1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለማችን እና የኮሮና እለታዊ መረጃ  

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2012

በኢትዮጵያ በኮሮና የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር 82 ደረሰ፤ በአዉሮጳ፤ ኦስትርያና ስፔን ያወጡትን የዝዉዉር ሕግ ማላላት ጀመሩ። ድንበርዋን ለ 30 ቀናት ዘግታ የነበረዉ ዩናይትድ ስቴትስ በርዋን አሁንም ላልተወሰነ ጊዜ እንደምትዘጋ አስታዉቃለች።  በአሜሪካ በኮረና የሚያዘዉም ሆነ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር በዓለም ሃገራት ሁሉ ከፍተኛዉ ነዉ ተብሎአል።  

https://p.dw.com/p/3auGi
Symbolbild Corona-Virus Impfstoff
ምስል picture-alliance/dpa/Geisler-Fotopress

በኢትዮጵያ በኮሮና የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር 82 ደረሰ፤ በአዉሮጳ፤ ኦስትርያና ስፔን ያወጡትን የዝዉዉር ሕግ ማላላት ጀመሩ። በሌላ በኩል ከአዉሮጳ ለሚገቡ የዉጭ ሃገር ዜጎች ድንበርዋን ለ 30 ቀናት ዘግታ የነበረዉ ዩናይትድ ስቴትስ በርዋን አሁንም ላልተወሰነ ጊዜ ዘግታ እንደምትቆይ አስታዉቃለች።  ይሁንና በዩናይትድ ስቴትስ በኮረና የሚያዘዉም ሆነ የሚሞተዉ ሰዉ በዓለማችን ከሚገኙ ሃገራት ሁሉ ከፍተኛዉ ነዉ ተብሎአል።

ኢትዮጵያ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 82 ደርሶአል 

ኢትዮጵያ ዉስጥ በኮሮና ተሕዋሲ የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር 82 መድረሱን የሃገሪቱ የጤና ሚኒቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ዛሬ ከቀትር በኋላ ባሳረጫዉ ዕለታዊ መረጃ እንዳለዉ፣ ባለፈዉ 24 ሰዓት 447 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።ከተመረመሩት 8ቱ ሰዎች «የኮሮና ተሕዋሲ እንደተገኘባቸዉ ማረጋገጥ ተችሏል ሲል የጤና ሚንስቴር ያወጣዉ ያሳያል። ኢትዮጵያ ዉስጥ እስካሁን በይፋ የሚታወቀዉ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት አዝጋሚ ቢመስልም የምርመራ ቁሳቁስ እጥረት በመኖሩ ትክክለኛዉን ሁኔታ ማረጋገጥ ግን አስቸጋሪ ነዉ። እስካሁን ኢትዮጵያዉ ዉስጥ ከዚሕ ቀደም በኮቪድ19 ህመም  3 ሰዎች ሞተዋል።

ኦስትርያ የዝዉዉር ሕግን አላላች

የኮሮና ስርጭትን ለማለዘብ ሲባል በኦስትርያ ተዘግተዉ የነበሩ ሱቆች ከዛሬ ጀምሮ ቀስ በቀስ ስራ እንደሚጀምሩ ተገለፀ። የኦስትርያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር  ሰበስታይን ኩርዝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሃገሪቱ የሚገኙ 80 በመቶ የሚሆኑ አነስተኛ መደብሮች ከዛሬ ጀምሮ ቀስ በቀስ ስራቸዉን ይጀምራሉ። ይህ የኦስትርያ ርምጃ ሃገሪቱ ከኮሮና ቀዉስ አገግማ ወደተለመደ ኑሮ የሚያመራት የመጀመርያ ርምጃ ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰበስትያን ተናግረዋል።  በአዉሮጳ ሃገራት የኮሮና ቀዉስን ተከትሎ ሱቆች ከተዘጉ የተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችም  ከተቋረጡ ቤት ተቀመጡ ድንጋጌ ከተላለፈ ከሳምንታት በኋላ ኦስትርያ ህግጋትን ያላላች የመጀመርያዋ የአዉሮጳ ሃገር ናት። እንድያም ሆኖ ኦስትርያ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመከላከል በሱቆች እና ኅብረተሰብ በጋራ በሚጠቀምባቸዉ አካባቢዎች አፍና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ግዴታ መሆኑም ተመልክቶአል። ሰዎች ሁሉ እቃን ለመግዛት ወደመደብሮች ሲገቡም ሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችን ሲጠቀሙ  የአካል ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም የአፋና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

Atemschutzmaske der Kategorie FFP3
ምስል picture-alliance/dpa/C. Beutler
Österreich Coronavirus Sebastian Kurz
ምስል picture-alliance/dpa/APA/R. Schlager

ዩናይትድ ስቴትስ ኮሮና የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር ጨምሮአል

ዩናይትድ ስቴትስ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት የአዉሮጳ ተጓዥ ወደ ሃገሪ እንዳይገቡ ስትል እገዳ የጣለችበትን  ቀጠነቀጠሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘምዋን አስታወቀች። ይህ ዉሳኔ የተደረሰዉ የአዉሮጳ ሃገራት የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት በሚያደርጉት ጥረት ገና አመርቂ ዉጤት ላይ ባለመድረሳቸዉ  ነዉ ተብሎአል። የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአዉሮጳ ተጓዦችን ወደ አሜሪካ እንደማያስገቡ የወሰኑት ኢጣልያ ፤ ስፔን ከኮሮና ጋር የጀመሩት ትግል ገና ጥሩ ዉጤት አይደለም፤ ፈረንሳይም ብትሆን የኮሮና ስርጭትን ለመግታት የደነገገችዉን የዝዉዉር ሕግ ቀነገደብ በማራዘምዋ ነዉ ብለዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአዉሮጳ ሃገራት የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን በመግታቱ ረገድ አመርቂ ዉጤት ሲታይ ዩናይትድ ስቴትስ ለአዉሮጳ ሃገራት ዜጋ ተጓዦች  በርዋን በአፋጣኝ ትከፍታለች ብለዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከአዉሮጳ ወደ አሜሪካ ለሚመመጡ የዉጭ ሃገር ዜጎች በርዋን ዘግታለች ብለዉ የካቲት መጨረሻ ላይ ሲያዉጁ እገዳዉ የሚፀናዉ ለ 30 ቀናት ብቻ እንደሆን ተናግረዉ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ  በኮሮና እጅጉን የተጠቃች የዓለማችን የመጀመርያዋ ሃገር መሆንዋ ተሰምቶአል። በአሜሪካ በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23, 650 ደርሶአል ፤ በተኅዋሲዉ የተያዙ ሰዎች ደግሞ ወደ 600 ሺህ ሆንዋል። በዓለም ዙርያ በኮሮና ተኅዋሲ የተያዘዉ ሰዉ ቄጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን ተጠግቶአል፤ የሟቾችም ቁጥር 121 ሺህ መድረሱ እየተዘገበ ነዉ።  

Coronavirus New York Kingsbrook Jewish Medical Center Toter wird transportiert
ምስል Reuters/L. Jackson

ጀርመን የኮሮና ስርጭት ቀንሶአል

USA Corona-Pandemie PK Trump
ምስል Reuters/L. Millis

የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በጀርመን የወጡት የተለያዩ ሕግጋቶች እና ርምጃዎች በማኅበረሰቡ ተግባራዊ በመሆናቸዉ በእየለቱ በተኅዋሲዉ የሚያዘዉ ሰዉ ቁጥር መቀነሱን ሮበርት ኮህ የተባለዉ የተኅዋሲ ጉዳይ ጥናት ተቋም አስታወቀ። የተኅዋሲዉ ስርጭት በጀርመን ቢለዝብም ማኅበረሰቡ አሁንም ጥንቃቄዉን እንዲቀጥል ተቋሙ አስታዉቋል። የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፤ ቡና ቤቶች እና ምግቤቶች፤ እንዲሁም ሱቆች ይከፈቱ በሚለዉ ጉዳይ ላይ ለመወሰን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጀርመን ግዛት ጠቅላይ ሚኒስሮች ጋር ለመወያየት እና ለመወሰን የፊታችን ረቡዕ ቀጠሮ ይዘዋል። ትናንት እሁድ ፋሲካ በዓልን ቤቱ ተቀምጦ ያከበረዉ የጀርመን ኅዝብ  ትምህርት ቤቶች መስርያ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ ሱቆች እና የፀጉር ማስተካከያ ቤቶች  ከተለመደዉ የፋሲካ እረፍት በኃላ ማለትም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ቀስ በቀስ ይከፈታል የሚል ተስፋን ሰንቀዋል።  የተዛማች ተኅዋሲ ምርምር  ሮበርት ኮህ ተቋም ዛሬ ከቀትር በፊት በሰጠዉ መግለጫ በጀርመን ወደ 125 ሺህ ሕዝብ በኮሮና ተኅዋሲ ተይዞአል፤ 2969  ሰዉ ደግሞ ኮሮና ባስከተለዉ በሽታ ሞትዋል። 

ፈረንሳይ የዝዉዉር ህግ ቀነገደብ ተራዘመ

የአዉሮጳ ሃገራት ላለፉት ሦስት እና አራት ሳምንታት የኮሮና ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ሱቆች መዘጋታቸዉ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ማጥበቃቸዉን ለማላላት እየተነጋገሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ እስከመጭዉ ግንቦት 3 የዝዉዉር ደንቡ ሁሉ ባለበት እንደሚፀና  አስታወቀች። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቴሌቭዥን  ለሕዝባቸዉ ባደረጉት ንግግር፤ ኮሮና ተኅዋሲ አሁንም እየተፈታተን ነዉ፤ የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመግታት ህግጋት ሁሉ እስከ ግንቦት ሦስት ይፀናል ብለዋል። ማክሮ በፈረንሳይ ሱቆች እንዲዘጉ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እና የሰዎች ዝዉዉር እንዲገደብ የወጣዉ ሕግ እንዲቀጥል የተደረገዉ ፤ በፈረንሳይ ሆስፒታሎች በኮሮና ተኅዋሲ ህሙማን በመጨናነቃቸዉ  ነዉ ሲሉ ምክንያቱን ተናግረዋል። የፊታችን ግንቦት አጋማሽ በፈረንሳይ የተዘጉ ሱቆች ትምህርት ቤቶች ቡና ቤቶች እና ምግቤቶች ዳግም ይከፈታሉ ተብሎአል። በፈረንሳይ እስካሁን ወደ 15 ሺህ ሰዎች ኮሮና ባሳደረባቸዉ ሕመም ሞተዋል። 98,100 ሰዎች ደግሞ በኮሮና ተኅዋሲ ተይዘዋልበፈረንሳይ የኮሮና ቀዉስን ተከትሎ ሱቆች እና ትምህርት ቤቶች ብሎም ምግብ ቤት እና ቡና ቤቶች የተዘጉት ብሎም የዝዉዉር ሕግ የጠበቀዉ ከመጋቢት 8 ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል።     

Macron hält in Corona-Krise erneut Ansprache an Franzosen
ምስል imago images/IP3press/V. Isorex

ቱርክ በሺህ የሚቆጠሩ እስረኞችን ፈታች

 የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት የቱርክ ምክር ቤት በሃገሪቱ የሚገኙ በአስርሽዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ለመፍታት ወሰነ። በእስረኛ ከተጨናነቁት የቱርክ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚለቀቁት እስረኞች ወደ 90 ሺህ እንደሚሆኑ ተዘግቦአል። ከቱርክ መንግሥት በኩል በወጣዉ መረጃ መሰረት ምህረት ከተደረገላቸዉ መካከል ገሚሱ መለቀቅ የጀመሩት ምክር ቤቱ ወሳኔዉን ማስተላለፉን ይፋ ከማድረጉ ከቀናት በፊት ጀምሮ ነዉ።  ገሚሱ እስረኛ ከእስር ቤት ቢለቀቅም የቁም እስረና ሆኖ ከቤት እንዳይወጣ  የተነገረዉ ነዉ ተብሎአል። ከተለቀቁት እስረኞች መካከል በአብዛኛዉ በቱርክ የፀረ-ሽብር ሕግ መሰረት የተከሰሱ ፤ ጋዜጠኞ እና ፖለቲከኞች መሆናቸዉ ታዉቋል። የቱርክ ፓርላማ እስረኞች ን ለመፍታት ዉሳኔ ከማስተላለፉ በፊት ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፤ በቱርክ እስር ቤት ዉስጥ የነበሩ ሦስት እስረኞች በኮሮና ተኅዋሲ ህመም ምክንያት ሕይወታቸዉ ማለፉ ተመልክቶአል።    

Türkei Ankara | Coronavirus & Ausgangssperre | Sicherheitsbeamte
ምስል picture-alliance/abaca/Depot Photos/A. Antakyali

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ