ዉሎ አዳር ከጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ጋር
ሐሙስ፣ ጥር 18 2015ዉሎ አዳር በሚል ቅፅል ስሟ የምትታወቀዉ ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ኢትዮጵያን ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ተጉዛ፤ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ጎብኝታ፤ ባህላቸዉን ተዋዉቃ ኑሮአቸዉን ኖራ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለህዝብ «ዉሎ አዳር» በሚል ፕሮግራምዋ ከባልደረቦችዋ ጋር አቀናብራ ለሃገር የምታሳየዉ የአገርህን እወቅ ዝግጅቷ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን አትርፋለች። ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ከተጓዘችባቸዉ የኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች ዉቡን ባህል ከምንጩ፤ ከህብረተሰቡ ጓዳ ቀድታ እና አብራ ኖራ፤ በበዘጋቢ ፊልም መልክ በኢትዮጵያ በቴሌቭዝን ታቅርበዉ እንጂ ዝግጅቱ ለእይታ እስኪበቃ የምትሄድበት መንገድ የምትሰራዉ ሥራ ቀላል ባለመሆኑ እጅግ ከባድና ፈታኝ ሁኔታዎችን በጥበብ አልፋ ጥዑም ዝግጅትን ማቅረቧን ያስመሰከረች ጠንካራ ጋዜጠኛ ሲሉ ብዙዎች ይመሰክሩላታል። አስካለ ተስፋዬ በዶቼ ቬለ የባህል መድረክ እንግዳ ሆና ቀርባለች።
አስካለ ተስፋዬ ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ የገባቸዉ ከዛሬ 25 ወይም 26 ዓመት በፊት በሬድዮ የህጻናት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆና ነዉ። የጋዜጠኝነት ሞያን ከጀመረች ሃያ አምስት አያ ስድስት ዓመት እንደሆናት የምታናገረዉ አስካለ በቴሌቭዝን ዉሎ አዳር ዝግጅቷን ከጀመረች ግን አንድ አራት ዓመት ገደማ እንደሆናት ትናገራለች። ዝግጅቱ አስደሳች፤ ስራዉ አድካሚ ፈታኝ ቢሆንም፤ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር አግኝቼበታለሁ ስትልም ለስራዉ ያላትን ፍቅር አፅኖት ትሰጣለች። ህዝብ ለስዋ ፍቅርና ክብር እንዳለዉ ያወቀችዉ ግን ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ታማ አልጋ ላይ በዋለችበት አጋጣሚ መሆኑን አትደብቅም። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተጉዛ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል እና አኗኗርን አይታ እና ኖራ መልሳ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ስትጓዝ በኖረችባቸዉ ማኅበረሰቦች ዘንድ ሁሉ ንፁህ ፍቅርን አግኝታለች፤ አብራ ማዕድ ተቀምጣ፤ ቁርበት ላይ አድራ፤ ስራዋን ጨርሳ ደህና ሁኑ ብላ ስትወጣ ከማህረሰቡ ጋር ተላቅሳ እንደምትለያየም ነግራናለች።
ሰዉ ምን ያህል ገንዘብ ቢከፍል ሊያገኘዉ እና ሊያየዉ የማይችለዉን የተለያየ ማኅበረሰብ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ከዝያም ደግሞ የህዝብ ፍቅር ታክሎበት በዉሎ አዳር ስራዬ አግንቻለሁ ስትል፤ አንደበተ ርትዑዋ ጋዜጠኛ ወደ ኮንሶ ተጉዛ ከማህበረሰቡ ጋር ኖራ ያየችዉን አጫወታናለች። አስካለ አብራቸዉ የኖረቻቸዉን የኮንሶ አባላት ስማቸዉን አብራቸዉ ያሳለፈችዉን ነገር ሁሉ የተረከችልን በደስታ ነዉ።
ጋዜጠኛ አስካለ ስላየችዉ ነገር ስትገልፅ አንጠልጣይ በሆነ ቅላጼ ነዉ። ትረካዋን ትጀምራለች፤ ምን እንደበላች፤ ከማህበረሰቡ ጋር ምን ስትሰራ እንደዋለች፤ ምን አስደናቂ ነገር እንዳየች ትተርካለች፤ ከዝያ ደግሞ ቆም ትልና ድንቅ የሆነ ባህል፤ ገራሚ የሆነ ገጠመኝ ትላለች። ንፁህ የሆነ ፍቅር የሚገኘዉ እኮ ከከተማ ወጣ ሲባል ነዉ ስትል ፤ ደሞ ወደሌላኛዉ ገጠመኞችዋ ትረካዋን ትቀጥላለች።
በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ማህበረሰብ ዉስጥ የሚገኙ የወጣቶች ባህላዊ የፍቅር መገላለጫ ሌላዉ ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬን የገጠማት አስገራሚ ሁኔታ ነዉ። በበሰለ እና በጥሪ ሎሚ የሚገለጽ ፍቅር። ጋዜጠኛዋ መጓዝ ወደ ፈለገቻቸዉ ቦታዎች ሁሉ ለመጓዝ ስታቅድ የአካባቢዉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሁሉ ተባባሪዎችዋ እንደሆኑ እና በእነሱ በኩል፤ ሁሉ ነገር ለእስዋና ለፊልም ቀራጩ ባልደረባዋ እንደሚመቻችም ነግራናለች።
ጋዜጠኛ አስካለ በትረካ ዳግም ወደ ደቡብ ክልል አባያ አካባቢ ወደ ሚኖሩ ወደ ጌዲቾ ማህበረሰብ ዘንድ ይዛንም ተጉዛለች። አስካለ ተስፋዬን በዚህ አገርህን አስተዋዉቅ የዉሉ አዳር ጉዞዋ እስካሁን የሚያስደነግጥ ወይም የሚያስፈራ ነገር አልገጠማት ይሆን? ጠይቀናታል አስካለ ከሃመሮች ጋር ዉሎ አዳር ላይ ሳለች እባብ ገጥሟታል። እንዴት አልፋዉ ይሆን? ጋዜጠኛ አስካለን ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስትጓዝ የወቅቱ የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ አያስፈራትም? ሌላዉ ያቀረብንላት ጥያቄ ነበር። አስካለ እኔ አልፈራም፤ ከከተማ ወጣ ሲባል ሁሉ ነገር ንፁህ፤ ፀጥ ያለ እና ደግነት ብቻ ነዉ ባይ ናት። ከአስካለ ጋር ያደረግነዉን ቃለምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ