1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የወጣቱ የፈጠራ ሥራ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27 2013

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያስተዋውቁ ወጣቶች  እየተበራከቱ መምጣታቸው ይስተዋላል፡፡ በተለያዩ አካላት አውደ ርዕዮች መዘጋጀትና በዘርፉ የውድድር መንፈስ እንዲጠናከር መደረጉ በሳይንስና ቴክኖሎጁ ፈጠራዎች ላይ መነቃቃት ሣይፈጥር እንዳልቀረ ይገመታል።

https://p.dw.com/p/3sz84
Äthiopien Hawassa | Student Akliil Assefa entwickelt Smart Phone App für den Haushalt
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የእጅ ስልክን በመጠቀም የተለያዩ ተግባራትን የመፈፀም ፈጠራ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያስተዋውቁ ወጣቶች  እየተበራከቱ መምጣታቸው ይስተዋላል፡፡ በተለያዩ አካላት አውደ ርዕዮች መዘጋጀትና በዘርፉ የውድድር መንፈስ እንዲጠናከር መደረጉ በሳይንስና ቴክኖሎጁ ፈጠራዎች ላይ መነቃቃት ሣይፈጥር እንዳልቀረ ይገመታል።

የሀዋሣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪ አክሊል አሰፋ ሰሞኑን ያስተዋወቀው የፈጠራ ሥራ ለዚህ በማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ተማሪው ያስተዋወቀው የፈጠራ ሥራ የተንቀሳቃሽ ስልኩን ከቤት ውስጥ የመገልገያ ቁሳቁሶች ጋር በማገናኘት ካለበት ቦታ ሆኖ ማንኛውንም ትዕዛዝ ለመስጠት ያስችለዋል።

Äthiopien Hawassa | Student Akliil Assefa entwickelt Smart Phone App für den Haushalt
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በኮሌጁ የምርምር ማዕከል ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ተማሪ አክሊል የእጅ ስልኩን ብቻ በመጠቀም አምፖል ማብራትና ማጥፋት፣ ክፍሎችን ማቀዝቀዝና ማሞቅ እንዲሁም ሻይ እንዲፈላለት ትዕዛን ሲሰጥ ይታያል፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሆስፒታሎችና በከተሞች የሚገኙ የመንገድ መብራቶች አልፎ አልፎ በቀን ጭምር ክፍት ሆነው ሲበሩ ይታያል። ይህም ለኃይል ብክነት የተጋለጡ ያደርጋቸዋል የሚለው ተማሪ አክሊል ይህ የፈጠራ ሥራ ታዲያ ሁሉንም የመብራት መስመሮች ከአንድ ቦታ ሆኖ በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል በተግባር ባደረገው ገለጻ አብራርቶልኛል፡፡

አንድ ሰው ከመንገድ ሆኖ በቤት ያለን ሰው ሻይ አፍልቶ እንዲጠብቀው ከፈለገ የሥልክ መልዕክት ሊነግር ይችላል፡፡ በአንጻሩ የተዘጋ ቤት ከፍቶ የሚገበ ሠው ግን ይህ እድል አይኖረውም፡፡ የተማሪ አክሊል ሌላው ፈጠራ ታዲያ ውኃና ሻይ ቅጠል ጥዶ ከቤቱ የወጣ ሰው በመንገድ እያለ ሻይ ተፈልቶ እንዲጠብቀው ከፈለገ ሥልኩን ከኪሱ በመውጣት ማዘዝ ብቻ ይጠበቅበታል ይላል ተማሪ አክሊል፡፡

Äthiopien Hawassa | Student Akliil Assefa entwickelt Smart Phone App für den Haushalt
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ተማሪ አክሊል እንደሚለው የአሁኑን ጨምሮ ከአሁን ቀደም እስከ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ባቀረባቸው የፈጠራ ሥራዎች ተደጋጋሚ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ አሁን ላይ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን የሚያገኝበትና ፈጠራው ወደ ምርት የሚሸጋገርበት ሁኔታ ቢኖር ከዚህ በተሻለ ለመሥራት ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ