1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጊያ ያነቀው የትግራይ እና የአማራ ግብርና

ሐሙስ፣ ነሐሴ 6 2013

የተ.መ.ድ. በመጪዎቹ ሦስት ወራት ቀድሞም የተከሰተ ረሐብ የበለጠ ይበረታባቸዋል የሚል ማስጠንቀቀያ ከሰጣቸው 23 አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። በትግራይ ዘጠኝ ወራት የዘለቀውና ወደ አማራ ክልል የተዛመተው ውጊያ ለእርሻ ሥራዎች ማነቆ በመሆኑ ባለሙያዎች ብርቱ ሥጋት አድሮባቸዋል። ውጊያ ባለባቸው አካባቢዎች ገበሬዎች ማሳቸውን ጥለው መሸሽ ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/3yrDS
Tigray Konflikt | Äthiopien Eritrea Flüchtlinge
ምስል YASUYOSHI CHIBA/AFP

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ውጊያ ያነቀው የትግራይ እና የአማራ ግብርና

ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው ትናንት ማክሰኞ በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው የኮምቦልቻ ከተማ የገቡት የመርሳው ገበሬ አቶ መሐመድ ሁሴን ከአንድ በጎ ፈቃደኛ መኖሪያ ቤት መጠለያ ቢያገኙም ልባቸው አላረፈም። አቶ መሐመድ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ልጆቻቸውን ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሚንደረደረው ውጊያ ለማትረፍ መንገድ ሲጀምሩ ልብስ አልያዙም፤ በቂ ገንዘብም በኪሳቸው አይገኝም። የሚከነክናቸው ግን መርሳ የቀሩት የአያታቸው እጣ ፈንታ ነው።

"ከእኔ ጋር የምትኖር አያት አለችኝ። እሷን ትቺያት ነው የመጣሁት። ይዢያት እንዳልመጣ መንቀሳቀስ አትችልም። በመኪና ይዤያት አልመጣ፤ ገንዘብ የለም፤ መኪና የለም። ዝግ ነው መንገዱ። እነዚህን ትናንሽ ልጆች መሸከም ራሱ በግድ ነው" የሚሉት አቶ መሐመድ "አሁን እዚያ በየቤቱ ትልልቅ መንቀሳቀስ የማይችሉ አዛውንቶች አሉ። እኛስ እሺ እነዚህን ልጆች ይዘን አመለጥን። እነዚያ ሰዎች ምንድነው የሚሆኑት?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ መሐመድ እንደሚሉት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት ሐራ በተባለ አካባቢ በኩል ወደ መርሳ የገቡ የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው። እንደ አቶ መሐመድ ሁሉ ወልድያ፣ ውርጌሳ እና መርሳን ጨምሮ ውጊያው ከደረሰባቸው አካባቢው ከእርሻ እና ሌሎች ሥራዎቻቸው የተፈናቀሉ በኮምቦልቻ ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት ብቻ ቢያንስ 50 አባወራዎች መጠለላቸውን ዶይቼ ቬለ ለተፈናቃዮቹ መጠጊያ ከሰጡ በጎ አድራጊ ለመረዳት ችሏል።

"ማሽላ ኩትኮታ አለ። ደባላ የምታርምበት አረም አለ፤ ጤፍ አረም አለ። የእኔ የሚኮተኮት ማሽላ አለ። ማሽላው ራሱ ሰው የመደበቅ አቅም ደርሷል" የሚሉት አቶ መሐመድ እንዲህ በነሐሴ ውጊያ ከደጃፋቸው ባይደርስ ኖሮ ሥራ የሚበዛባቸው ባተሌ ገበሬ ነበሩ። በዘንድሮ ክረምት ግን የዘሩትን ማሽላ የሚኮተኩቱበት ዕድል የላቸውም። የተዘራውም ማሳ የውጊያ አውድማ ሆኗል።

"ትናንትና እንዳይሆን ነው ያደረጉት። መሀሉ ላይ ጥይት እየተኮሱ ማሽላው ራሱ ጠፍቷል። እየደረሰ የነበረውን ማሽላ አወደሙት። ምርት ለመስጠት የደረሱ ብዙ ነገሮች አሉ። እነሱ ሁሉ ወደሙ። የጁንታው ቡድን መደበቂያ፣ መሳሪያ መታኮሻ ሆነ። ተደብቆ መሳሪያ ይተኮስበታል፤ ጠቅላላ ማሽላው በመሳሪያ ከመሬት ላይ ጠፋ" እያሉ ተዋጊዎቹ በአካባቢው ከደረሱ በኋላ ደረሰ ያሉትን ጥፋት ዘርዝረዋል።

Äthiopien Lalibela
የትግራይ ኃይሎች ወደ በአማራ ክልል ወደሚገኘው የሰሜን ወሎ ዞን ከተሻገሩ በኋላ ገበሬዎችን ጨምሮ በርካቶች ኮምቦልቻ እና ደሴን ወደመሳሰሉ ከተሞች ሸሽተዋል።ምስል Sergi Reboredo/picture alliance

ወደ አማራ ክልል የተስፋፋው ውጊያ የግብርና ሥራዎችን ከማስተጓጎል ባሻገር የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥላውን አጥልቷል። ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻ እና ደሴን  በመሳሰሉ ከተሞች በተወሰነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ናቸው። የመንግሥት ተቋማትም በቅጡ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ከወልድያ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የስሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል በውጊያው ምክንያት ሥራ አቁሟል።

በማዕከሉ በተባባሪ ተመራማሪነት የሚያገለግሉት አቶ ስዩም አሰፌ እንደሚሉት የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የውጊያ ቀጠና ከሆኑ ወር በላይ ሆኗቸዋል። አቶ ስዩም "ቀድሞ ሚያዝያ ላይ የተዘራ ማሽላ አለ። እንደገና ሐምሌ ሲገባም የሚዘራ ማሽላ አለ። ጤፍ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 20ዎቹ ነበር የሚዘራው። ሙሉ በሙሉ ራያም ላይ ጤፍ አልተዘራም። የጁ የሚባለውም አካባቢ አርሶ አደሩ ስላልተረጋጋ መዝራት አልቻለም። የገጠሩም የከተማውም ሰው ነው የፈለሰው። ስለዚህ አምራቹ ኃይል አሁን ምርት ላይ አይደለም ማለት ነው። አሁን አረም አለ፣ ማዳበሪያ መጨመር አለ፣ መኮትኮት አለ። አሁን ከዚያ ውጪ ነው። [ሰብሉ] በአረም ይበላል። ወደ ቆላው አካባቢ ስትሔድ፤ ሐራ እና ወደ ሶዶማ በእንስሳት እርባታ ሰፊ ቁጥር ነው ያላቸው። አሁን ከእነ እንስሳቶቻቸው ሁሉ የተፈናቀሉ አሉ። ስለዚህ አጠቃላይ ግብርናውን በጣም ነው የጎዳው" ሲሉ አስረድተዋል።

"ሕዳር ላይ ተመርቶ የሚሰበሰበው እህል ሐምሌ እና ነሐሴ በብዛት የሚያልቅበት ነው። ሐምሌ እና ነሐሴ ፈጣን ሰብሎችን ዘርቶ መስከረም ላይ ድራሾት የሚባል ነገር አለ። ቶሎ የሚደርስ ጤፍ፣ አተር፣ ሐምሌ ላይ የሚደርሱ ሰብሎችን አርሶ አደሩ ይጠብቅ ነበር። ስለዚህ የምግብ እጥረቱ አሁን ጀምሮ ነው ያለው። ምክንያቱም አብዛኛው ተፈናቃይ አርሶ አደር ነው። አርሶ አደሩም የከተማውም ነዋሪ ከራያ አካባቢ ወልድያ ተፈናቅሎ መጥቶ ነበር። አሁን ጤፍ አልተዘራም። ወደ ኋላ ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ሽምብራ እና የተለያዩ የጥራጥሬ ሰብሎች የሚዘራበት ወቅት ነበር። አሁን ይኸም ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው። በተለይ ምሥራቅ አማራ ዝናብ አጠር ነው። ዘንድሮ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። የዝናብ ሁኔታው ቀድሞ ነው የገባው። ሰኔ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጀምሮ እስካሁን ያለው የዝናብ ሥርጭቱ የተሻለ ነው። ስለዚህ ጥሩ ምርት የሚገኝበት ወቅት ነበረ። ነገር ግን ካሁኑ ጀምሮ ረሐብ ጀምሯል፤ ተፈናቃዮች መጠለያ የላቸውም። የእንስሳት መኖ ችግር ይኖራል። የተፈሉ ችግኞች እንኳ መትከል አልተቻለም።"

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ውጊያ ወደ አማራ ክልል ከመዝለቁ በፊት በትግራይ ክልል የከፋ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ አሳድሯል። በቤልጅየም ጌንት ዩኒቨርቲ የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ እምነት ነጋሽ የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም ውጊያው በትግራይ ማሳዎች ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ የሚገመግም ትንታኔ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመተባበር አዘጋጅተዋል። "ሁሉም የተጎዳ ቢሆንም" የትግራይ ክልል ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምዕራባዊ ክፍሎች በውጊያው ምክንያት የግብርና ሥራ በከፍተኛ ደረጃ የተስተጓጎለባቸው እንደሆኑ አቶ እምነት ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። አቶ እምነት እንደሚሉት በትግራይ በወርሀ ሰኔ አሊያም ቀደም ብሎ ገበሬው የእርሻ ዝግጅት ማድረግ ቢኖርበትም በውጊያው ሳቢያ ተስተጓጉሏል።

Äthiopien Frau mit Teff-Getreide
ምስል picture-alliance/blickwinkel/G. Fischer

አቶ እምነት "በነበረው የጦርነት ሁኔታ በነጻነት መንቀሳቀስ አይቻልም ነበር፤ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ቁሳቁስ የመሳሰሉ የእርሻ ግብዓቶች ማግኘት አይችልም ነበር። በዚያ ምክንያት በጊዜው መዝራት አልቻለም፣ ማረስ፣ መሬቱን ማዘጋጀት አልቻለም" ሲሉ የትግራይ ገበሬ በተያዘው አመት ያለፈበትን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተናጠል "ሰብዓዊ የተኩስ አቁም" ቢያውጅም  ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ከተኩስ አቁሙ ዓላማዎች አንዱ የትግራይ ገበሬ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን ዕድል መስጠት ነበር። አቶ እምነት እንደሚሉት የኢትዮጵያ ጦር ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ የትግራይ ገበሬ ወደ እርሻ ሥራው የመመለስ ዕድል ቢኖረውም "ዘግይቷል።"

"ሰኔ መጨረሻ አካባቢ የትግራይ መንግሥት መቀሌ ከገባ በኋላ የፌድራል መንግሥት ከወጣ በኋላ የእርሻ እንቅስቃሴውም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴው ፈታ ያለ ነው። ቢሆንም ግን ጊዜው ካለፈ በኋላ ነው። ይዘራል ግን ዘግይቶ ነው። ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር ሊኖር ይችላል። ግን ከዚያ በኋላ ሊዘሩ ለሚችሉ አዝርዕት ነው እንጂ ለአንዳንዶቹ ጊዜው አልፏል። ያልታረሰ መሬትም አለ። በዚያው ልክ ሰዉ ስለተፈናቀለ ወደ እርሻ ቦታው መመለስ ስለማይችል፤ አቅሙም የሌለውመልሶ ማስፈርም ከባድም ስለሚሆን ተስተጓጉሎ የሚቀርም አለ። አብዛኛው አልሚ የምንለው ኃይል ደግሞ ወደ ጦር ግንባር ገብቷል" ሲሉ አስረድተዋል። 

በሳተላይት ምስሎች አማካኝነት በክልሉ የመስኖ ማሳዎች በጣም መቀነሳቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል። ከዚያ ባሻገር ሰብል የተዘራባቸው የመስኖ ማሳዎችን ገበሬው በቦታው ሆኖ ዕለት ከዕለት መንከባከብ አለመቻሉን ይጠቅሳሉ። "መስኖ ላይ ብዙ ጊዜ የሚተከለው ሸጠው ብር የሚያገኙበት፣ ኑሯቸውን የሚደግፉበት ሰብል ነው። እነዚያ ግን ሁሌም መሬቱ ላይ ሆነህ መከታተል ይፈልጋሉ። ግን ይኸንን ማድረግ አይችሉም" ሲሉ አስረድተዋል።

 

Heuschreckenplage in Äthiopien
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ውጊያ ከመቀስቀሱ በፊት የአንበጣ ወረርሽኝ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ሰብሎች ላይ የከፋ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበርምስል Ali Mekonnen

በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች እና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ በትግራይ ከተዘራው ሰብል ሊገኝ የሚችለው ምርት ከሚጠበቀው አንድ አራተኛው ቢበዛ ግማሽ ያክሉ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ትግራይ ላይ ብቻ የምርቱ 25 በመቶ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ አውድሞታል። ከምግብ ዕርዳታ ወጥቶ የማያውቅን ሕዝብ ከምርቱ ላይ 25 በመቶ በአንበጣ ወደመ ማለት አሳሳቢ ነው" የሚሉት አቶ እምነት አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታከልበት ሕዝቡ "ምን አልባትም በታሪክ ያልነበረ አደጋ የተጋረጠበት ይመስላል" ሲሉ ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ጥቂት ጦርነት ባልተካሔደባቸው አካባቢዎች ምርት ሊኖር እንደሚችል አቶ እምነት ተናግረዋል። ይሁንና "በምዕራብ [ትግራይ] ሰሊጥ እዚያው ተቃጥሎ ነው የቀረው። ሰሜን ምዕራብም የኤርትራ ወታደር እዚያው መጥቶ ነው ያቃጠለው። አብዛኛው ቦታ ምርት አልተሰበሰበም ነበር" ሲሉ በውጊያው በግብርና ላይ የደረሰው ጉዳት ይዘረዝራሉ።

ገበሬው በውጊያው ምክንያት ማሳውን ሳያዘጋጅ፣ ግብዓቶች ሳይቀርቡለት ቀርቶ ማረስ ባለመቻሉ አቶ እምነት እንደሚሉት "ምርታማነቱ በጣም እንደሚቀንስ ይጠበቃል።" "ምንም ምርት የማይኖርባቸው አካባቢዎችም ይኖራሉ።" የሚሉት ባለሙያው በሳተላይት አማካኝነት የሰበሰቧቸውን መረጃዎች እያጣቀሱ በትግራይ የእርሻ ሰብል በዚህ ወቅት መድረስ የነበረበት ደረጃ ላይ አለመድረሱን ገልጸዋል።

በአንበጣ ወረርሽኝ ጉዳት የደረሰበት የትግራይ ግብርና በተከታዩ የምርት ዘመን ለውድቀት ሲዳረግ የሚያስከትለውን አደጋ ለአቶ እምነት መገመት ቀላል አይደለም። "እንደ ማሕበረሰብ የማሰብ አቅሙን ራሱ የሚፈታተን ይመስለኛል። ገበሬ ከእጅ ወደ አፍ ነው የሚኖረው። ፈጣሪውን እና ራሱን የሚያምን ማሕበረሰብ ነው ያለን። መሬቱ ላይ ያለው ምርት ራሱ ከፈጣሪ እጅ እንደሚሰጠው ነው የሚያውቀው" ያሉት አቶ እምነት "ያ ሲቀርበት የምግብ ዋስትናው ብቻ ሳይሆን እምነቱን ራሱ የሚፈታተን ነው" ሲሉ ሥጋታቸውን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ