1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ ኢህአዴግ፤ ወደ ዉህደት ወይስ ክስመት?

እሑድ፣ መስከረም 25 2012

በቅርቡ ይመሰረታል የተባለዉ ፓርቲ የብልጽግና ፓርቲ እንደሚባል ጋዜጠኞች በስፋት ሲያስነብቡት ተስተዉሎአል። በተለያዩ  ዘገባዎችም ኢህአዴግ አለቀለት፤ ዉህድ ፓርቲዉ እዉን የሚሆን ከሆነም የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ይቀየራል፤ ኢህአዴግ ከተቀየረም ጥሩ ይሆናል እያሉ ትንታኔ ሰጥተዋል። የኢህአዴግ ቀጣይ አቅጣጫ ወዴት?

https://p.dw.com/p/3QnQX
EPRDF Logo

ዉይይት፤ ኢህአዴግ፤ ወደ ዉህደት ወይስ ክስመት?

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ  ከተለያዩ የክልል ተወካዮች ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በተወያዩበት ወቅት እንደጠቀሱት ለሃገሪቱ ብልፅግና የሚሰራ ሁላችንም የሚያሰባስብ አንድ የፖለቲካ ዉህድ ፓርቲ እንመሰርታለን ማለታቸዉ ይታወሳል። ሚኒስትሩ ይህ የሚዋሃደዉ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎችንም እኩል እንደሚሳትፍ ጥቆማ ሰጥተዉ ነበር። በቅርቡ ከአንድ የሃገር ዉስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ አዲስ ዉህድ ፓርቲ እንደሚመሰረት ፍጭ ሰጥተዋል። በቅርቡ ይመሰረታል የተባለዉ ፓርቲ የብልጽግና ፓርቲ እንደሚባል በተለያዩ ድረ-ገፆች ሲዘገብ ጋዜጠኞችም በስፋት ሲያስነብቡት ተስተዉሎአል። በተለያዩ  ዘገባዎችም ኢህአዴግ አለቀለት፤ ዉህድ ፓርቲዉ እዉን የሚሆን ከሆነም የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ይቀየራል፤ ኢህአዴግ ከተቀየረም ጥሩ ይሆናል እያሉ ትንታኔ ሰጥተዋል። ይኽ ሁሉ ሆኖ ግን ከኢህአዴግ  ዉስጥ የሚሰማዉ ደግሞ ጥያቄን ያስነሳል። ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነዉ ህወሃት ዉህደቱን እንደማይቀበለዉ አመልክቶአል። አንዳንድ ፖለቲካዉን በቅርብ የሚከታተሉ አካላት እንደሚሉት ከሆነ አራቱ የኢህሃዴግ እህት ድርጅቶች ተስማምተዉ ባልቆሙበት ሁኔታ ዉህደቱ ሊሳካ አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ በሃገሪቱ ብሔርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አሰላለፍ እየተበራከተ መምጣቱ ለዚህ ዉህድ ፓርቲ ሌላዉ ፈተና መሆኑም እየተነገረ ነዉ። ኢህአዴግ  የዉስጥ ችግሮችን ተቋቁሞ ለዉህደት ቢበቃ እንኳ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ አስተካክሎ ያለዉን ችግር መፍታቱ አጠራጣሪ ነዉ የሚሉም አሉ። ይህ ዉይይታችን ይመሰረታል የተባለዉ ዉህድ ፓርቲ በምስረታ ሂዱትና ከምስረታ በኋላ ሊያጋጥሙት በሚችሉት ተግዳሮቶች ላይ ያተኩራል። በዚህ ርዕስ ላይ እንዲወያዩልን የጋበዝናቸዉ፤  ፕሮፊሰር የማነ ካሳ በመቀሌ ዩንቨርስቲ የሕግና የሥነ መንግሥት መምህር፤  መሃመድ አሊ መሃመድ፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ተንታኝ፤  እያስፒድ ተስፋዬ ፤ የፖለቲካ ጉዳይ አቀንቃኝ እና የአቦል ሚዲያ መስራቾች አንዱ፤ እንዲሁም ፤ ቸርነት ወርዶፋ ፤ የሕግ ባለሞያ ናቸዉ። ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ