1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የሽብርተኝነት ፍረጃዉ መፍትሄ ወይስ አግላይ?

እሑድ፣ ግንቦት 1 2013

«የመንግሥት መዋቅሮችን እያፈረሱ፤ እየገደሉ እያፈናቀሉ ሃገሪቱን ወደማፍረስ የሄዱት ትጥቅ ያልፈታዉ ሸኔና ህወሃት ናቸዉ። ግድያን የጀመሩት ከባለስልጣናት ነዉ። መንግሥት ለዉይይት ዛሬም በሩ ክፍት ነዉ» «ከዚህ በፊት መንግሥት የማይወዳቸዉን ቡድኖች ከፖለቲካዉ መድረክ ለማግለል አሸባሪ ይል ነበር። ትክክል አይደለም ብለናል፤ ዛሬም እንላለን»

https://p.dw.com/p/3t9lT
Äthiopien Logo Parlament  FDRE

እንወያይ፤ የሽብርተኝነት ፍረጃዉ መፍትሄ ወይስ አግላይ?

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀመዉ ግድያ እና መፈናቀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉ የተለያዩ አካላት መንግሥትን እየወቀሱ ነው። በትግራይ የሚታየዉ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ  እንዳሳሰባቸዉም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መግለጫ እየሰጡ ነዉ። በሃገሪቱ የሚደርሱ የመብት ጥሰትና ግድያ እንዲሁም መፈናቀልን በሃገር ዉስጥ ያሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም አዉግዘዋል ስጋታቸዉንም ገልፀዋል። ሆኖም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እስካሁን ይፋ የሚያደርጓቸው ማስጠንቀቅያዎች ከወረቀት ያለፈ ምንም አይነት መፍትሄን ያስገኘም አይመስልም። የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግድያና መፈናቀል በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ጥሰት ተጠያቂ ያደረጋቸውን  “ህወሓት” እና “ሸኔ” የተባለዉን ቡድን ሽብርተኛ ሲል ፈርጆአል። የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች በሽብርተኝነት መሰየም በሃገሪቱ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል ለማስቆም መፍትሄ ይሆን ይሆን? ውሳኔውስ ኢትዮጵያ ከምትከለው የለውጥ ጉዞ ጋር አብሮ ይሄዳል? የዛሬ የምንወያይባቸዉ አንኳር ነጥቦች ናቸው።

በዚህ ነጥቦች ላይ እንዲወያዩ የጋበዝናቸዉ ፦

አቶ ኃይሉ አዱኛ ፤ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ / ቤት የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ፤ ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ፓርቲከፍተና አመራር፤ ዶ/ር አወል አሎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ብብሪታንያ ኬል ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር፤ እንዲሁም በፈቃዱ ኃይሉ በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ የፖለቲካ ተንታን። 

ተወያዩች ካነስዋቸዉ ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

« ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነዉ»

«የመንግሥት መዋቅሮችን እያፈረሰ፤ እየገደለ እያፈናቀለ ሃገሪቱን ወደማፍረስ የሄደዉ ትጥቅ ያልፈታዉ የሸኔ ቡድን እና ህወሃት ናቸዉ»

« ከዚህ በፊት የነበረዉ መንግሥት አንዳንድ የማይወዳቸዉን ቡድኖች ከፖለቲካዉ መድረክ ለማዉጣት አልያም ለማግለል አሸባሪ እያለ ይጠቀምበት የነበረዉን አካሄድ ትናንት ትክክል አይደለም ብዬ እንደማስበዉ ዛሬም ትክክል አይደለም እላለሁ»

«አንዳንድ ሃሳባቸዉን የማንወዳቸዉ ሃይሎች ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት፤ ሃሳብ ያላቸዉ ቡድኖች ወይም ብዙ ተከታይ ያላቸዉ ግለሰቦች ወደ ዉይይት ጠረቤዛ ዉይይት መጀመራቸዉ ነዉ። ህወሓትንም ጨምሮ»

« የተወሰኑ ቡድኖችን ብቻ ይዞ፤ የተወሰኑትን አግልሎ፤ ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄ አይመጣም»

«ኢትዮጵያ ዉስጥ ሽብርተኝነት መኖሩ የተረጋገጠ ነዉ። ዜጎች በየቀኑ ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ፤ ንብረታቸዉ ይወድማል፤ ማንነታቸዉን መሰረት ያደረገ ጥቃት በማናዉቀዉ ሁኔታ ይፈፀምባቸዋል»

« አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚታየዉ ሁኔታ ጋር ሽብርተኛ ብሎ መፈረጅ ምን ይጠቅማል? ታጣቂዎቹ ጥቃት የሚፈፅሙት አንዳንዴም በመንግሥት መዋቅር እየታገዙ፤ ሕዝብ ሁሉ እያወቃቸዉ፤ መንግሥት ማድረግ የሚገባዉን ባለማድረጉ ግድያ ሲፈፅሙ እንደቆዩ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ»

« ታጣቂዎቹ በመንግሥት ታግዘዉ፤ አልያም መዋቅር ስር ነዉ ጥቃት የፈፀሙት፤ የሚለዉ ነገር፤ ሊታረም ይገባል። ይህን የምንልበት ምንም አይነት ማረጋገጫ የለንም»

« ኢትዮጵያ ዉስጥ ሽብር የሚፈፅሙት ቡድኖች፤ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት፤ መንግሥት ስራዉን ባለመስራቱ፤ ሆደ ሰፊ እንሁን እየተባለ፤ ነገሩን ችላ በማለቱ፤ ትጥቅ የያዙ ቡድኖች ትጥቅ አልፈታም አሉ እያለ በማለቱ እና ነገሩን ችላ በማለቱ ነዉ»

«መንግሥት ሃገሪቱ ዉስጥ ሚፈፀመዉን ግድያ ሲያወግዝ፤ አልሰማንም አላየንም»

«የሽብርተኝነት ፍረጃዉ መንግሥት ለራሱን ስልጣን እንጂ ለዜጎች ደህንነት አለመሆኑ የታየበት ዉሳኔ ነዉ»  

«መንግሥት እስከዛሬ በሃገሪቱ ዉስጥ እያሸበሩ ያሉ ታጣቂዎችን፤ ሽብርተኛ ስላላለ አይደለም ድርጊታቸዉን ማስቆም ያልቻለዉ። ይልቁንም እርስ በርስ ተግባብቶ ዉሳኔዉን ወደ መሪት ማዉረድ ስላልቻለ ብቻ ነዉ። በባለስልጣናት መካከል ከፍተኛ አመግባባት እናዳለ፤ እራሳቸዉ  ባለስልጣናቱ በማኅበራዊ መገናኛ ላይ የሚጽፉት የተጣረሰ ሃሳብ ይሄንን በግልፅ የሚያሳይ ነዉ»

« ዛሬ መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ በመፈረጁ በሃገሪቱ የሚደርሰዉን የመብት ጥሰት እና ጉዳት ሊያስቆም ይችላል ማለትም አይደለም»

«በርግጥ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚታየዉ የመብት ጥሰት እና አሰቃቂ ግድያ ተጠያቂዎቹ በሽብርተኝነት የተፈረጁት ቡድኖች ናቸዉ? ጥርጣሬ አለን። ይህን የሽብር ጥቃት በርግጥ ማን እያደረሰ እንደሆን በርግጠኝነት መናገር አይቻልም»

« ቀደም ሲል መንግስት ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት ብዙ ጥረት አድርጎአል። ይህ ቡድን ግን ግድያን የጀመረዉ ከመንግሥት ባለስልጣናት ነዉ። እስካሁን ከ 100 በላይ ከተለያዩ ቦታዎች ባለስልጣናት ተገድለዋል»

« መንግሥት ከተለያዩ አካላት ጋር ዉይይት ለማድረግ አሁንም በሩ ክፍት ነዉ። ይህ ሲሆን ምርጫ ይካሄዳል፤ ጎን ለጎን ሰላም ለማምጣት ዉይይቶች ይካሄዳሉ፤ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ነዉ»

« ከምንግዚዉም በላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን በተሻለ ደረጃ ላይ ነዉ። የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከምንጊዜዉም በላይ በተሻለ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል።

« በሃገሪቱ ከሚካሄዱት የተለያዩ የፖለቲካ ሂደቶች ማለትም ምርጫን የመሳሰሉ ጉዳዮች እያስፈፀምን፤ ከስር ጀምረን ዉይይቶችን ማካሄድ ይኖርብናል።»   

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ አስተያየቶንም ያስቀምጡልን!

 

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ