1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

ዉኃ መጣጩ ዛፍ

ረቡዕ፣ የካቲት 3 2013

ይህ አዲስ ጥናት በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ቦታዎች በተለይም በአፋር ክልልና አጎራባች አካባቢዎች ሀገር በቀል ያልሆኑ ተክሎች የውሃ ሀብትን በመቀነስና በአካባቢው ያሉ ሀገር በቀል ተክሎችን በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/3pAa2
Wiederaufforstung in Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/Maxppp Ef Afrimages

ፕሮሶፒስ  ጁሊፎራ፣ «ወያኔ»፣ ዉኃ መጣጩ ዛፍ


«ፊዝ ኦርግ» የተባለ የሳይንስ መፅሄት በቅርቡ ያወጣው አንድ ጥናት እንዳመለከተው ፤በረሃማነትና ጨዋማነትን ይቋቋማል በሚል እንዲሁም ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ተብሎ ወደ ሀገር የገባ አንድ ተክል የከርሰ ምድር ውሃን በመቀነስ ጉዳት እያደረሰ ነው። ዛፉ በዓመት ከ3 ቢሊዮን በላይ ሜትሪክ ውሃ ሊጠቀም ይችላል ተብሏል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ በተለይም ከስሃራ በታች ባሉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅ ከጊዜ ወደ ጊዚ እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ።ለዚህም የደን ሽፋን መመናመን አንዱ ምክንያት መሆኑ ይነገራል።ይሁን እንጅ የደን ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም ለአፈርና የውሃ ጥበቃ ተብለው ከውጭ የሚመጡ ሀገር በቀል ያልሆኑ አንዳንድ ተክሎችም በአካባቢ ላይ እያሳደሩ ያሉት ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ «ፊዚ ኦርግ» የተባለ የሳይንስ መፅሄት በቅርቡ ያወጣው አንድ ጥናት አመልክቷል። የኢትዮጵያውያ፣የደቡብ አፍሪቃና የስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ አዲስ ጥናት በኢትዮጵያ ዝቅተኛ ቦታዎች በተለይም በአፋር ክልልና አጎራባች አካባቢዎች ሀገር በቀል ያልሆኑ ተክሎች የውሃ ሀብትን በመቀነስና በአካባቢው ያሉ ሀገር በቀል ተክሎችን በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን አመልክቷል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና የመሬት ሀብት ማዕከል ዶክተር ጠና አላምረው ከተመራማሪዎቹ አንዱ ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት ጥናቱ ያተኮረው በአጠቃላይ እንጨታማ በሚባሉ አረሞች ላይ ሲሆን፤በተለይም በእንግሊዝኛው አጠራሩ«ፕሮሶፒስ ጁሊፎራ» የተባለው ዛፍ ሀገር በቀል ዕፅዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። 
«ፕሮሶፒስ  ጁሊፎራ» የተባለው ተክል በረሃማነትና ጨዋማነትን ይቋቋማል በሚል ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ተብሎ በ1970ዎቹ መጨረሻ ከደቡብ አሜሪካ ፔሩ በማምጣት በአፋር ክልል መልካወረር አካባቢ የተጀመረ ቢሆንም ያልተፈለገ ቦታ በመብቀልና ወራሪ አረም በመሆን በግጦሽና በእርሻ መሬቶች ላይም ችግር ማድረሱን ይናገራሉ።ጥናቱ እንደሚያሳየው ከ1980 ዎቹ ጀምሮ በአፋር ክልል ብቻ ይህ ሀገር በቀል ያልሆነ ዛፍ ወደ 1.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ወሯል።ይህም ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ፈተና ሆኗል። 
በግጦሽና በእርሻ መሬት እንዲሁም በሌሎች ሀገር በቀል ዕፅዋት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ይህ ተክል አጫጭር ሥሮች ካሏቸው የሀገሬው ዛፎች ጋር ሲነፃጸር የስሮቹ ከመሬት ወለል በታች እስከ 50 ሜትር ድረስ ዘልቆ መግባት የሚችል በመሆኑ በደረቅ ወቅት ሳይቀር አንድ ዛፍ በየቀኑ እስከ 15 ሊትር ውሃ ይጠቀማል።ይህም የከርሰ ምድር ውሃን በመቀነስ በአዋሽ ወንዝ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። 
በአዋሽ ወንዝ እና የአከባቢውን ደረቅ መሬት የወረረው ይህ ባዕድ ዛፍ፤ በዓመት እስከ 3.3 ቢሊዮን ሜትሪክ ውሃ ሊጠቀም እንደሚችል ጥናቱ አመልክቷል። ይህም የውሃ ሀብትን በመቀነስ በመስኖ ከሚለሙ የሸንኮራ አገዳና የጥጥ ምርቶች በዓመት ሊገኝ ይችል የነበረውን በርካታ ሚሊዮን ዶላር ያሳጣል። ስለሆነም ይህ ወራሪ ዛፍ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የተክሎቹን ጥግግትና ብዛት መቀነስ ካልተቻለና የመጤ ተክሎቹ መስፋፋት ከቀጠለ በክልሉም ይሁን በሀገር ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ተብሏል፡፡ እንደ ተመራማሪው ዶክተር ጠና የአርብቶ አደሮችን የህይወት ዘይቬ እስከመቀየር ሊደርስ ይችላል ። ያም ሆኖ ጉዳቱን ለመከላከል አትክልቱን ከመንቀል ጀምሮ ኬሚካል እስከመጠቀም የሚደርሱ የመከላከያ መንገዶች ቢኖሩም የተቀናጀ ፖሊሲና የተቋም ስርዓት ግን የለም። 
በደቡብ አፍሪቃ የሽቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑትና በሀገሪቱ እንጨታማ አረሞችን ለማጥፋት በወጣው መርሃ ግብር ሳይንሳዊ አማካሪ ብሪያን ፋን ዊልገን እንደሚሉት ፤ አዲሱ የጥናት ውጤት በደቡብ አፍሪካ ወራሪ በሆኑ የዛፍ ዝርያዎችና የውሃ አጠቃቀምን አስመልክቶ የተሰራውን ጥናትና ግኝቶች የሚደግፍ ነው። ፕሮፌሰሩ ለሳይንስ መጽሄቱ እንደገለፁት በደቡብ አፍሪቃም ወራሪና ባዕድ ዛፎች በዓመት ከ 1.5 እስከ 2.5 ቢሊዮን ሚትሪክ ኪዩብ ውሃ ሊቀንሱ ይችላሉ።ፕሮፌሰር ብሪያን ፋን እንደሚሉት እነዚህ ተክሎች በጊዜ ካልተገቱ የከርሰ ምድር ውሃን ቀጣይነት በመቀነስ የውሃ እጥረትን በማስከተል የአርሶ አደሮች እና የከተማ ነዋሪዎችን ችግር ላይ ይጥላሉ።የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እና ዕድገትን በመገደብም በሀገር ላይ ከባድ ኪሳራን ያስከትላሉ ። ይህንን ለመከላከል በደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብና “ለውሃ መሥራት” የሚል መጠነ ሰፊ ሀገራዊ መርሃ ግብር ቀርፆ በመስራት ላይ ሲሆን፤ወራሪ የውጭ ዛፎችን እንዳይባዙ የሚከለክልና የመሬት ባለቤቶችም እንዲቆጣጠሩ የሚያስገድድ ሕግ አውጥቷልም ብለዋል። በኢትዮጵያም እነዚህን ዛፎች መትከል የተከለከለ ቢሆንም ዶክተር ጠና እንደሚሉት ያደረሱትን ጉዳት ለመቆጣጠርና የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የተቀናጀ የቁጥጥር መርሃግብር የለም። በችግሩ ላይ ያለው አረዳድና የመፍትሄ ሃሳብም ቢሆን የተለያዬ ነው። 
የድርጊት መርሃ ግብር በተደራጀ መንገድ ችግሩን ከመቆጣጠር ባሻገር እንዲህ መሰሉን ጉዳት ከወዲሁ ለመከላከል ከውጭ ወደ ሀገር በሚገቡ ዕፅዋት ላይ ቅድመ ጥናት ማድረግ፤ ከገቡ በኋላም የሚያስከትሉትን ጥቅምና ጉዳት በናሙና ደረጃ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተመራማሪው ዶክተር ጠና አላምረው ጨምረው ገልፀዋል። 
ፀሐይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ