1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ ጦርነት ሒደትና ሰላም

እሑድ፣ ኅዳር 26 2014

መንግስት ድሉን ለማጠናከር፣ ሕወሓት ጦርነቱን ባጭር ጊዜ ለመቋጨት ከመዘጋጀት ባለፍ ሰላም የማዉረድ ጭላንጭል አላሳዩም።ጦርቱ አምና ጥቅምት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ወገኖች ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያ አቁመዉ እንዲደራደሩ፣ ለችግረኞች ርዳታ እንዲደርስ፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር ያደረጉት ጥሪ፣ ጥረትና ሙከራ እስካሁን ያስገኘዉ ዉጤት የለም።

https://p.dw.com/p/43oj3
Äthiopien Spezialeinheiten der Armee und Milizen in der Region Afar
ምስል Seyoum Getu/DW

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ ጦርነትና የሰላም አማራጭ

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የገጠሙት ጦርነት የኃይል ሚዛን እየተቀያየረበት፣ነገር ግን የኢትዮጵያዊ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት እያወደመ፣ የዉጪ ኃይላትን ትኩረት እንደሳበ ቀጥሏል።ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት፣የአፋርና የአማራ ኃይላት ጭፍራን፣ ጋሸናንና ላሊበላን የመሳሰሉ ሥልታዊና ታሪካዊ ከተሞችን ጨምሮ ሕወሓትና ተባባሪዎቻቸዉ ይቆጣጠሯቸዉ የነበሩ በርካታ አካባቢዎችን መልሰዉ ተቆጣጥረዋል።

እስካለፈዉ ኃሙስ ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ድል ያስመዘገበዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርና ተባባሪዎቹ ደሴንና ኮምቦልቻን የመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞችን ባጭር ጊዜ ዉስጥ ከሕወሓት እጅ እንደሚማርኩ እያስታወቁ፣ ለአዳዲስ ዉጊያ እየተዘጋጁ ነዉ።

ዉጊያዉን በግንባር ተገኝተዉ የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ሐሙስ በሰጡት መግለጫ ጦራቸዉ ድል ማስመዝገቡን እንደሚቀጥል አስታዉቀዋል።

ሕወሓት ባንጻሩ ሽንፈት እንደገጠመዉ ቃል በቃል ባያምንም «ስልታዊ ማፈግፈግ» ማድረጉን አምኗል።ይሁንና «የትግራይ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ» የተባለዉ ኃይል አወጣዉ የተባለዉ መግለጫ ሕወሓት የስልት ለዉጥ ያደረገዉ «ጦርነቱን ባጭር ጊዜ በበላይነት ለመቋጨት ነዉ።

መንግስት ድሉን ለማጠናከር፣ ሕወሓት ጦርነቱን ባጭር ጊዜ ለመቋጨት ከመዘጋጀት ባለፍ ሰላም የማዉረድ ጭላንጭል አላሳዩም።ጦርቱ አምና ጥቅምት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የዉጪ ኃይላት በተለይም የአፍሪቃ ሕብረት፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዩናይትድ ስቴትስ ተፋላሚ ኃይላት ዉጊያ አቁመዉ እንዲደራደሩ፣ ለችግረኞች ርዳታ እንዲደርስ፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር ያደረጉት ጥሪ፣ ጥረትና ሙከራ እስካሁን ያስገኘዉ ዉጤት የለም።

Äthiopien | Binnenvertriebene
ምስል Privat

ከሐገር ዉስጥም ከዉጪም ጥቂት ኢትዮያዉያን ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቆም፣ተፋላሚ ኃይላት በሙሉ እንዲደራደሩና ሁሉንም የፖለቲካ ኃይል ያሰባሰበ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አላገኘም።እንዲያዉም ጥያቄዉን ካቀረቡት አንዳዶቹ በመንግስት፣ በሕወሓትና በየደጋፊዎቻቸዉ እየተወገዙና እየተወቀሱ ነዉ።

በነገራችን ላይ የሰላም ድምፅ የሚያሰማ፣ ጋዜጠኛ ይሆን ፖለቲከኛ፣ የመብት ተሟጋች ይሆን ተንታኝ ወይም አቀንቃኝ የዚሕ ወይም የዚያኛዉ ወገን እየተባለ ሲዘለፍ፣ ሲወገዝ፣ ሲገለል ማየትና መስማት ከጀመርን ዓመት ዓለፈን።

ይህን የሚያዉቁ  አንዳድ የዉጪ ጋዜጠኞችና ተንታኞች «ኢትዮጵያዉያን ሰላም አይወዱ ይሆን?» የሚል ጥርጣሬ የተላበሰ ጥያቄ ሲሰነዝሩ እየሰማን ነዉ።

ኢትዮዉያን ለመጠፋፋት ሲሰላለፉና ሲዘላለፉ የርስ በርስ ጦርነትና እልቂትን በየሐገራቸዉ የሚያዉቁት፣ የሰላም ኖቤል ተሸላሚዎቹ የቀድሞ የላቤሪያና የኮሎምቢያ ፕሬዝደንቶች፣ እና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ-ሙን የሚገኙበት የሽማግሌዎች ቡድን የኢትዮጵያዉ ጦርነት እንዲቆም ሰሞኑን ጠይቀዋል።

የጦርነቱ ሒደት፣የሰላሙ አማራጭና ዉጤቱ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ሶስት እንግዶች አሉን።

ነጋሽ መሐመድ