1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ የደኢህዴን ህልውና እያበቃለት ነውን?

እሑድ፣ ሐምሌ 21 2011

በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰውን ግጭት እና ኹከት ተከትሎ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ተከታታይ እርምጃዎችን ወስዷል። የደቡብ ክልል የጸጥታ ስራን በፌደራል ኮማንድ ፖስት እንዲመራ ማድረግ ከእርምጃዎቹ አንዱ ነው።

https://p.dw.com/p/3Mntr
Logo von SEPDM

ውይይት፦ የደኢህዴን ህልውና እያበቃለት ነውን?

በቀውስ ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ክልል ባለፉት ሳምንታት በርካታ ፖለቲካዊ ሁነቶችን አስተናግዷል። ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ወደ ግጭት እና ኹከት አምርቶ ለሰዎች ህይወት መቀጠፍ፣ ለንብረት ውድመት እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መታሰር ምክንያት ሆኗል።   

የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ክልሉን ለማረጋጋት ተከታታይ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ይገኛል። የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትላንት ሐሙስ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሲዳማ ዞን ለተከሰተው ችግር ድርሻ አላቸው ያላቸውን አመራሮች አግዷል። ተመሳሳይ የእግድ እርምጃም በሃዲያ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ላይ ወስዷል። ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዚሁ ውሳኔው ለወላይታ እና ከፋ ዞን አመራሮችም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

Äthiopien Stadtansicht Awassa
ምስል DW/S. Wegayehu

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል የሚነሱ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎችን መፍትሄ ለመስጠት ጥናት እንዲያደርግ የተቋቋመው ኮሚቴም የጥናቱን ግኝት በሳምንቱ አጋማሽ ይፋ አድርጓል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ግን ጥናት ሳይሆን በህገ መንግስቱ መሰረት "የክልል እንሁን" ጥያቄዎች ተግባራዊ እንዲደረግ ሲጠይቁ ሰንብተዋል። ከዚህ በኋላ በደቡብ ክልል ስር የመተዳደር ፍላጎት እንደሌላቸው ሲገልጹ የተደመጡት ሰልፈኞቹ ደኢህዴንም አምርረው ተቃውመዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ አስተዳዳሪዎችም የህዝቡን ስሜት ሲያስተጋቡ ታይተዋል። 

የሳምንታዊው "እንወያይ" መሰናዷችን ወቅታዊውን የደቡብ ክልል የፖለቲካ ትኩሳት፣ የክልሉን እና የደኢህዴንን ዕጣ ፈንታ አጠያይቋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በደቡብ ክልል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች የጻፉት ዶ/ር ተመስገን ቶማስ፣ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እና የመልካም አስተዳደር ጥናት ባለሙያ ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ እንደዚሁም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የላጋ የተባለው የወላይታ ማህበራዊ ንቅናቄ መስራች አቶ አሸናፊ ከበደ ናቸው። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ልደት አበበ