1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝነኛዋ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ

Sophie Mbugua
ሐሙስ፣ መጋቢት 10 2012

በጎርጎሪዮሳዊው 1940 በማዕከላዊ ኬንያ ንየሪ የተወለዱት ፕሮፌሰር ዋንጋሪ ማታይ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ እንዲሁም ግሪን ቤልት( አረንጓዴ መቀነት) የተባለው ንቅናቄ መስራች እና የ 2004 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3YnT1
DW African Roots | Wangari Maathai

የዋንጋሪ ማታይ የልጅነት ሕይወት እንዴት ነበር?

ዋንጋሪ ሙታ ማታይ በጎርጎሮሲያኑ 1940 ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደጋማ አካባቢ ቴቱ መንደር ተወለዱ፡፡ እሳቸውም በ 1960 ዎቹ በኬኔዲ ኤርሊፍት ነፃ የትምህርት መርሃግብር አማካይነት በዩናይትድ ስቴትስ ለመማር እድል ካገኙ 800 አፍሪቃውያን ወጣቶች አንዷ ናቸው።

ዋንጋሪ ማታይ ከሳይንስ ጥናታቸው ያገኙት ውጤት ምንድን ነው?

ማታይ በዩናይትድ ስቴትስ የባዮሎጂ ሳይንስ ተማሪ ነበሩ። ለመብት ጥያቄ ለመቆርቆር ተነሻሽነትንም ያገኙት እዛው ከነበረ የሲቪል መብቶች ንቅናቄ ነው። ማታይ ለቀጣይ ትምህርታቸው ወደ ኬንያ ተመልሰዋል ኃላም ወደ ጀርመን ተጉዘው ተምረዋል። እሳቸውም ከምስራቅ እና ከመካከለኛው አፍሪቃ የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው። በጎርጎሮሲያኑ 1976 ዋንጋሪ ማታይ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና አናቶሚ ዲፓርትመንት ሊቀመንበር ሆኑ እዛም የመጀመሪያዋ ሴት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው አገልግለዋል። 

DW African Roots | Wangari Maathai

የዋንጋሪ ማታይ የግሪን ቤልት ንቅናቄ እንዴት ተመሠረተ?

ማታይ ግሪን ቤልት ንቅናቄ (ጂ.ቢ.ኤም) ብለው የሰየሙት ንቅናቄ የተመሠረተው በጎርጎሮሲያኑ 1977 ዓ ም በኬንያ የሴቶች ብሔራዊ ምክር ቤት ድጋፍ አማካኝነት ነበር። አላማውም በኬንያ የገጠር ሴቶችን የኃይል እና የውሃ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የዛፍ ተከላ ንቅናቄ ነበር።
በአመታት ውስጥ የማታይ (ጂ.ቢ.ኤም) በኬንያ ከ 51 ሚሊዮን በላይ ዛፎችን ተክሏል ፡፡ ንቅናቄውም በብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰራ ትኩረቱን ያደረገው የአየር ንብረት ለውጥ እና ማህበረሰቡን በማጠናከር ላይ ነበር። በተለይም ሴቶች ዴሞክራሲያዊ ስፍራ እና ዘላቂ የሆነ ኑሮ እንዲኖራቸው በማጎልበት ላይ ይሰራ ነበር።


ዋንጋሪ ማታይ እንዴት የሰብዓዊ መብት ዘመቻ ያካሂዱ ነበር? 

ማታይ በኬንያ ውስጥ የመሬት መቀራመትን ለማስቆም ፣ የውሃ ማውጫ ቦታዎችን እና አረንጓዴ ቦታዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ባበረከቱት አስተዋፅዎ ይታወቃሉ። በ 1989 
ኬንያ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ስር በነበረችበት እና በፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሙአይ መምትመራበት ወቅት ማታይ የኬንያ ታይምስ ሚዲያ ትረስት ቢዝነዝ የተባለው ባለ 60 ፎቅ የንግድ ማዕከል እንዳይገነባ ዘመቻ አካሂደዋል። ህንፃው ሊገነባ የነበረው ኡሁሩ ፓርክ በመባል በሚታወቀው ባለ 13 ሄክታር (130,000 ካሬ ሜትር) የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ አጠገብ ነበር። 
ከአስር ዓመት ገደማ በኋላ ማታይ ከ 1932 አንስቶ በከተማዋ የሚገኘውን ሰው ሰራሽ የካሩራ ደን ለመያዝ ከሞከሩ ሙሰኛ ሰዎች ጋርም ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር። በ 2005 የወጣ አንድ የኬንያ ዘገባ እንደሚጠቁመው 1,041 ሄክታር ስፋት የነበረው ይኼው የደን ስፍራ በሕገ-ወጥ የልማት ፕሮጀክት ሳቢያ ወደ 564 ሄክታር ቀንሷል ፡፡ ዋንጋሪ ማታይ በአገራቸው የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲዘረጋ በትጋት የታገሉ ሰውም ናቸው። የመድብለ ፓርቲዎች ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደበት በጎርጎሮሲያኑ 1992 አመተ ምህረትም ማታይ ናይሮቢ ውስጥ በኡሁሩ ፓርክ የረሃብ አድማ ያደረጉ እናቶች የቡድን መሪ ነበሩ። ሴቶቹ እና የፖለቲካ እስረኞች ይለቀቁ በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ የመብት ተሟጋቾች ቡድን በአንድነት በፖለቲካ ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረው የሚገኙ ልጆቻቸው እንዲለቀቁ ጠይቀዋል ፡፡ የፀጥታ ኃይላት ተቃውሞውን ለመበተን በሞከረበት ጊዜም ሴቶቹ አልባሳታቸውን እያወለቁ ራቁታቸውን ተቀምጠዋል። ይህ ተቃውሞም ለ 11 ወራት ያህል ዘልቋል ፡፡ ከዚያ በኋላ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ፈታና ከእስር ነፃ አደረገ ፡፡ ያንን ክስተት ለማስታወስም ተቃውሞው የተካሄደበት የኡሁሩ ፓርክ ስፍራ የነፃነት ማእዘን ጥግ ተብሎ ይጠራል። 
የሀገሪቱ የብዝሃ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስርዓት መገንባት ከተጀመረ በኋላ በማታይ የሚመራው የአረንጓዴ ቤልት ንቅናቄ ህብረተሰቡን በመልካም አስተዳደር ላይ በማስተማር ፣ ሰላምን በማስጠበቅ እና አከባቢን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ፡፡

ዝነኛዋ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ

ማታይ ዋንጋሪ ላበለከቱት አስተዋፅዎ ምን አይነት እውቅና አገኙ?

ዋንጋሪ ማታይ ላከናወኗቸው ግሩም አስተዋፅዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሽልማቶች አግኝተዋል።  ከእነዚህም መካከል የ ራይት ላይቭሊውድ ሽልማት፣ የኢንዲራ ጋንዲ የአካባቢ ጥበቃ የወርቅ ሽልማት ፣ እና የፈረንሣይ የክብር ሽልማት ይገኙበታል።  በጎርጎሮሲያኑ 2005 አሥራ አንድ የኮንጎ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለኮንጎ ደን ሥነ-ምህዳር በጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው ሾሞዋቸዋል። 
ከፍተኛው ሽልማት ደግሞ የተበረከተላቸው በ 2004 የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ በኬንያ እና በአፍሪቃ ዘላቂ ልማት ፣ ዴሞክራሲ እና ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋፅኦ በሚል የሰጣቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት ነው።

ዋንጋሪ ማታይ ከተናገሯቸው ጥቅሶች መካከል በጥቂቱ

« ኃላ ላይ ዋጋ የሚከፍለው አካባቢን የሚያጠፋው  ትውልድ አይደለም ፡፡ ችግሩ ይህ ነው ፡፡»

«የሰብአዊ መብቶች ሰዎች እንዲደሰቱባቸው ጠረጴዛው ላይ የተቀመጡ አይደሉም ፡፡ 
እነዚህ የምትታገሉላቸው ከዛም የምትንከባከቧቸው ነገሮች ናቸው። »

«ዛሬ በአስተሳሰባችን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቅ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሞናል ። ይህም የሰው ልጅ ለህይወቱ ድጋፍ የሆነውን ተፈጥሮ እንዳያበላሽ ነው። ምድራችን ቁስሏን እንድታድን እና መልሶ የራሳችን ቁስል እንዲድን ጥሪ አለብን። ለዚህም ፍጥረታት ያላቸውን ልዩነቶች እና ውበትን ጠብቀን ማቆየት አለብን። ዘላቂ ልማት ፣ ዴሞክራሲ እና ሰላም ከዚህ የማይነጠል መሆኑን የምንገነዘብበት ሰዓት አሁን ነው።»

"ብቻ መስራት የማይቻል መሆኑን ተረድቻለሁ። የቡድን ስራ ነው። ምክንያቱም አንድ የሌለን ቀን የሚሰራልን ሰው አይኖርምና።»

DW African Roots | Wangari Maathai

ዋንጋሪ ማታይ እንዴት ይታወሳሉ?

ዋንጋሪ ማታይ የማህፀን ካንሰር ትግላቸውን በ 71 ዓመታቸው ተሸንፈው በጎርጎሮሲያኑ መስከረም 25 ቀን 2011 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በ 2012 የአፍሪካ ህብረት መጋቢት 3 ቀንን የዋንጋሪ ማታይ ቀን ሲል ሰይሟል። ዕለቱ የሚታወሰው ከአፍሪቃ የአካባቢ ጥበቃ ቀን ጋር ተያይዞ ነው ፡፡

 በ 2016 የናይሮቢ ከተማ መስተዳድር የዱር ጎዳና የተሰኘውን የመንገድ ስም በፕሮፌሰር ዋንጋሪ ማታይ ተክቷል።

የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ተቋም (WMI) የተቋቋመው የፕሮፌሰር ዋንጋሪ ስራዎችን እውቅና ለመስጠት፣ ለማክበር እና ቀጥሎ ለማቆየት ነው ፡፡

ዋንጋሪ ማታይ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው