1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የሴቶቹ ሹመት ለተጀመረዉ ለዉጥ ተስፋ?

እሑድ፣ ጥቅምት 25 2011

የታህድሶ ለዉጥ አራማጅ የሚባሉት የኢትዮጵያዉ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያለዉን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ተጨባጭ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ ምናልባትም በአፍሪቃ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ሴት የካቢኔ አባላት ቁጥርን ከፍ በማድረጋቸዉ የዓለምን ቀልብ ስበዋል።

https://p.dw.com/p/37cUg
Wenshet Molla, Yetnebersh Nigussie, Tsedale Lemma

ኢትዮጵያ ላይ የታየዉ የንጋት ጎህ እንዲቀደድ በጋራ መስራት አለብን

የሴቶች በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ ያላቸዉን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላቅ እንዲል የተመድን የመሳሰሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም  ግለሰቦች  መከራከር ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል። ሴቶች ልጅ ከማሳደግ  ወይም ትዉልድ እንዲቀጥል ከማድረግ ጀምሮ በማኅበረሰቡ ዉስጥ ከሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና በተጨማሪ የአንድን ሀገር የኤኮኖሚ ልማት፣ ሰላምና ደኅንነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸዉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህም ይመስላል በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢዉ የሚነሱ ግጭቶችን እንዲቆሙ ለማድረግ ሴቶች ያላቸዉ አስተዋፅኦ ትልቅ ሥፍራ እየተሰጠዉ የሚገኘዉ። ይህን ዓለማቀፍ መልክ ያለዉን የሴቶችን እኩልነትና ተሳትፎ የሚያጠናክር እንቅስቃሴን ገቢር ለማድረግ የተለያዩ ሃገሮች መንግሥታት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ። ምንም እንኳ እስካሁን የተወሰዱት ርምጃዎች እና የተወጠኑት እቅዶች የታሰበዉን ያህል ዉጤት ባያመጡም ጥረቱና ዉጥኑ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። በኅብረተሰቡ ዉስጥ ሴቶች በአብዛኛዉ ከፍተኛ ቁጥር ስላላቸዉ፤ መንግሥታት ወይም ድርጅቶች በየመስኩ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሙከራዎችን ያደርጋሉ። በቅርቡ ሥልጣን የያዙትና የታህድሶ ለዉጥ አራማጅ የሚባሉት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድም ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያለዉን የሴቶችን ተሳትፎ የማሳደግ መርህ ተግባር ላይ ለማዋል ተጨባጭ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ ምናልባትም በአፍሪቃ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ሴት የካቢኔ አባላት ቁጥርን ከፍ አድርገዋል። የዐብይ መንግሥት የሃገሪቱን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ለሴት አድርጎ ታዋቂዋን ዲፕሎማት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አድርጎዉ ሾመዋል። ጠ/ሚ ዐብይ ሕግን ፍትህን በተመለከተ ፈራንክፈርት ላይ ጠቆም ያደረጉትን ተግብረዋል። ይኸዉም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አድርገዉ አንዲት ሴትን በመሾማቸዉ የበርካቶችን ይሁንታ ተቸረዋል። ይሁንና አሁንም ለሴቶች እኩልነት የሚታገሉ ወገኖች የሴቶችን ሹመት ቢደግፉትም ሌሎች ወገኖች ግን ተቃዉሞ እና ትችት መሰንዘራቸዉ አልቀረም። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ያዋቀሩት ካቢኔ ለሴቶች ሥልጣን በመስጠት ስም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራር ሊፈትኑና ሊፎካከሩ የሚችሉ ባለሞያዎችን ከስልጣን ለማራቅ ያለመ ነዉ ብዙዎቹ ተሽዋሚዎች ሴቶች መሆናቸዉ ብቻ ሳይሆን በልምድም ሆነ በትምህርት የተመደቡበትን ሥፍራ ሊመጥኑ የማይችሉ ናቸዉ በማለት ይወቅሳሉ። ስለዚህ ሹመቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትዕዛዝ ብቻ የሚቀበሉ ሰዎችን ያሰባሰበ ነዉ ባዮች ናቸዉ። በዚህ ዉይይታችን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ መንግሥት አዲስ ባዋቀረዉ ካቢኔ ላይ የተነሱ እነዚህን ጥያቄዎች በአጭሩ ለመቃኘት ይሞክራል። በዚህ ዉይይት እንዲሳተፉልን የጋበዝነዉ ሴቶችን ብቻ ነዉ። በዉይይቱ ላይ፤ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ የአማራጭ ኖቤል ተሸላሚና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች፤  ወ/ት ወይንሸት ሞላ፤ የፖለቲካ ምሁር እንዲሁም ወ/ሮ ፀዳለ ለማ ጋዜጠኛ እና የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ናቸዉ። ተወያዮችን የ«DW» ግብዣን ተቀብለዉ በዉይይቱ ተሳታፊ ስለሆኑ እያመሰገንንn፤ ሙሉ ዉይይቱን እንድኃደምጡና አስተያየታችሁን እንድትሰጡን እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ