1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት ድርድር ለምን ተደበቀ?  

እሑድ፣ የካቲት 6 2014

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር መጀመሩ ተሰምተዋል።  ሆኖም ከመንግሥት የተሰማ ማረጋገጫ ካለመኖሩም በላይ ጦርነቱ አሁንም አልቆመም። የመረጃው መደናገር ድግሞ ስጋት አጭሮአል። ይህን ሀገራዊ ጉዳይ ለሕዝብ ግልጽ ማድረጉ ጠቀሜታ የለውም ወይ? የመንግሥትና የህወሓት ድርድር ለምን ተደበቀ ?  

https://p.dw.com/p/46wjk
Addis Abeba Treffen Africa Union | Impressionen aus der Stadt
ምስል Seyoum Getu/DW

ዉይይት መጀመሩን የተመድ፤ የአፍሪቃ ህብረትና ሌሎችም የገለፁት ነዉ

የኢትዮጵያዉ ጠ/ሚ ዶ/ር  ዐቢይ አህመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ህግ ማስከበር ዘመቻ ያሉት ማብቃቱን በተለያየ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲናገሩ ቆይተዋል። ለጦር ሰራዊት መሪዎችም የምስጋና ሽልማት እና የከፍተኛ ጦር ሰራዊት ማዕረግን  ሰጥተዋል። ይሁንና  የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንዴ ጋም አንዴ ፋም እያለ እንደቀጠለ ነዉ። ህወሓት በአፋር ክልል እንደ አዲስ የጀመረዉ ጦርነት ሰዎች እየተገደሉ ነዉ። ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸውመፈናቀላቸው ፣ መኖርያ ቤቶች  እና  መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ከአፋር ክልል የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።  በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚደርሰዉ ዘር ተኮር ጥቃት አሰቃቂ ግድያ እና መፈናቀል ሌላዉ የኢትዮጵያ አሳዛኝ የየለት ዜና ሆኗል። በትግራይም የምግብ እና የህክምና መድሃኒት እጥረት፤ ህዝብ እየተሰቃየ መሆኑን ከስፍራዉ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።  በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት 35ኛውን የአፍርቃ ህብረት ጉባኤን በሰላም ማስተናገዷ አገሪቱን የተረጋጋችና ሰላምም የሰፍነባት አስመስሏታል።  ከሳምንታት በፊት የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል፤ ፓርቲያቸዉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተዘዋዋሪ እየተደራደረ መሆኑን እና «ዕመርታም እያሳየ» መሆኑን መናገራቸዉ ተሰምቶአል። የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰላም እንዲቋጭ፤ አሜሪካንን ጨምሮ የተመድና የአፍሪቃ ህብረት ናይሮቢ ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር መጀመሩን ገልፀዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ሰላም ለሚያመጣ ለየትኛዉም አማራጭ በሩ ክፍት እንደሆነ የገለፁት የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በተለይ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸዉ ከህወሓት ጋር ድርድር አልጀመረም። በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለአስራ አምስት ወራት ገደማ የዘለቀው ጦርነት በድርድር እልባት ሊገኝለት ነዉ የሚለዉ ተስፋ  ብዙዎችን ግራ እንዳጋባ ይገለፃል። ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ዉይስ ሰላምን ለማምጣት ድርድር ላይ ያለች አገር? የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገለፃል? ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የያዙት አቋምና እየወሰዱት ያለው እርምጃ አገሪቱን ወዴት ሊመራት ይችላል? ከዚህ ጦርነትና ውድመት መውጫው መንገድ ምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ በሚካሄደው ዉይይት ሃሳባቸዉን እንዲሰጡን የጋበዝናቸዉ: 

Äthiopien UN-Untergeneralsekretärin Amina Mohammed in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW
Äthiopien | Treffen Getachew Reda, Olusegun Obasanjo und Debretsion Gebremichael
ምስል Privat

ዶር / ደመላሽ መንግሥቱ በጅማ ዩንቨርስቲ የኮሚኒኬሽን እና የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ደጋፊ ፤ ዶ/ር አደም ካሴ አበበ- ዘሔግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ሰጪ ተቋም፣ የሕገ-መንግሥትና የዴሞክራሲ ግንባታ አጥኚና አማካሪ ፤ ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር  እንዲሁም   አቶ ገአዝ አህመድ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝደንት፤ ናቸዉ።   

ተወያዮች በዉይይቱ ላይ ሃሳባችሁን ለመስጠት በመቅረባችሁ አመስግናለሁ፤ በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የጥናት እና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ  አቶ ከድር መሐመድ በዚህ ዉይይት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነዉ ነበር ግን ስልካቸዉን አላነሱልንም። እንደማይሳተፉ ቢነግሩን ጥሩ ነበር።

ለ 15 ወራት ገድማ የዘለቀዉን ጦርነት ለማብቃ መፍትሄ ለማግኘት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ተጀምሯል የሚሉ ዜናዎች ተሰምተዋል።  ህወሃት በሦስተኛ ወገን በኩል ከመንግሥት ጋር የሚደረግ ድርድር መኖሩን ይገልጻል፤ የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ተመሳሳይ መረጃ መናገራቸው ተሰምቷል። ሆኖም ከመንግሥት በኩል የተሰማ ማረጋገጫ ካለመኖሩም በላይ አሁንም ጦርነቱ አልቆመም፤ የመረጃው መደናገር ሕዝቡ እየሆነ ያለውን ባለማወቁ ስጋት ላይ ጥሎታል። እንዲህ ያለውን አሳሳቢ ሀገራዊ ጉዳይ ለሕዝብ ግልጽ ማድረጉ ጠቀሜታ የለውም ወይ? 

ሰዎች ይፈናቀላሉ ይገደላሉ፤ ከተማ ይወድማል፤ በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢች ሰዎች እየተራቡ ነዉ እየሞቱ ነዉ ። በትግራi itህክምና መድሃኒት ችግር ከፍተኛ ችግር እንዳመጣም እየተነገር ነዉ። ጦርነት የተሳተፉ ብቻ ሳይሆን ንፁሃንም እየተራቡ እየተሰቃዩ ነዉ።  ይህን የሕዝብ ስቃይ ለማስቆም በሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት መካከል ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ?ከተፋላሚ ኃይሎች ምን ይጠበቃል? በበኩላቸው ሰላም ለማዉረድ ምን መደረግ አለባቸው? 

 

አዜብ ታደሰ