1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ኮሮናን እንዴት እንከላከል ከሌሎችስ ምን ልምድን እንዉሰድ? 

እሑድ፣ ሚያዝያ 4 2012

«የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመቀነስ ይህን ያህል ሚና ይጫወታል ብለን መዘርዘር ባንችልም፤ አደጋዉን ለመቀነስ ሚና እንዳለዉ እሙን ነዉ። በኤች አይቪ ላይ የሰራነዉ ስህተት የኮሮና ላይ ልንደግም አይገባም። የፖለቲካ ልዩነት የሚነሳበት ጊዜ አይደለም። ሁሉም በጥምረት በጋራ የሚሰራበት ጊዜ ነዉ» ተወያዮች ያነስዋቸዉ ነጥቦች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/3anlR
Äthiopien Coronavirus
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ኮሮና በሌሎች በሃገራት ሲዛመት ጥንቃቄ ለማድረግ እድሉን አልተጠቀምንም

የጎርጎረሳዉያን 2019 ዓመት መጨረሻ ታኅሳስ ወር በቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ የጀመረዉ የኮሮና ተኅዋሲ በአሁኑ ወቅት የዓለም ሃገራትን አዳርሶአል፤ በተኅዋሲዉ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ሞትዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ደግሞ በተኅዋሲዉ ተይዞአል። ያም ሆኖ ለተኅዋሲዉ ማርከሻ የሚሆን መድሐኒትም ይሁን መከላከያ ክትባት አልተገኘም። በመሆኑም መፍትሄዉ ጥንቃቄ ብቻ ነዉ።  የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን  ለመግታት የዓለም ሃገራት መንግሥታት በየሃገሮቻቸዉ የተለያዩ የጥንቃቄ ድንጋጌዎችን እያሳለፉ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሮና ሥርጭትን ለመግታት፣ ለአምስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን አስታዉቋል። በኢትዮጵያ  ኅብረተሰቡ በተኅዋሲዉ እንዳይያዝ ነባሩን ማኅበራዊ ትስስር እንዲገታ ለማድረግ የሚደረገዉ ሙከራም ከባድ ሲሆን ታይቶአል። የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገሮች ምን ልምድን ትዉሰድ?  የኮሮና  ጥንቃቄ እና መፍትሄዉ እንዴት ሊተገበር ይገባል?  

በዉይይቱ የተሳተፉት:- 

ዶ/ር መሳይ ገብረማርያም፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በስኩል ኦፍ ሶሻል ዎርክ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁር  

መስከረም አበራ በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች በመምህርነት ያገለገሉ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ፤ አምደኛ፤ 

ጋዜጠኛ ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ የዶቼ ቬለ የሀዋሳ ወኪል እንዲሁም በአዉሮጳ ኅብረት መቀመጫ በብራስልስ ቤልጂየም የሚገኘዉ የዶቼ ቬለ ተወካይ ጋዜጠኛ ገበያዉ ንጉዜ ናቸዉ። 

ተወያዮች ካነስዋቸዉ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል:-

«የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመቀነስ ይህን ያህል ሚና ይጫወታል ብለን መዘርዘር ባንችልም፤ አደጋዉን ለመቀነስ ግን ሚና እንዳለዉ እሙን ነዉ። በሃገሪቱ ዉኃ በወረፋ የሚታደልበት አሰራር በመኖሩ የንጽሕና መጠበቅያ ዉኃ እጥረት ቢኖር እንኳ ንክኪን መቀነስ አካላዊ ቅርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል።»

«የኮሮና ተኅዋሲ አደገኝነነት ለጥቁር አልያም ለአፍሪቃ አደጋ የለዉም በሚል በተሳሳተ መረጃ ችላ ተብሎ ነበር። ነገር ግን ሃገሪቱ ላይ የመጀመርያዉ የኮሮና ተኅዋሲ ታማሚ ከተገኘ በኋላ ጉዳዩ አጽኖት ተሰጥቶት ጥንቃቄ ለማድረግ እየተሞከተረ ነዉ። »
« የኮሮና ተኅዋሲ በመጀመርያ በኢትዮጵያ ሳይሆን በሌሎች ሃገሮች ተዛምቶ መረጃዉ እኛ ጋር ቢደርስም በቅድምያ ጥንቃቄ ለማድረግ እድሉን አልተጠቀምንም። ለዚህ ምክንያቱ የኅብረተሰቡ አንድ ላይ የመኖር ባህላዊ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ወይም ኅብረተሰቡ ላይ ያለዉን የባህሪ ለዉጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ይሆናል።»
«ኮሮና ተኅዋሲ ኅብረተሰቡ ዉስጥ ስነ- ልቦናዊ ጫና ፈጥሮአል። » « ኮሮና ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ የተከሰተ ከባድ ቀዉስ ነዉ። እንዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዝብን የሚያፈናቀል እንዲህ ፍርሃት ዉስጥ የሚከት ሁኔታ ታይቶ አይታወቅም። ኮሮና ማንንም ሰዉን የማይለይ ሁሉንም የሚያጠቃ ወርሺኝ በመሆኑ የዓለም ሕዝብ አሁን የአኗኗሩንም ሆነ የሳይንስ ምርምሩን ዳግም እየፈተሸ ነዉ» « ተኅዋሲዉን ተከትሎ ኢትዮጵያዉ ዉስጥ ስጋት ነግሶአል። ማኅበራዊ ትስስር በጎላበት በኢትዮጵያ ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገዉ ጥረት ከባድ አድርጎታል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ጀምሮ የተለያዩ ሚኒስትሮች ኅብረተሰቡን ስለኮሮና ጥንቃቄ ንቃትና ትምህርት ለማድረግ ሲጥሩ ይታያል። ነገር ግን ይህ ተግባራዊ እንዳይሆን ከእጅ ወድአፍ በሆነ ሆኑኃ የሚኖረዉ ሕዝብ ሁኔታ ጥረታቸዉን ከባድ ሲያደርግባቸዉ ታይቶአል» « በአካባብያችን ያሉ የተቸገሩ ሰዎችን ችግር መካፈል ብንችል የተኅዋሲዉን ስርጭት ለማለዘብ በሚደረገዉ ጥረት ጠቃሚ ስራ ይሆናል።» «በመንግሥት ረገድ የትራንስፖርት አጠቃቀምን በተመለከተ የወጣዉ ደንብ የሕዝቡን እና የትራንስፖርት አቅሙን የሚመጥን ስላልሆነ ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝቡ የወጣዉን ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ችግር ዉስጥ ከቶታል። ስለሆነም ሁሉም የተጣለዉን ቢያደርግ ችግሩን መወጣት እንችላለን።»
«የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተኅዋሲዉን ስርጭት ለመቀነስ ይህን ያህል ሚና ይጫወታል ብለን መዘርዘር ባንችልም፤ አደጋዉን ለመቀነስ ግን ሚና እንዳለዉ እሙን ነዉ። በሃገሪቱ ዉኃ በወረፋ የሚታደልበት አሰራር በመኖሩ የንጽሕና መጠበቅያ ዉኃ እጥረት ቢኖር እንኳ ንክኪን መቀነስ አካላዊ ቅርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል።»
« በአፍሪቃ የኮሮና ተኅዋሲ መዛመት ታሪክ ሲታይ፤ አብዛኛዉን የሚታየዉ በከተሞች ላይ ነዉ። ይህ የሆነዉ በአፍሪቃ ዋና ከተሞች ከአዉሮጳ አልያም ከሌላ ክፍለዓለማት ከተኅዋሲዉ ጋር ንኪኪ ያላቸዉ ተጓዦች ስለሚገቡ ነዉ። ኢትዮጵያ ላይ ያለዉን ሁኔታ ስንወስድ አዲስ አበባ ላይ ይህ ይታያል። በሌላ በኩል ከተማ ዉስጥ የሚኖረዉ ሕዝብ ቁጥር በጣም ከፍተኛ እና ተጠጋግቶ የሚኖር በመሆኑ ነዉ። የተኅዋሲዉን መዛመት ስናጤን አዲስ አበባ ከሌሎች ከተሞች ጋር ያ,ለዉን መስተጋብርም ማጤን ይኖርብናል። ብዙ ክልሎች ድንበራቸዉን ዘግተዉ መዉጣት መግባት አይቻልም። ግን አሁንም ይህ ጉዳይ ሊጤን ይገባል ወደ አዲስ አበባ እንደልብ መዉጣት መግባት ይቻላል። ክልሎችም ዘጉ ሲባል እንዴት መሆኑ ሊጣራ ይገባል። ግልፅ የሆነ አሰራር የለም። ምርመራስ ይካሄዳል ወይ ብለን ልንጠይቅ ይገባል። የአዲስ አበባ ሁኔታ በደንብ ሊጤንበት ይገባል»
« ሌላዉ በኮሮና ተኅዋሲ የተያዘዉ ቁጥር ተብሎ መግለጫ አልያም መረጃ ሲወጣ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል የሚወጣዉ መረጃ ትክክለኛ አይደለም። ስንት ሰዉ ተመርምሮ ስንት ሰዉ ተገኘበት ብሎን ልንጠይቅ ይገባል። በሃገሪቱ ዉስጥ ኮሮናን ለመርመር ያለዉ አቅም እጅግ ጥቂት ነዉ። ስለዚህም መረጃ ስንሰጥ ከዚህ ሰዉ መካከል ይህን ያህል ተመርምሮ ይህን ያህል በተህዋሲዉ ተይዞ ተገኘ ብለን ግልፅ ልናደርግ ይገባል። በመረጃዉ ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ተብሎ በአጽሕኖት ሊነገር ይገባል።»
የምዕራቡን ሃገራት ያየን እንደሆነ አዉሮጳም አሜሪካም የሚገኙ ፖለቲከኞች ከአክራሪ እስከ ቀኝ አልያም መሃል ሰፋሪዉ ፖለቲከኛ ሁሉ አንድ ላይ ቆሞ የጤና ምሁራንን ምክር እየሰማ ኮሮናን ለመታገል አንድ ላይ መቆሙ ታይቶአል። በዚህ ወቅት ምንም አይነት የፖለቲካ ልዩነት የሚታይበት መድረክ ሊኖር አይገባም። የፖለቲካ ልዩነት የሚነሳበት ጊዜም አይደለም። »
« የኮረና ተኅዋሲ ወረርሺኝ የዓለምን የጤና ፖሊስ የጤና መርህ ያጋለጠበትም አጋጣሚ ነዉ። የሃገራት ፖለቲከኞችም ሆኑ የጤና ባለሞያዎች በጤና ፖሊስያችን እንዴት እናስተካክል፤ በተለይ የወረርሽኝ ሕክምናን እንዴት እናቃል ብለዉ ዳግም መርሃቸዉን የሚፈትሹበት ይሆናል። » « ኮሮና የተባለ ድንገተኛ በዓለም ሕዝብ ላይ የመጣዉን ጦርነት ለመከላከል በአንድ ላይ የምሁራንን ምክር መስማት አካላዊ ርቀትን እና ንጽህናን መጠበቅ አስ,ፈላጊ ነዉ።» «በሌላ በኩል በተለይ በአፍሪቃ የኮሮና መፈወሻ መድሃኒት ናቸዉ ተብሎ እየተራገፉ ናቸዉና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ከሃሰ,ኛ መረጃዎች መራቅ ይኖርብናል። ተኅዋሲዉን ማርከሻም ሆነ መከላከያ መድሃኒትም ሆነ ክትባት እስካሁን አልተገኘም። ትክክለኛ መረጃዎችን ከምሁራኖቻችን እና ከጤና ባለሞያዎች እንስማ።»

በዉይይቱ የተሰታፉትን በማመስገን ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመቻ ማይቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን! 

አዜብ ታደሰ