1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ቀያቸዉ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ

ዓርብ፣ መስከረም 6 2015

በአፋር ክልል መንግሥት በሰመራና አጋቲና የተባሉ ሁለት መጠለያዎች ውስጥ ለደኅንነታቸው በሚል ተይዘው ከቆዩ ዘጠኝ ሺህ አሥር ያህል የትግራይ ተወላጆች የሰመራዎቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ቀያቸው አብአላ ከተማ መመለሳቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተናገረ።

https://p.dw.com/p/4Gz0Z
Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)
ምስል Solomon Muchie/DW

የሰመራዎቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ቀያቸው አብአላ ተመልሰዋል

በአፋር ክልል መንግሥት በሰመራና አጋቲና የተባሉ ሁለት መጠለያዎች ውስጥ ለደኅንነታቸው በሚል ተይዘው ከቆዩ ዘጠኝ ሺህ አሥር ያህል የትግራይ ተወላጆች የሰመራዎቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ቀያቸው አብአላ ከተማ መመለሳቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተናገረ።

ከነሐሴ 17 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ድረስ እንዲመለሱ የተደረጉት ነዋሪዎቹ ሲመለሱ ቤት ንብረታቸው በጦርነት ምክንያት በመውደሙ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። ይሁንና አሁንም ከሥጋት እንዳልተላቀቁ ተነግሯል። በዚሁ ክልል አጋቲና በተባለው የመጠለያ ካምፕ ውስጥ የቆዩት 600 ያህል ዜጎች ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ መሄድ ወደሚፈልጉበት ትግራይ ክልል አለመጓዛቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።

በአፋር ክልል በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የቆዩትን የትግራይ ተወላጅ ዜጎች ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ. ም ጀምሮ በተደረገ ውይይት ከዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የክልሉ መንግሥት ጥናት አድርጎ ሰዎቹ መመለስ እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸው ተገልጿል። ይህንን ትከትሎ ሰመራ ካምፕ ውስጥ የነበሩት ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ አብአላ መመለሳቸውን አቶ ዑስማን አህመድ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰመራ ጽ/ቤት ኃላፊ

BG Tigray | Mekele
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። በዚህም ከነሐሴ 15 ቀን ጀምሮ በተደረገው የማመላስ ሥራ የአፋር ክልል " ብዙ ሰርቷል" ሲሉ የተከናወነውም ሥራ ገልፀዋል። በአፋር ክልል የአብአላ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ እና በሁለቱ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ እያስተባበሩ የቆዩት አቶ አብደላ አሚን "ሰዎቹ ተመልሰው የሰመራ ካምፕ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል። ከተመለሱ በኋላም ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ" ብለዋል

ጦርነት ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ. ም እንደገና ማገርሸቱ በአጋቲና የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይግኙ የነበሩትና ወደ ትግራይ ክልል መሄድ እንፈልጋለን ብለው የነበሩት እክል እንዲገጥማቸው አድርጓል። ይህንንም አቶ ዑስማን አህመድ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰመራ ጽ/ቤት ኃላፊ አረጋግጠዋል። ኢሰመኮ የአፋር ክልል እነዚህ ሰዎች ወደመጡበት ቀየ እንዲመለሱ ማድረጉን እውቅና እንደሚሰጥ እና ለዚህ ስኬት የሰሩትን በምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በኩል አመስግኗል። መመለሳቸው መልካም ሆኖ ሳለ ሰዎቹ አሁንም ከሥጋት ሙሉ በሙሉ አለመላቀቃቸውን ያነጋገርናቸው የሥራ ኃላፊዎች ገልፀዋል።

እነዚህ የትግራይ ተወላጆች የሕወሓት ኃይሎች በአብአላ ከተማ ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ሕይወታቸውን ለማዳን በሚል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ታኅሣስ 9 ቀን 2014 ዓ .ም ወደ ሰመራ ከተማ እንዲወሰዱ የተደረጉና ካምፕ ውስጥ የቆዩ ናቸው። መንግሥት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደኅንነታቸውን ሲጠበቅ ቆይቶ የተሻለ ሰላም መፈጠሩን በማመኑ አሁን እንዲመለሱ መደረጉንም ከዚህ በፊት ዘግበናል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ