1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክፍፍል የጎላበት ዓመት

ነጋሽ መሐመድ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 21 2011

ትራምፕ በአሜሪካ ታማኝ፣ጥብቅ፤ ተሻራኪ ሐገራት ሸቀጦች ላይ ሳይቀር የቀረጥ ጭማሪ ማድረጋቸዉ ያቀጣጠለዉ የንግድ ጦርነት፣ ዓለምን ግራ ቀኝ እንዳላጋ-አሜሪካንን ከወዳጆችዋ እንደነጠለ ዓመቱ ከፍፃሜዉ ተቃረበ።

https://p.dw.com/p/3AjwK
Donald Trump und Kim Jong Un Singapur
ምስል Reuters/K. Lim

ዓለም በ2018፣ ዉይይት

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሐገራት መሐል ደኃ፣ደካማ፣አሜሪካ በመራችዉ ወይም በምትደግፈዉ «ወረራ» የተመሰቃቀሉ ሐገራት ዜጎችን መርጠዉ አሜሪካ እንዳይገቡ ማገዳቸዉ ለአብዛኛዉ ዓለም ደብዛዛ ርዕሥ ነበር።ትራምፕ  በአሜሪካ ግፊት ከዓለም ከተነጠለችዉ ሰሜን ኮሪያ ጋር ሥለ ኑክሌር ቦምብ ለመነጋገር መፍቀድ-መቀራረባቸዉ ግን ታላቅ የምሥራች።ምስራች-ተስፋዉ አስገምግሞ ሳያበቃ፣ በአሜሪካ መሪ አስተባባሪነት ኃያሉ ዓለም ከኢራን ጋር ያደረገዉን፣ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የፀደቀዉን ስምምነት ትራምፕ ማፍረሳቸዉ «ጉድ» እንዳሰኘ የጎርጎሪያኑ 2018 ሊሰናበት ዕለት ቀረዉ።

ትራምፕ በአሜሪካ ታማኝ፣ጥብቅ፤ ተሻራኪ ሐገራት ሸቀጦች ላይ ሳይቀር የቀረጥ ጭማሪ ማድረጋቸዉ ያቀጣጠለዉ የንግድ ጦርነት፣ ዓለምን ግራ ቀኝ እንዳላጋ-አሜሪካንን ከወዳጆችዋ እንደነጠለ ዓመቱ ከፍፃሜዉ ተቃረበ።

ዩናይትድ ስቴትስ አምና ይሔኔ አወዛጋቢዋን የዓለም ትላልቅ ኃይማኖቶች ከተማ እየሩሳሌምን የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ እንድትሆን እዉቅና በመስጠትዋ፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ፣ ሠላም ይወርዳል ብለዉ ነበር።ነበር።የእስራኤል ፍልስጤሞች ዉዝግብ፤ግጭት መገዳደል ግን ለሰባኛ  ዓመት ቀጠለ።

ሶሪያዎች ዘንድሮም እንዳምና ያልቃሉ።ዩናይትድ ስቴትስ ጦሯን ከሶሪያ ለማዉጣት ወስናለች።የመኖችም ይረግፋሉ።የየመን ተፋላሚ ኃይላት በቅርቡ ስዊድን ላይ ያደረጉት ስምምነት ግን አዲስ ተስፋ ሰጥቷል።

Symbolbild EU-Brexit-Gipfel
ምስል AFP/Getty Images/D. Leal-Olivas

የሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሠልማን የመንን ያጠፋዉን ወረራ በማዘዛቸዉ ከምዕራቡ ዓለም ምስጋና እንጂ ወቀሳ አልገጠማቸዉም።እንዲያዉም ለዉጥ አራማጅ እየተባሉ ሲንቆለጳጰሱም ነበር።

መሐመድ ቢን ሠልማን ቢን አብዱል አዚዝ አል ሳዑድ።የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሰፊ፤ሐብታም፤ የሙስሊሞች ቅዱስ ሥፍራዎች ባለቤት ሐገር ልዑል ናቸዉ።አልጋወራሽ ናቸዉ።ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ናቸዉ።መከላከያ ሚንስትር ናቸዉ።የኤኮኖሚና ልማት ምክር ቤት ሊቀመንበር ናቸዉ።የፖለቲካና ፀጥታ ምክር ቤት ሊቀመንበር ናቸዉ።

ከየመኑ እልቂት ፍጅት ይልቅ ስደተኛዉን ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂን አስገድለዋል ተብለዉ መጠርጠራቸዉ የትልቅ ሐገራቸዉን ትልቅ -ስም እንዳረከሰዉ፣ድርብርብ ስልጣን ክብራቸዉን እንዳጎደፈዉ ዘመኑ-በዘመን  ሊተካ ነዉ። 

ትራምፕ ኃያል፣ትልቅ፣ ኃብታም ሐገራቸዉን ከዓለም ለመነጠል ወደ ቀኝ ጠርዝ ሲገፏት፣ የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች ሐገራቸዉን ከጠንካራዉ የአዉሮጳ ማሕበር እንድትነጠል በሕዝብ ያስፀደቁት ዉሳኔ-ዛሬም ያሻኩታል።

የአዉሮጳ ሐብታም፣ኃያል፣ የብዙ ሕዝብ ሐገሪቱን ጀርመንን ለ13 ዘመን የመሩት አንጌላ ሜርክል  «በጡረታ» ለመገለል አንድ-ሁለት ሲሉ፣አምና ይኸኔ የአዉሮጳ ፖለቲካ አንፀባራቂ ኮኮብ ተብለዉ የነበሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማንኡል ማክሮ ሥልጣናቸዉንቸዉን ከ1968 ወዲሕ በፈረንሳይ ታሪክ ታይቶ ከማይታወቅ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ለማትረፍ ትግል ገጥመዋል።በዛሬዉ ዉይይታችን ከአፍሪቃ በስተቀር ባለዉ ዓለም በ2018 የጎሉ ፖለቲካዊ ክስተቶችን እንቃኛለን።

Syrien - Syrische Armee fährt in  Manbidsch ein
ምስል Reuters/K. Ashawi

ነጋሽ መሐመድ 

ሂሩት መለሰ