1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ ሰላም በኢትዮጵያ እንዴት ይረጋገጥ?

እሑድ፣ ኅዳር 7 2012

«ወጣቱን መዉቀስ ብቻ ሳይሆን፤ ቆም ብለን ለወጣቱ ምን ያስፈልገዋል ብለን ልናስብ ይገባል። ለምን ወጣቱን ቀረብ ብለን አናወያይም? ለአዛዉንቶች የሚዲያ መድረክ ከምንሰጥ እና ግጭትን ከምናሰፋ ወጣቱን ቀረብ ብለን እናወያይ። ድሕነትና መሐይምነት ሲጋቡ አሁን እኛ ሃገር የሚታየዉን ችግር ወልደዋል። »

https://p.dw.com/p/3TB7u
Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr

ከእድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች ይልቅ ወጣቱን እናወያይ!

ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ የምትገኘዉ ኢትዮጵያ የዛኑ ያህል የተለያዩ ባህሎች ፤ ሃይማኖቶች ያሉባት  ሃገር ናት። እነዚህ የተለያዩ ብሔር ተወላጆችና የተለያዩ ሃይማኖት ተከታይ ዜጎች ለዘመናት በክፉም በደጉም ተቻችለዉ አብረዉ ኖረዋል። የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚያሳየዉም  ኢትዮጵያዉያን ለዲሞክራሲና ለነፃነት በጋራ ታግለዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ማንነት ላይ ያተኮቱ ጥቃቶች እየተስተዋሉ ነዉ።  በተለይ ወጣቶች ዘር ለይተዉ በየአካባቢዉ፤ በዩንቨርስቲዎች፤ በሚገጥሙት  ግጭትና በሚያደርሱት ጥቃት የብዙ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ጠፍቶአል። በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎአል። ግምቱ በትክክል ያልታወቀ ሐብትና ንብረት ወድሞአል። የግጭትና ግድያ ጥፋቱ ወደፊትም ላለመቀጠሉ እስካሁን ምንም ዋስትና የለም ሰሞኑን በዩንቨርስቲ ቅጥር ግቢዎች በተማሪዎች መካከል የሚደረገዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ሲታይ ደግሞ ጥፋቱ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ይቆማል የሚል ተስፋ እንዳይኖር እያደረገ ነዉ። በኢትዮጵያ ለዉጥን ለማምጣት ወጣቱ በግንባር ቀደምትነት፤ በአማራ ፋኖ፤ በኦሮሚያ ቄሮ፤ ፤ በደቡብ ኢጄቶ ፤ እንዲሁም ዘርማ በሚል የተለያየ መጠርያን ይዞ የታገለዉ ወጣት ተሳትፎ በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀስ ቆይቶአል። ሰላም ዲሞክራሲና ፍትህን በኢትዮጵያ ለማምጣት የታገለዉ  ወጣት በብሔር እና በማንነት ላይ በሚደረጉ ግጭቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑ ደግሞ አንዳንዶችን ሲያሳዝን ሌሎችን እያሳሰበ ነዉ።  ለዘመናት የቆዩት የአብሮነት እሴቶቻችን ማኅበራዊ ግንኙነታችን ላልቶ አንዱ አንዱን በስጋት የመመልከት አንዱ አንዱን በጥርጣሬ የማየት በሰላም ወጥቶ የመግባትም ችግር እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ሲሉ ብዙ ዜጎች አሳሳቢነቱን እየገለፁ ነዉ። ይህን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይሆን?  የችግሮቹ መንስኤዎችስ ምንድ ናቸዉ? ወጣቶችስ ምን ይላሉ? በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸዉ ፤ መጋቤ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ፤  ዶ/ር አባተ ጌታሁን የወሎ ዩንቨርስቲ ዳይሬክተር ፤ ዶ/ር ገብረየሱስ ተክሉ፤ የትግራይና አማራ ሰላም ፎረመ አዘጋጅ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለዉ ወጣት ነጋ ወዳጆ ናቸዉ።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ