1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐበይት የጤና እና አካባቢ ክንውኖች በ2021

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2014

ተሰናባቹ ጎርጎርዮሳዊ ዓመት 2021 መላውን ዓለም ያዳረሰው እና ያስጨነቀው የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ክትባት ብዙ የተባለበት እና ከሞላ ጎደል የተዳረሰበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል። በዚሁ ዓመትም ወረርሽኙ አደናቅፎት የነበረው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባኤ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/44v5A
Israel Coronavirus l Impfung, BioNtech
ምስል Jack Guez/AFP

« ጤና እና አካባቢ 2021 ዓ. ም ሲቃኝ»

በተሰናባቹ ዓመት 2021 መባቻ በርካታ ሃገራት ክትባት ለዜጎቻቸው ማዳረስ የጀመሩበት እንደመሆኑ ወረርሽኙን የመቆጣጠር ተስፋ የታሰበበት እንደነበር አይዘነጋም። ዓመቱን ሙሉ ክትባቶች ሲሰጡ ቢከርምም ተሐዋሲው እራሱን እየለወጠ መሰራጨቱን በመቀጠሉ አሁንም ሃገራት ላይ ናቸው።  ኮቪድ 19 ወረርሽኝነቱ እንዲያበቃ ክትባቱ ለሁሉም በእኩልነት መዳረስ ይኖርበታል ባይነው የዓለም የጤና ድርጅት፤ በሌላ በኩል በዚሁ ዓመት ክትባት በበርካታ ሃገራት መሰጠቱ በኢንተርኔት መስመር በርቀት መነጋገሩ ቀርቶ ዘንድሮ ግላስጎው ላይ ከ190 ሃገራት በላይ መሪዎች እና ተወካዮች በአካል ተሰባስበው ስለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ለመወያየት ችለዋል። 

US Lafayette | Hurrikan Ida
ምስል Scott Clause/AP

የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ዓለምን ከዳር እስከዳር ያካለለበት ሁለተኛ ዓመቱን በያዘበት በጎርጎሪዮሳዊው 2021 ከአየር ጠባይ ጋር የተያያዙ በርከት ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተዋል። ሃይቲን ጠንካራ የመሬት መንቀጥቀጥ ለከፋ ችግር ሲዳርጋት፤ የአውሮጳ እና እስያ ሃገራት ደግሞ በሞቃት ወራት የዘነበ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የሕይወት እና ንብረት ውድመት አድርሶባቸዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዚህ ተሰናባች ዓመት ዝናብ እና ውሽንፍር ያስከተለው ጎርፍ በብዙ ሃገራት የተፈጥሮ አደጋዎች ካደረሱት ጉዳት አንድ ሦስተኛውን እጅ ይሸፍናል።  

ሴሮያ የሚል ስያሜ የተሰጠው ኢንዶኔዢያን የመታው ውሽንፍር ያስከተለው የመሬት መናድ ቢያንስ ለ222 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፤ ሕንድ ውስጥ በግንቦት ወር የተከሰተው ውሽንፍርና ጎርፍ ቢያንስ ለ200 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፤ በተመሳሳይ ሕንድ እና ኔፓልን ጥቅምት ወር ላይ ባጥለቀለቀው ጎርፍ 201 ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል። ነሐሴ ወር ላይ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ አይዳ የሚል ስያሜ በተሰጠው ወጀብ እና ጎርፍም የ91 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በዚህ ዓመት ጀርመን እና ቤልጂየምም በሐምሌ ወር ለተከታታይ ቀናት የወረደ ዝናብን ተከትሎ በተለይ ከቤልጂየም በሚጎራበተው የምዕራብ ጀርመን ፌደራላዊ ግዛት ኖርድ ራየን ቬስትፋለን በወንዝ ዳር በሚገኙ ከተሞች የደረሰው የጎርፍ አደጋ 196 ሰዎችን ሕይወት በጀርመን ሲያሳጣ 38 ደግሞ ቤልጂየም ውስጥ ሞተዋል። በተመሳሳይ ወቅት ቻይና ውስጥ እንዲሁ ጎርፍ ባስከተለው የመሬት መናድ ቢያንስ 302 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

Eco India I ECIE Flood Protection
ምስል DW

በየዓመቱ በአማካኝ ለ20 ጊዜ ኃይለኛ ውሽንፍር እና ወጀብ በምታስተናግደው ፊሊፒንስ በዚህ በያዝነው ወር አጋማሽ የደረሰው አደጋ ቢያንስ ለ375 ሰዎች ሞት እንዲሁም ለ500 ሰዎች መጎዳት ምክንያት ሆኗል። በሰዓት 195 ኪሎ ሜት የሚምዘገዘገው ውሽንፍር ባደረሰው ውድመትም በብዙ ሺህ የሚገመቱት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።  በሌላ በኩል ሃይቲን ባለፈው ነሐሴ ወር የመታት 7,2 የተገመተው የመሬት ነውጥ 2,248 ሰዎችን ገድሏል፤ በርካታ ሺህዎችን ለጉዳት ዳርጓል። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ መኖሪያ ቤታቸውን አውድሟል። በተለያዩ ሃገራት ከደረሱት በርካታ ከአየር ጠባይ ጋር የተያያዙ የተፈጥሮ አደጋዎች አስሩ እጅግ ከባድ ክስረት ማስከተላቸው ነው የተነገረው። በየዓመቱ ከአየር ጠባይ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ አደጋዎች ያደረሱትን ጉዳት የሚመዘግበው የብሪታኒያ የክርስቲያን ረድኤት ድርጅት እንደሚለው በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከ170 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ጉዳት ደርሷል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ ከ1,3 ሚሊየን የሚበልጡ ደግሞ ከመኖሪያ ቦታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። እንደመረጃው ከሆነም ከባድ ጉዳት እና ኪሳራ ካስከተሉት ሁሉ የባሰው ምሥራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስን የገረፈው አይዳ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከባሕር ላይ የተነሳው ማዕበል እና ውሽንፍር ነው። ባለፈው 2020 ዓ,ም በተፈጥሮ አደጋዎች ብቻ የ150 ቢሊየን ዶላር ውድመት መድረሱን ያመለከተው መረጃው ይኽ ሁሉ የሚሆነው ሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል።  
በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተስተጓጉሎ በዚህ ዓመት የተካሄደው 26ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የተጋነነ ባይባልም ተስፋ የታየበት እንደነበር የሚናገሩ አሉ። ከሁሉም በላይ በርካታ ሃገራት ወደ ከባቢ አየር የገባውን ሙቀት አማቂ ጋዝ በተፈጥሮ መንገድ ማስወገድ እንዲቻል በደን ክብካቤ ላይ ለማተኮር ቃል ገብተዋል። ሌላው በአዎንታዊነት የተወሰደው ከቅሪተ አጽም ኃይል ማመንጨትን ስለማቆም የተባለው ነው፤

UN-Klimakonferenz COP26 in Glasgow
ምስል Jane Barlow/empics/picture alliance

«ትናንት ምሽት ዓለም ለማየት ወደሚፈልገው ጨዋታውን ከሚለውጥ ስምምነት ላይ ደርሰናል። 200 የሚሆኑ ሃገራት ከባቢ አየርን ብከላ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚናቸውን ለመጫወት በግላስጎው የአየር ንብረት ስምምነት ላይ ስማቸውን አኑረዋል። እየጨመረ ያለውን የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ ለማድረግ ግልጽ የሆነ አካሄድ ቀይሰዋል፤ የከሰል የኃይል ምንጭት እንዲቆም የሚያደርግ የመጀመሪያ ርምጃ ወስደዋል። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ከከሰል ኃይል ማመንጨት እንዲቆም ጠይቋል።» 

UN-Klimakonferenz COP26 in Glasgow I Protest
ምስል Christoph Soeder/dpa/picture alliance

ያሉት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሲሆኑ እሳቸው እንዳሉትም በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ ከድንጋይ ከሰል ኃይል ማመንጨት ይቁም የሚለው አዋጅ በዚህ ጉባኤ ታውጇል። ተግባራዊነቱን የሚጠራጠሩ ግን ጥቂት አይደሉም። በካልጋሪ ካናዳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የጉባኤውን አጠቃላይ ውጤት አስመልክቶ በወቅቱ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው ጥርስ የሌለው ስምምነት ብለውታል።

«ምናልባት እንዳለ ጨለማ ነው ላለማለት ስምምነቱ የሚቀጥለው ዓመት የሚደረገው ጉባኤ የበለጠ ጥርስ ያለው የሚያደማ፤ ጥልቅ የቅነሳ ቃልኪዳኖችን ይዘው ሊመጡ ስምምነቶች ስለተደረገ በዚያ ተስፋ እናደርጋለን። በገንዘቡ በኩል እንደዚሁ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በፊት 100 ቢሊየን ዶላር በዓመት ይሰበሰባል ተብሎ የከሸፈው፣ አሁን ወደ 500 ቢሊየን ይሰበሰባል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚለው እና ለአዳጊ ሃገራት የማጣጣሚያ ፕሮጀክቶች እንዲውል የታሰበው እሱም ያው እንደበጎ ልናየው እንችላለን። አጠቃላይ ግን እንዳልኩት የአየር ንብረት ለውጥ እሚፈልገው ይታወቃል፤ ሳይንሱ የታወቀ ነው፤ ከዚያ አንጻር እዚህ ግባ የማይባል ስምምነት ነው ብዬ ነው የምገልጸው።»

ባለፉት 12 ወራት የተለያየ የተፈጥሮ አደጋ በየቦታው ቢደርስም የየዕለቱ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንደሳበ የቀጠለው ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የኮሮና ተሐዋሲ ያስከተለው ጉዳት እና ተጽዕኖ ነው። የኤኮኖሚ አቅማቸው የጠነከረው በርካታ ሃገራት በዚሁ ዓመት ፤ እውቅና ያገኙ ክትባቶችን ለኗሪዎቻቸው ለማዳረስ ሲታገሉ በአንጻሩ ክትባቱን ለመውሰድ የሚያንገራግረው ቁጥሩ ቀላል ባለመሆኑ የተለያዩ አስገዳጅ ስልቶችን ተግባራዊ ሲያደርጉ ታይቷል። ለምሳሌ ጀርመን በበጋ ወራት የነበረው የተለሳለሰ አቀራረብ የቅዝቃዜው ወቅት ገብቶ ክረምቱ ሲጠናከር ያልተከተቡ ሰዎች ላይ የተለያዩ እገዳዎችን አድርጋለች። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት ሁለቱን ክትባት የወሰደው ከጠቅላላ ነዋሪዎች 70 ከመቶ ደርሷል። ከተከተቡ ስድስት ወር ያለፋቸው ማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱ እየተጠየቀ የኮሮና አዲስ ልውጥ ተሐዋሲ ኦሚክሮን መከሰት ሌላ ስጋት ሆኗል። የመዛት ፍጥነቱን አሳሳቢ ነው የተባለው ኦሚክሮን በብዙ ሃገራት መገኘቱም በሳምንቱ መጨረሻ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር የሚቆጥረው ዓለም የሚያከብረውን የገና በአል ለሁለተኛ ጊዜ እጅግ የቀዘቀዘ አድርጎታል። በእነዚህ የበዓል ቀናትም በፈረንሳ እና ጣሊያን በተሀዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እጅግ መጨመሩ ተነግሯል። ፈረንሳይ ውስጥ በበዓሉ ዕለት ብቻ 104,611 ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸውን ገልጻለች። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 78 በመቶ የሚሆነው የፈረንሳይ ነዋሪ ተከትቧል። ጎረቤቷ ጣሊያንም እንዲሁ በፈረንጆቹ የገና ዕለት ከ54 ሺህ በላይ አዲሱ ተሐዋሲው የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች። ጀርመንም በዚሁ የበዓል ቀን 22,214 አዲስ በተሐዋሲው የተያዙ መኖራቸው ተገልጿል። በተሀዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየሀገሩ በመበራከቱም  ወረርሽኙ እንዳዲስ ማዕበል ሊቀሰቀስ እንዳይሆን የሚለውን ስጋት አጠናክሮታል። የወረርሽኙን ዳግም ማገርሸትን ታሳቢ ያደረጉ እገዳዎች በየሃገራቱ መደረግ ብዙዎችን ወደ አደባባይ ለተቃውሞ እያስወጣ ነው። በተለይም ክትባትን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሰዎች የግድ እንዲወስዱ የሚደረጉ ጥረቶች ጠንካራ ተቃውሞ አውሮጳ ውስጥ እያስከተሉ ነው። ጀርመን ውስጥ ይኽንን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ዜጎች በቁጣ የታጀበ ድምጻቸውን ሲያስተጋቡ ቪየና ኦስትሪያ ላይ ደግሞ ወደ 40ሺህ የተገመቱ ሰልፈኞች የእንቅስቃሴ ገደቡን እና የግዳጅ ክትባቱን በአደባባይ በማውገዝ ከፖሊስ ጋር እስከመጋጨት ደርሰዋል። የአውሮጳ ሕብረት መቀመጫ በሆነችው ብራስልስ እና ሌሎች ሃገራትም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ለኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ተጠናክሮ መቀጠል ክትባቱ ለሁሉም ካለመዳረሱ ጋር ይገናኝል ብሏል። የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ክትባቱን ያዘጋጁ ሃገራት ለሦስተኛ ጊዜ ክትባት ለማዳረስ ጥረት ሲያደርጉ በሌሎች አቅም በሌላቸው ሃገራት በቂ ክትባት ገና እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

Proteste gegen die Corona-Maßnahmen - Rostock
ምስል Bernd Wüstneck/dpa-Zentralbild/dpa/picture alliance
Symbolbild Corona Covid Variante Omicron B.1.1.529
ምስል Pavlo Gonchar/Zumapress/picture alliance

በዚህ መሀል እስራኤል ከ60 ዓመት በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ አራተኛ ክትባት ለመስጠት ማሰቧን አሳውቃለች። ኦሚክሮን የተሰኘውን አዲሱ ልውጥ ተሐዋሲን በመጀመሪያ ይፋ ያደረገችው ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ምክንያት የበረራ እግድ የደረሰባት በዚሁ ዓመት ነው። መለዋወጡን የቀጠለው የኮሮና ተሐዋሲ ከቀናት በኋላ በሚጀምረው አዲስ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መፍትሄ ይገኝለት ይኾን የሚለው አሁንም ስጋት እና ጥያቄ እንደሆነ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ