ ላይ ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ያለዉን የትሪፖሊ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ የፎከሩት ማርሻል ሐፍጣር በ8ኛ ወሩ ታሕሳስ ትሪፖሊን ለመቆጣጠር እንደገና ዛቱ።ታሕሳስ 12።
« ዛሬ ትሪፖሊን የቀፈደዳትን ሰንሰለት ለመበጠስ  ወሳኝ ዉጊያ ለመክፈት መወሰናችንን አስታዉቃለሁ። ጥቃቱ፣ ለትሪፖሊ ሕዝብ ደስታን ለማጎናፀፍ፣ ከተማይቱን በታሪክ እንደምትታወቀዉ የስልጣኔ ርዕሠ-ከተማ ለማድረግ ያለመ ነዉ።»
ኸሊፋ ሐፍጣር። በ1980ዎቹ ቻድ ሲዘምቱ ጠላቶቻቸዉን ግድይ ሊጥሉ ከያኔ አዛዣቸዉ ከኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ፊት ፎክረዉ ነበር።ግን ተማረኩ። ከምርኮ ሲለቀቁ አለቃቸዉን ከድተዉ  ቃዛፊን ለማስወገድ ለአሜሪካኖች ቃል ገብተዉ ዉጊያ ገጠሙ።ግን ተሸነፉ።ዘንድሮ ሚያዚያ ፎከሩ። አልቻሉም። ታሕሳስም ደገሙት። እስካሁን አልቻሉም።
ይልቅዬ የሐፍጣር ፉከራ ዛቻ ጥሩ ሰበብ የሆናት ቱርክ የትሪፖሊን መንግስት የሚደግፍ ጦር ለማዝመት ወሰነች። ሊቢያም፣  ግብፅ፣ሳዑዲ አረቢያ፣ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና ግሪክ፣ ሩሲያና ፈረንሳይ ከሐፍጣር ጎን፣ ቱርክ፣ ቀጠርና ኢጣሊያ ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ካለዉ የትሪፖሊ መንግስት ጎን ቆመዉ በተልዕኮ የሚዋጉባት የዕልቂት ምድር እንደሆነች ስምተኛ ዓመቷን ሸኘች።
አክራሪዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ በ2017 የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ስልጣን ከያዙ ወዲሕ የተጃገኑት የአሜሪካ ነጭ ዘረኞች እንዳምና ሐቻምናዉ ሁሉ ከዘራቸዉ ዘር የማይጋራዉን እንደረሸኑ  ዘንድሮም አምና ሊሆን ነዉ።
ኤል ፓሶ፤ ኃምሌ 3። የ21 ዓመቱ ወጣት ፓትሪክ ክሩሲዮስ ጠመጃዉን አቀባብሎ ዎልማርት ከተባለዉ የገበያ አዳራሽ ገባ። ሕፃን ከሽማግሌ፣ ሴት ከወንድ ሳይለይ ጥይቱን ያርከፈክፈዉ ገባ።22 ገደለ።24 አቆሰለ።
«አንድ ወጣት ይዘናል። በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ነጭ ወንድ መሆኑን አረጋግጣለሁ።»
ፖሊስ።አብዛኞቹ ሟች ቁስለኞች  የሜክሲኮ ዝርያ ያለቸዉ ናቸዉ። 
ከ13 ሰዓታት በኃላ። ዳይተን፣ ኦሐዮ።ሌላ ዘረኛ። ተጨማሪ ግድያ። የ24 ዓመቱ ወጣት ኮርነር ስቴፋን ቤተስ ለዘር ጥላቻ ዛሩ 10 አሜሪካዉያንን ጭዳ አደረገ። አንዷ ታናሽ እሕቱ ነበረች። 27 አቆሰለ።
ሕንድ ዉስጥ ሚያዚያ ላይ በተደረገዉ ምርጫ ባሕራተን ጄናታን የተባለዉ ሒንዱ ብሔረተኛ ፓርቲ ከፍተኛ ድል ከተቀዳጀ ወዲሕ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ናረንድራ ሞዲ «የእስያ ትራምፕ» ይባሉ ይዘዋል።
ሞዲ የደልሒ መንበራቸዉ ድድር ምድር መቆንጠጡን  እንዳረጋገጡ፣ ጃሙና ካሽሚር ለሚባለዉ ግዛት በሕገ-መንግስት የተደነገገዉን የልዩ አስተዳደርነት መብት ገፈፉ። ነሐሴ 5።
የግዛቲቱ ሕዝብ ባደባባይ ሲቃወም ጠቅላይ ሚንስትሩ በጦር ኃይል  ያስቀጠቅጡት ያዙ። ስልክ፤ ኢንተርኔት፣ የገንዘብ ዝዉዉርና የባንክ አገልግሎትን ሳይቀር ዘጉ።
የሞዲ እርምጃ በካሽሚር ሰበብ ከሕንድ ጋር በጠብ የምትፈላለገዉ ፓኪስታንን  ጎትቶ አካባቢዉን ከሌላ ዉጊያ ይዶላል ተብሎ ሲፈራ፣ ሸማግሌዉ ፖለቲከኛ ሕዝባቸዉን የሚያንጫጫ ሌላ ደንብ አስፀደቁ። የዜግነት  ሕግ።
ሕጉ የቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ ቁጣ፣ የትልቂቱን ሐገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያሽመደመደ፤ሐብት ንብረቷን እያወደመ፣ ምጣኔ ሐብቷን እያንገራገጨዉ ነዉ።
ፖሊስ እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ በወሰደዉ እርምጃ በትንሽ ግምት 32 ሰልፍኞችን ገድሏል።የመንግስትን እርምጃ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አዉግዘዉታል። ሙስሊሞችን ያገላል የተባለዉን ሕግ የሕንድ ሙሕራን ማሕበር፣ የሴቶች ማሕበር፣  የመብት ተሟጋች ድርጅቶች  አዉግዘዉታል።
ከዉጪ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ማሌዢያ፣ ፓኪስታን እና ባንግላዴሽ በይፋ ተቃዉመዉታል። ናረንድራ ሞዲ ግን  «ፍንክች አባ ሒንዱ ልጅ» እንዳሉ 2019፤ በ2020 ሊተካ ነዉ።
ወደ ድሮ ላፍታ እንመለስ።ሚዚያ 18 1980።አፍሪቃ አዲስ ነፃ ሐገር አስመረቀች።ዚምባቡዌ። አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ሾመች። «እኔ ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ፣ ለዚምባቡዌ በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቃል አገባለሁ።»
በሰባተኛዉ ዓመት ፕሬዝደንት ሆኑ።በ37ኛዉ ዓመት ከስልጣን ወረዱ።በ39ኛዉ ዓመት ሞቱ። መስከረም 6። የአፍሪቃ መሪዎች የመጨረሻዉን የፀረ-ቅኝ ገዢ ተዋጊን ሸኙ።መስከረም 28።ሮበረት ጋብሬኤል ሙጋቤ። 95 ዓመታቸዉ ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስና  ዓለምን አስከትላ ከመስከረም 2001 ጀምሮ አፍቃኒስታንን በቦምብ፣ ሚሳየል፣ የቀጠቀጠችበት ክርኗ ድል አልቦ ሲዝል ከዋና ጠላቷ ታሊባን ጋር የጀመረችዉ ድርድር እንዲቆም ፕሬዝደንት ትራምፕ አዘዙ። ምክንያት፤ ታሊባን ካቡል ዉስጥ በጣለዉ ቦምብ አንድ የአሜሪካ ወታደር መግደላቸዉ ነበር።
በ11ኛዉ ቀን የአሜሪካ ጦር ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ናንጋርሐር ግዛት በተኮሰችዉ ሚሳዬል 30 ለዉዝ አምራች ገበሬዎችን ገደለች።40 አቆሰለች።
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር  ኒምሮዝ እና ፋራሕ በተባሉ የአፍቃኒስታን አዉራጃዎች የገደላቸዉን ሰላማዊ ሰዎች አሟሟት ሲመረምር የነበረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪ ቡድን ጥቅምት 9ኝ ባወጣዉ ዘገባ የአሜሪካ ጦርን ጥቃት «ሕገ ወጥ » በማለት አወገዘ።
አወገዘ። በቃ። የአሜሪካ የጦር ጄቶች በሁለቱ አዉራጃዎች ባንድ ጊዜ የገደሏቸዉ ሰላማዊ ሰዎች 39 ነበሩ።
ብቻ አፍቃኒስታን መስከረም 28 ላይ ምርጫ አደረገች ተባለ። ዉጤቱን ለማወቅ ግን መራጭ-ተፎካካሪዎች እስከ ታሕሳስ ማብቂያ መጠበቅ ግድ ነበረባቸዉ። ታሕሳስ 23። ፕሬዝደንት አሽረፍ ጋኒ አሸነፉ ተባለ። 
አፍቃኒስታን፥ ዉጊያ- ድርድር፣ ጦርነት-የሰላማዊ ሰዎች እልቂት፣ ማጣራት- ትርጉም የለሽ ዉግዘት፣ ምርጫ-ሶስት ወር የሚዘገይ-ዉጤትን ለዓለም እስተዋዉቃ 2019ኝ ልትሰናበት ነዉ።
መስከረም 14። አብቃይቅ-ኹራይስ የሚገኙ ሁለት የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያና ማከማቻ ማዕከላት ጋዩ። ጥቃቱ የሳዑዲ አረቢያን የፀጥታ አጠባባቅ ዝርክርክነት፣ የአሜሪካ አማካሪዎቻቸዉን ደንታ ቢስነት ያጋለጠ፣ የዓለም የነዳጅ ገበያን ያወረገረገ ነዉ።
የየመን ሁቲ አማፂያን ለጥቃቱ ሐላፊነቱን ወስደዋል።የሪያድና የዋሽግተን መሪዎች ግን  ኢራንን መወንጀሉን ነዉ የወደዱት።በጥቃቱ ሰበብ ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ ወታደሮች፣  ጦር መሳሪያና አማካሪ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንድታሰፍር የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዘዙ። መስከረም 21።
የቱጃር አረቦችን ሰላምና ደሕንንነት የአሜሪካ ጦር ይጠብቃል። የአሜሪካ ጦር መሳሪያን የታጠቀዉ የአረብ ጦር የየመን አረቦችን ይገድላል።የአረብ ገንዘብ ለአሜሪካ ጦር፣ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ፣ የመንን፣ ሊቢያን፣ ሶሪያን ሊባኖስን ለማፍረስ ይንዠቀዠቃል።
ለዶናልድ ትራምፕ ጠንካራ ሥልጣን ጠንካራዉ ስጋት ግን ቴሕራን፣ሞስኮ፣ቤጂንግ ሌላም አልነበረም። ዋሽግተን እንጂ። ትራምፕ ስልጣናቸዉን ተመክተዉ ተቀናቃኛቸዉን ለማጥፋት ከዩክሬን መንግስት ጋር ተመሳጥረዋል  ብለዉ የጠረጠሯቸዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የሕገ-መምያ ምክር ቤት አባላት ጥርጣሬዉ እንዲመረመር ወሰኑ። መስከረም 24።
በአራተኛ ወሩ  ምክር ቤቱ በሁለት አንቀፆች ትራምፕን ጥፋተኛ ብሎ ወሰነ። ታሕሳስ 18።
                                     
«አንቀፅ አንድ ፀድቋል። ጥያቄዉ የአንቀፅ 2 መፅደቅ ነዉ። የምትደግፉ «አይ» በሉ፣ የምትቃወሙ፣ «ኔ» በሉ።---- አይ ያሉ አሸንፈዋል፣ አይ ያሉ አግኝተዋል።---»
የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፖሎሲ።
ትራምፕ ዉሳኔዉን አጣጥለዉ ነቅፈዉታል። የሕግ-መወሰኛዉ ምክር ቤት (ሴኔት፣ ፕሬዝደንቱ ሥልጣን መልቀቅ አለመልቀቃቸዉ ሳይወስን አሮጌዉ ዓመት-አሮጌዉን ፕሬዝደንት ለአዲሱ ዓመት ሊያስረክብ ነዉ።
ጥቅምት፣ አሜሪካ ኢራቅን ከወረረች ከ2003 ጀምሮ ግድያ፣ሽብር፣ አፈና ያልተለያቸዉ የኢራቅ ትላልቅ ከተሞች በተቃዉሞ ሰልፍ፣ ጩኸት፣ ግድያ፣ ይተረማመሱ ገቡ።ፖሊስ ባንድ ቀን ብቻ 91 ሰዉ ገደለ። ጥቅምት 5። ያቆሰለ፣ ያሰረዉን ሰዉ የቆጠረዉ የለም።
ሕዳር 30። ጠቅላይ ሚንስትር አድል አብዱል መሕዲ ሥልጣን ለቀቁ። ታሕሳስ 26 ፕሬዝደንት በርሐም ሳሌሕ ስልጣን ለመልቀቅ አመለከቱ። ተቃዉሞ፤ ግጭት ግድያዉ ግን ሰከነ እንጂ አልቆመም።
ዘንድሮ ጥቅምት ኤኳዶር፤  ቺሌ፣ቦልቪያ፣ ኮሎምቢያ በአደባባይ ሰልፍ፤ ዉግዘት፣ ዉዝግብ፣ ግጭት የቀደመቻቸዉን ቬኑዙዌላ ጋር ለመወዳደር እልሕ የያዙ መስለዋል።
ጥቅምት 5 የኤኳደር መንግስት ተቃዋሚዎች የሐገሪቱን ብሔራዊ ቤተ-መንግስት በመቆጣጠራቸዉ የመንግሥት ሹማምንት ወደ ሌላ ሥፍራ ለመሸሽ ተገድደዋል።
ጥቅምት 20።ቦሊቪያ በተደረገዉ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት ኢቮ ሞራሌስ ማሸነፋቸዉ ታወጀ። ግን የምርጫዉን ዉጤት የተቃወመዉ ሕዝብ የሐገሪቱን ርዕሠ-ከተማ ላ ፓዝን አጥለቀለቃት።ሞራሌስ ሥልጣን ለቀቁ።ሕዳር 30።
«የቦሊቪያ እሕት ወንድሞቼ፣ መላዉ ዓለም  ሆይ፣ አሁን ከምክትል ፕሬዝደንቱና ከጤና ሚንስትሯ ጋር ሆኜ የሚከተለዉን እነግራችኋለሁ። የሠራተኛ ማሕበሩን መልዕክት ሰምቻለሁ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥሪም ሰምቻለሁ። ፕሬዝደንታዊ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ።»
የመጀመሪያዉ የሐገሬዉ አጡራ መሪ ሐገራቸዉን ጥለዉ ተሰደዱ።
ታሕሳስ 10። ኦስሎ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁን የዓለም የሰላም ሽልማት ኖቤልን ተረከቡ። «ለእዉነተኛ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ መሰረቱን ጥለናል።በቅርቡም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደርጋለን።»
መቀሌ፣ዎላይታ ሶዶ፣ ሞጣ፣ በየዩኒቨርስቲዎቹ የሆነና ከየስፍራዉ የሚሰማዉ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቃል-ተስፋ የሚቀጭጭ መምሰሉ እንጂ ክፋቱ።ዓመቱ አንድ ያለዉ የብራዚል ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ  ያር ቦልሳኔሮ ቃለ-መሐል ሲፈፅሙ «ብራዚልን ከሶሻሊስቶች ነፃ አወጣን»  እያሉ ሲፎክሩ ነበር።
ሕዳር ላይ ከወሕኒ የተለቀቁት የቀድሞዉ የሐገሪቱ ሶሻሊስታዊ መሪ ሉላ ደሲልቫ መልስ ሰጡ።ታሕሳስ 19።
«ቦሎሳኔሮ፣ እንደ ናዚ ጀርመን  ብራዚልን ለማጥፋት ባሕሏን ከማጥፋት ጀምረዋል። ይሕ እንዲሆን አንፈቅድም። ሌላዉን ፈተና እንደተቋቋምን ሁሉ።ይሕንንም እንቃወም።»
የዩናይትድ ስቴትስ «ጠላቶች» ኢራን፣ሩሲያና ቻይና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከሰፈረበት አጠገብ፣ ኦማን ባሕረ-ሰላጤ ላይ  የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀመሩ። ዓርብ ታሕሳስ 27።
በማግስቱ ሩሲያ ከድምፅ 27 ጊዜ የሚፈጥን ረቂቅ ሚሳዬል በይፋ መረቀች። አሜሪካኖች ከጠንካራ ፖለቲካዊ ተቃዉሞ  ጋር ምናልባት ቭላድሚር ፑቲንን እንደ ዓመቱ ተወዳጅ ሙዚቃቸዉ «Bad Guy» ይሉ ይሆናል። ድምፃዊቱ ቤሊ ኤሊሽ ናት። እኔ  ነጋሽ መሐመድ። በዘመኑ ለምትቆጥሩ፣ መልካም አዲስ ዓመት።

Evo Morales
ምስል picture-alliance/NurPhoto/M. Baglietto
Argentinien l Pro-Morales Demonstration
ምስል picture alliance/AP/G. Garello
Aghanistan, Kabul: Ashraf Ghani auf einer Pressekonferenz
ምስል picture-alliance/AP/R. Gul
Symbolbild | Papst Selfie
ምስል Getty Images/AFP/T. Fabi
Irak Schiitische Miliz droht USA nach Luftangriffen
ምስል AFP/H. Hamdani
Argentinien l Pro-Morales Demonstration
ምስል picture alliance/AP/G. Garello
Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/AP Photo/NTB scanpix/H. M. Larsen
US-Präsident Donald Trump
ምስል picture-alliance/CNP/M. Reynolds

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ