1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ መቐለ የተጓዙ የተ.መ.ድ አውሮፕላኖች ፈቃድ ተከልክለው መመለሳቸውን መንግሥት ገለጸ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 13 2014

ወደ ትግራይ የተጓዙ ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ አውሮፕላኖች ትናንት አርብ የተመለሱት "በሥፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው" መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ። 

https://p.dw.com/p/4260a
Äthiopien Stadtansicht Mekele
ምስል Edwin Remsberg/imago images

ወደ ትግራይ የተጓዙ ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ አውሮፕላኖች ትናንት አርብ የተመለሱት "በሥፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው" መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ። 
በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች እና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ ትናንት አርብ ባወጡት መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ አውሮፕላን ወደ መቐለ ያደረገው በረራ "በአየር ድብደባ ምክንያት" መስተጓጎሉን ይፋ አድርገው ነበር። 
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአየር ድብደባዎቹ በፊት ማስጠንቀቂያ አልተሰጠውም" ያሉት ግሪፊትዝ ለበረራ አስፈላጊ ፈቃድ ተሰጥቶት እንደነበር ገልጸዋል።
ወደ መቐለ የተጓዙት ሁለት አውሮፕላኖች መሆናቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን "በረራው በሥፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ወደ አዲስ አበባ" እንደተመለሱ ዛሬ ቅዳሜ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በተባለው የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ በኩል አስታውቋል። 
ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ የበረሩት አውሮፕላኖች በመቐለ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ እንዳይርፉ እንደተነገራቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች መግለጻቸውን ሬውተርስ ትናንት አርብ ዘግቧል። 
የተባበሩት መንግሥታት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የተቸገሩ ሰዎች ዕርዳታ ለማድረስ ሁሉንም ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት የሰብዓዊ ጉዳዮች እና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪው ተለዋዋጭ የሆነ የግጭቱ ጠባይ ግን ይኸንን የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት አርብ በአየር በተፈጸመው ድብደባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት "ማሰልጠኛ ማዕከል" ዒላማ እንደነበር የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በተባለው የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ በኩል ይፋ አድርጎ ነበር። በኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ መሠረት የአየር ድብደባ ዒላማ የሆነው ተቋም "ለአሸባሪው ቡድን ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል ነበር።" ይኸው ተቋም ህወሓት "ወታደራዊ ስልጠና የሚሠጥበት" እና "የዉጊያ ግንኙነት ኔት ወርክ ያለበት" መሆኑንም ገልጿል።
በሳምንቱ ለአምስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት በፈጸመው የአየር ድብደባ አስራ አንድ ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸውን ህወሓት የሚቆጣጠረው የትግራይ ቴሌቭዥን ዘግቧል። 
አስራ አንድ ሰዎች የጫነው አውሮፕላን በረራውን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ወደ መቐለ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ እንደሰረዘ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች ትናንት አርብ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።  
ማርቲን ግሪፊትዝ የኢትዮጵያ መንግሥት በመቐለ በሚያደርጋቸው ድብደባዎች የሰላማዊ ሰዎች ደሕንነት እና ለትግራይ የሚቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታ በቂ አለመሆን እንደሚያሳስባቸው ሥጋታቸውን ገልጸዋል። 
ማርቲን ግሪፊትዝ "በአማራ እና አፋር ክልሎች እየተካሔደ ያለው ጦርነት እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት" እንዳስጨነቃቸውም ጠቁመዋል።
አስተባባሪው "ሰላማዊ ሰዎችን እና መሠረተ-ልማቶቻቸውን ለመጠበቅ ሁሉም የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል። በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋት መሠረት ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን፣ ሰላማዊ ንብረቶችን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞችን እና ንብረቶቻቸው ከጉዳት ለመጠበቅ ቋሚ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።
እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ