1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞው ቀያቸው አንመለስም አሉ

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች “በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ አካባቢው መመለስ እንፈልግም” ሲሉ ትላንት እና ዛሬ ተቃውሞ አሰሙ። በአካባቢው አሁንም ሰዎች እንደሚገደሉ ተፈናቃዮች ተናግረዋል። አንድ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃላፊ በመተከል ዞን አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የጸጥታ ችግር እንደሚስተዋል አምነዋል። 

https://p.dw.com/p/3Kn7T
Äthiopien Demonstration in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞው ቀያቸው አንመለስም አሉ

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ዳንጉር ከተባለ አካባቢ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች የአካባቢው ሰላም አስተማማኝ ባለመሆኑ ወደ ቦታው እንደማይመለሱ ተናገሩ። በባሕር ዳር ተጥለው የሚገኙት እነኚሁ ተፈናቃዮች የዕለት እርዳታ እንደተነፈጋቸውም ለዶይቼ ቬለ (DW) ገልጸዋል። መንግስት እርዳታ የሚሰጣችሁ ወደ ቦታው ስትሄዱ ነው በማለቱ ለከፍተኛ ችግር እንደተዳረጉም አመልክተዋል፡፡

አቶ ሰኢድ መሐመድ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አንዱ ሲሆኑ "ግድያ ስላልቆመ ወደ ቦታው መሄድ አደጋ አለው" ብለዋል። ሌላዋ ያነጋገርናት ወጣት እንደምትለው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አመራሮችም  "ለጥያቄያችን ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም" ብላለች። የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት "ችግሩን ለመፍታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሉበት ሁኔታ ላይ ነው ግድያ የተፈፀመው" ያሉት ደግሞ ሌላው ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪ ናቸው። "እርቁም እውነተኛ አይደለም" ሲሉ አጣጥለውታል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ጉዳች ቢሮ የሰላም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ በዳንጉር ወረዳ አንዳንድ አካባቢዎች ትንኮሳዎች እንዳሉ ግን ደግሞ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ በስልክ አመልክተዋል። የክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ  አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ለዋናው ኮሚሽነር እና ለምክትል ኮሚሽነሯ በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። 

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ