1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
እምነትኢትዮጵያ

የኢድ አል ፈጥር አከባበር ትውስታዎች እና ወጣቱ

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2018

በሀገር ውስጥ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን የኢድ አል ፈጥር በዓልን እንዴት እንደሚያከብሩ ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብለን ጠይቀናል። ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ስላሏቸው ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውስታዎችም አካፍለውናል።

https://p.dw.com/p/5Al1j
የኢድ አል ፈጥር በዓልን ለማክበር ጎዳና ላይ የተሰበሰቡ በርካታ ሰዎች በአማራ ክልል ደሴ፤ ልጅ ፣ ወንድ፣ ሴት አዋቂ
የኢድ አል ፈጥር በዓልን ለማክበር ጎዳና ላይ የተሰበሰቡ ሰዎች በአማራ ክልል ደሴምስል፦ Esayas Gelaw/DW

የኢድ አል ፈጥር አከባበር ትውስታዎች እና ወጣቱ

ከዲጃ አሰፋ ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። ስለ የኢድ አል ፈጥር ስታስብ አዕምሮዋ ውስጥ ወዲያው የሚመጣው፤ ከቤተሰብ ጋር መሰባሰቡ እና ከዘመድ አድማድ ጋር ኢድ ሙባረክ መባባሉ ነው። "ጠዋት ተነስተን የኢድ ሰላት እንሰግዳለን። ኢል አል ፈጥርን ከኢድ አል አደአ ትንሽ ለየት የሚያደርገው ከተማም ከሆነ ከተማ ብዙም ሳይርቅ አካባቢው የሚገኘው  በአካባቢው የሚገኘው ቤተሰብ በመሰባሰብ የሚያከብረው በዓል ነው።"

አብደላህ ኢድሪስ  በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ  ነዋሪ ነው። እሱም ዓመት በዓሉን የሚጀምረው በሶላት ነው። 
"ያው ጠዋት ተነስተን ኳስ ሜዳ ሄደን ሶላት እንሰግዳለን። ሁሉም እዛ አካባቢ የሚኖር ሰው በጠቅላላ ሶላቱን ሰግዶ ምክር ተለግሶ መመለስ ነው።" ይላል።

ኢድ አል ፈጥር ዓርብ መዋሉ ለመዘጋጀት ጊዜ የሰጣል?

የኢድ አል ፈጥር በዓል ሀሙስ ይዋል ዓርብ የታወቀው ዕሮብ አመሻሽ ላይ ነው። በከፊል ተዘጋጅተን  ነበር የምትለው የቢሮ ሰራተኛ ከዲጃ በዓሉ ዐርብ ዕለት እንደሚውል ስታውቅ ደስ ተሰኝታለች። "አርብ ነው ሲባል የቀሩት ስራዎቻችንን እንድንጨርስ ይበልጥ ሰፊ ጊዜ ነው ያገኘነው። ይህ በዓል ደግሞ ቤተሰብ ተሰብስቦ የሚያከብረው፤ ሰው የሚመጣበት ነውና ሌሎች የጎደሉ ነገሮች ካሉ እንድናሟላ ሰፊ ጊዜ ነው ያገኘነው።"

አብደላህ ግን ሐሙስም ዋለ ዓርብ «ለእኔ ለውጥ የለውም» ይላል።  "ወሩ የሚቆጠረው በጨረቃ አቆጣጠር ስለሆነ የግድ እሷ መታየት ስላለባት ነው። አንድ ወይም በሁለት ቀን ውስጥ ይሆናል ብለን በምንገምብበት ሰዓት  የሚገዛ ነገር  ይገዛል። የቀኑ አለዋወጥ ምንም ለውጥ አያመጣብንም።"

ሰዎች ቆመው ብር ሲቆጥሩ
የኢድ በዓል ሽመታ በደሴምስል፦ Esayas Gelaw/DW

የኢድ በዓልን ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? ኃይማኖታዊ አከባበሩ ያመዝናል ወይስ ከቤተሰብ ጋር መሰባሰቡ ያመዝናል?


"ሸሪዓው ይህንን የሐይማኖት በዓል በጣም ትልቅ አድርጎ ነው የሚይዘው።  የኢድ አል አረፋ እና የኢድ አል አልፈጥር እስልምና ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። ከነብያቶች ሲወራረሱ የቆዩ ስለሆኑ በጣም ትልቅ በዓላት ናቸው። ጌታችንን በመዝከር ነው የምናሳልፈው። ትኩረቴ እዛ ላይ ነው።  ከዛ ውጭ ምሳ ሰዓት ላይ ሰብሰብ ልንል እንችላለን።" በማለት ሐይማኖታዊ ስነ ስርዓቱ እንደሚበልጥበት ይናገራል።

„የኢድ ቀን ሰቀዳ በፍቃደኝነት መስጠት ይቻላል። ግን ግዴታ አይደለም ።” የምትለው ከዲጃ ግዴታ የሆነውንም ነገር እንዲህ ስትል ገልፃልናለች። 
"ኢል አል ፈጥር ከመከበሩ አንድ እና ሁለት ቀናት በፊት ግዴታ አለ። ዘካተል ፈጥር የሚባል። መሥፈርት አለው። በዛ መስፈርት መሰረት ለድሆች ለድሆች የምታካፍይበት። የሌላቸው ሰዎች በዓልን ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ። አቅም ያለው ሰው ሁሉ ይሰጣል። ያ የሁሉም ሰው ግዴታ ነው።" 


በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ባሉ ሃገራት ሰው ቤት ተቀጥረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንስ በዓሉን እንዴት ያከብራሉ? በበዓል ቀን የማይቀሩ ምግቦችስ?  

ሰሚራ አቡዳቢ አቅራቢያ የምትገኘው አላይን ከተማ ነው የምትኖረው። በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ስትኖር አራት አመት ገደማ ሊሆናት ነው።  ከዚህ ቀደም በዓሉን ደስ በሚል ሁኔታ እንዳሳለፈች ገልፃልናለች። "የምናከብር የነበረው ሰብሰብ ብለን ነው። የበዓል ቀን ዕረፍት ይፈቀድልናል። ጓደኞች አሉኝ። ኢትዮጵያ እንደምናከብረው ማለት ይቻላል። ጠዋት እንሄዳለን። መስገጃ ቦታ አለ። ለሴትም ለወንድም የተዘጋጀ አለ። "

ይሁንና የዘንድሮው በዓል ትንሽ ለየት ይላል። ዩናይትድ ስቴትስ እና  እስራኤል  በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ እና ኢራን የአፀፋ ምላሽ በአቅራቢያው የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ጥቅም ያለቻቸው እንደ ጦር ሰፈር የመሳሰሉ ቦታዎች ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ በአቡ ዳቢ አካባቢ ያለውም ሁኔታ ሳሚራ እንደምትለው የሚያሰጋ ነው።
"ድባቡ ለየት ብሏል። በስልክ ማስጠንቀቂያ ደርሶናል። ወደዚያ ወደዚህ እንዳይባል። የዱባይን ከተማ ቀርፃችሁ እንዳትልኩ የሚል ማስጠንቀቂያ በስልክ እየገባልን ነው። እንደልባችን አላከበርንም። የኢትዮጵያም ምግብ እየገባልን አይደለም። "

አቡ ዳቢ በኢራን ጥቃት እጎአ መጋቢት አንድ ቀን የደረሰ ፍንዳታ ፤ ፅስ ወደ ሰማይ
በኢራን ጥቃት እጎአ መጋቢት አንድ ቀን 2026 በአቡ ዳቢ የደረሰ ፍንዳታምስል፦ Ryan Lim/AFP

ሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራው ሰሚራ የመጀመሪያዋን ኢድ አል ፈጥር ከአሰሪዎቿ ጋር የማክበር እድሉ ነበራት።  በእነሱ ዘንድ ያለው አከባበር ምን እንደሚመስል እና በበዓል ቀን ስላለው የምግብ አይነትም ገልፃልናለች።
 "አልዋት እና ቡና ይጠጡ እና ቀጥታ ወደ ወንድ ቤተሰብ ቤት፤ ትልቅ ሰው ቤት ነው የሚሄዱት። ተሰግዶ እንደተመጣ ወንዱ እናቱ ቤት ነው  ልጆቹን እና ሚስቱን ይዞ የሚሄደው ። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ወደ እሷ እናት ቤት ነው። "

ምግብን በተመለከተ የዋዜማው ቀን የሚሰራው ለየት ያለ ምግብ ሙሉ ፍየል ታርዶ እና ተቀምሞ በአልሙኒየም ተጠቅልሎ ፍም እሳት ውስጥ እንደሚከተት እና ለሌቱን እዛው ምድጃው ውስጥ ሲበስል እንደሚያድር ነው። ሌላው ሳሚራ እንደምትለው አሪስ የሚባል ከስንዴ የሚሰራ ምግብ አለ። ቁርስ ላይ የሚበላ።

ቀኑን ሙሉ ምንም ነገር ሳይበሉ መዋል ተለምዶ ፆሙ ሲያበቃ ጠዋት መብላት እንዴት ነው?  

አይከብድም ይላል ኢትዮጵያ የሚኖረው አብደላህ "ችግር የለውም። ጠዋት ላይ ትንሽ ቁርስ ቀመስ ተደርጎ ይኬዳል። ከሶላት መልስ ምሳ በደንብ እንበላለን። ከዛ በማግስቱ የስድስት ቀን ጾም ይገባል።" ይላል አብደላህ- በፍቃደኝት የሚደረግ ፆም ነው።

ቀደም ሲል በዓመት በዓል ዕለት በሙስሊሙም ማህበረሰብ ይሁን በክርስትያኑ ዘንድ የእንኳን አደረሳችሁ ምኞት ለመግለፅ አስቀድሞ ደብዳቤ ይፅፋል ወይም የዕለቱ ቀን ስልክ በመደወል ምኞቹን ይገልፃል። የዘመኑስ ወጣት መልካም ምኞቱን እንዴት ይገልፃል? "አብዘሀኛው ወጣት ሜሴጅ ይላላካል። ወንድሞቼ፣ እህቶቼ ይፅፉልኛል። ሶሻል ሚዲያ ላይ አብዛሀኛው አፍጦ ነው የሚውለው። መፃፃፉ ግድ ነው።"


አብደላህም ይሁን ከዲጃ  ስለ ኢድ አል ፈጥር በዓል ያላቸው ግንዛቤ ልጅ ሳሉ እና አሁን በወጣትነት እድሜ ላይ ያለውን ሲያነፃፅሩ የተቀየረ ነገር አለ። 
 ከዲጃ "ልጅ እያለን ኢል ሲመጣ ጠዋት ተነስተን ታጥበን ለኢድ ሶላት መሄዱን በጣም የምንጓጓው ነበር። አሁንም እንጓጓለን። አሁን ወጣት ሆነን ግን ይበልጥ የሚያጓጓን የረመዳኑ ወር ነው። ወሩ ማለቁ በጣም ያሳሳናል። እሱ ይለያል። " ትላለች።

አብደላህ ደግሞ "ልጅ እያለሁ ኃይማኖት ላይ ብዙ ትኩረት አልነበረኝም። ወተን ያው ስንጫወት ውለን መመለስ ነው። አሁን ግን ኃይማኖት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ።
ይላል አብደላህ።

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ