1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጥረት በኦሮሚያ ከተሞች

ረቡዕ፣ ጥቅምት 12 2012

የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የኦሮሞ መብት ተሟጋች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን (OMN) ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ተሰማርተዋል መባሉን ተከትሎ በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች ውጥረት ነግሷል።

https://p.dw.com/p/3Rns8
ምስል DW/S. Wegayehu

በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች ውጥረት ነግሷል

የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የኦሮሞ አክቲቪስት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ቴሌቬዥን (OMN) ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር ጀዋር መሐመድን መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ተሰማርተዋል መባሉን ተከትሎ በአብዛኞቹ የኦሮሚያ ከተሞች ውጥረት ነግሷል። ድርጊቱን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እየተደረገባቸው ካሉ ከተሞች መካከል በሀረር ሶስት ሰዎች ተገድለው ከሃምሳ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንና በአዳማ አንድ ሰው ተገድሎ በርከት ያሉት መቁሰላቸውን እንዲሁም የንብረት ውድመት መድረሱን በስፍራው የነበሩ የአይን ተናግረዋል። 

በሀረር ከተማ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከአጎራባች የምስራቅ ሃረርጌ ወረዳዎች ወደ ከተማዋ የመጡ ወጣቶች ጭምር የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አንዲት የአይን እማኝ አስረድተዋል። በጥቃቱም ሶስት ሰዎች ተገድለው ከሃምሳ የሚልቁት መቁሰላቸውን በአይኔ አይቻለሁ ብለዋል። «ልጆች ሰልፍ ወጥተው ተሰልፈው እየሄዱ ነበር፤ በኮምቦልቻ ወረዳ በኩል የገቡት ተመተዋል፤ ከፈዲስ ወረዳ በኩል የመጡትም ተመተዋል፤ ሶስት ሰዎች ሞተዋል። በአጠቃላይ በኦፕሬሽን ውስጥ ያሉና እና በአይናችን ያየናቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሃምሳ ይሆናሉ። አሁን እንግዲህ ወጣቶቹን አንድ በአንድ ለመያዝ እየሞከሩ ነው፤ ወደ እስር ቤት ያስገቧቸውም አሉ። ጉዳት ደርሶባቸው አሁንም ወደ ሃኪም ቤት እየመጡ ያሉ አሉ። በዱላ እየደበደቧቸው ነዉ፤ የቦምብ ውርወራም ነበር።» 

የሀረሪ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ናስር ዩያ በከተማዋ ከጥዋት ጀምሮ ሲካሄድ በነበረው የተቃዉሞ ሰልፍ በተፈጠረ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉንና አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል። ተጨማሪ የማጣራት ስራዎችንም እየሰሩ ስለመሆኑ አስረድተዋል። «ጥዋት ላይ ሰላም ነበር ፤ ነገር ግን በአንድ ቀበሌ በተፈጠረ ግጭት ሶስት ሰዎች ተዳክመዋል። ከእነርሱ ውስጥ ሁለቱ ሞተዋል። ነገሩን አሁን እግር በእግር እየተከታተልነው ነው። ጥበቃ ላይ የነበሩ የመከላከያ ወታደሮች ናቸው የሚሉ አሉ። በእኛ በኩል ያሰማራነው የጸጥታ አካል የለንም ። ህዝቡ በሰላም ድምጹን አሰምቶ እንዲመለስ ነበር ፍላጎታችን፤ ለምን ይህ እንደሆነ እያየን ነው።» 

Äthiopien Addis Abeba Junge Menschen vor Haus von Jawar Mohammed
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

በአዳማው ተቃውሞ ፋብሪካ ሊዘርፉ ነበር በተባሉ ሰዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ስልሳ ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩም ይህንኑ አረጋግጧል። ባለቤታቸው ድብደባ ደርሶባቸው አዳማ ሆስፒታል በማስታመም ላይ የሚገኙ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወይዘሮ እንዳሉት ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የሚገኙት ቁጥራቸው በርከት እንደሚል ነው። «አሁን ሃኪም ቤት ነው ያለነው ህክምና እየወሰደነው፤ ጭንቅላቱ ላይ ላይ ነው የተመታው፤ ዱላ ነው ። ብዙ ነው ፤ ብዙ ነው። እኛ ሃይለማሪያም ሄደን አጣን ። ከሆስፒታል የወጡ አይቻለሁ አንድ ሁለት ሰው አይቻለሁ(የሞቱ) 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ከማለዳው ጀምሮ በከተማዋ በተፈጠረው ነውጥ ሁለት ሰዎች ተገድለው ስልሳ ስምንት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW) አረጋግጠዋል። « በአዳማ ከተማ ጥዋት ከአንድ ሰአት ጀምሮ መንገድ ተዘጋግቶ ነበር። ከዚያ በኋላም የዝርፊያ ሙከራ ተደርጎ ነበር ፤ አፍሪካ በሚባል ፋብሪካ ውስጥ ዝርፊያ ለማድረግ ሲሞክሩ ጥበቃው ወደ ሰማይ መተኮስ ሲገባው ወደ ጎን ተኩሶ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። እዚያው ፋብሪካ ውስጥ በተፈጠረ ሌላ ግጭት እርስ በእርስ በመደባደብ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። ሌላ ቦታም እንዲሁ የአንድ ድርጅት ጥበቃ ለመከላከል በሚል ተኩሶ አንድ ሰው ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።የተመታው ሰው በአደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ከዚያ ውጪ በእርስ በእርስ ግጭት ስልሳ ስምንት ሰዎች ቆስለው በሆስፒታል የህክምና ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው። ድነው ወደ ቤት የገቡም አሉ።» በአዳማ ከተማ የእርስ በእርስ ግጭት የባለውን ከንቲባው እንዲያስረዱን ጠይቀን መንገድ እንዲዘጋና እንዳይዘጋ በሚፈልጉ ወገኖች መካከል የተፈጠረ ነበር ሲሉ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል። 

ከአዳማ ሌላ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች መንገድ ተዘግቷል። በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችም ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ሰአት ድረስ በአራቱም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች መዘጋታቸውን በየአካባቢዎቹ ያሉ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። በአዳማ፣ ጅማ እና ሀረር ከተሞች ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች «ጃዋርን የሚነካ ማን ነው?» የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ በተቃራኒው አዳማ እና በአዲስ አበባ ጫፍ ባሉ አካባቢዎች ጃዋርን የሚኮንኑ ድምጾች መደመጣቸውን የአይን እማኞች ጠቁመዋል። 

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኦሮሞ አክቲቪስት እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ ‘በፖሊስ እርምጃ ተወሰደብኝ’ ብለው ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው ሲል ወቀሳውን አጣጥሏል። የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው የተዘጉ መንገዶች እና የመገልገያ ቦታዎች ተከፍተው ህብረተሰቡ በሰላም እንዲንቀሳቀስ ለህብረተሰቡ እና ለፀጥታ ኃይሎች መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በአዲስ አበባ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው የጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት አካባቢ አሁንም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች ተሰብስበው ይገኛሉ። በራፉ ላይ ክላሺንኮቭ መሳሪያ የያዘ ሰው እና ሚስማር የተመታበት ዱላ የያዙም ይታያሉ።

ታምራት ዲንሳ

ተስፋለም ወልደየስ