1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 21 2014

በጎርጎሳውያኑ 2030 የወባ በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ዐስታወቀ። የአሜሪካ መንግስት በአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኩል ይህንኑን ዓለማ በመደገፍ 9.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ፕሮጀክቱን እንደሚደግፍ ይፋ ሆኗል

https://p.dw.com/p/4AdVQ
Äthiopien Adama | USAID Programm gegen Malaria
ምስል Seyoum Getu/DW

ሕንጻው 60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል

በጎርጎሳውያኑ 2030 የወባ በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ዐስታወቀ። የአሜሪካ መንግስት በአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኩል ይህንኑን ዓለማ በመደገፍ 9.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ፕሮጀክቱን እንደሚደግፍ ይፋ ሆኗል። ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ «ናዝሬት የወባ መከላከያ እና ስልጠና ማእከል» በሚል የተመሰረተው ማእከል በአዳማ ከተማ በ«አርመር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት» እየተመራ በጠንካራ የወባ እና ሌሎች የቆላ በሽታዎች ምርምር ማዕከልነት እንዲያገለግል በጤና ሚኒስቴር ርክክብ ተደርጓል። 

Anopheles Mücke
ምስል dpa/picture alliance

የወባ ወረርሽኝ በ1958 ዓ.ም. 3 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ለህመም በመዳረግ የ150 ሺዎቹን ህይወት ቀጥፎ ነበር፡፡ ይህንኑን ተከትሎም በወቅቱ ወባን ለመከላከል የሚረዳ ማዕከል ለመጀመሪያ ጊዜ መመስረቱን የሚገልጹት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደሬጀ ዱጉማ ናቸው፡፡ በዚህ ማዕከል የላቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው በሚልም ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የተገነባው ህንጻ ዛሬ ተመርቋል፡፡ የአርመር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት የወባ እና ተጓዳኝ በሽታዎች ምርምር ይከናወንበታል የተባለውን ይህን ባለ 7 ወለል ሀንጻ ለመምራት ከጤና ሚኒስቴር ተረክቧልም፡፡
የስጋ ደዌ በሽታን መከላከል መሰረት አድርጎ ከ52 ዓመታት በፊት የተቋቋመው አርመር ሀነሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) ቲቢ እና ወባን ጨምሮ በርካታ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ እንደሚሰራም ተነግሯል፡፡  

በ2030 ወባን ጨርሶ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ያግዛት ከተባሉት ፕሮጀክቶች ዛሬ ይፋ የሆነው በአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት በኩል የተደረገው የ9.5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ዳይረክተር ሚስተር ሲያን ጆንስ ፕሮጀክቱን ዛሬ በአዳማ የወባ ምርምር ማዕከል ተገኝተው ይፋ ሲያደርጉ ይህን ብለዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት እና ህዝብን ወክለን እዚህ በመገኘት ወባን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ያግዛል ያልነውን ፕሮጀክት ይፋ ስናደርግ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ አሁናዊው የ10 ሚሊየን ዶላር ገደማ ድጋፍ ለኣመታት ስራውን ለመደገፍ ሲደረግ የነበረው የሰፊ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ከ2007 ወዲህ ብቻ ስንመለከት የአሜሪካ መንግስት እና ህዝብ ከ480 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ወባን ለማጥፋት የተከናወነ ነው፡፡ በዚህም ከኢትዮጵያ ወገኖቻችን ጋር ሆነን 90 በመቶ ሞት በማስቀረት ሰፊ ስኬት አስመዝግበናል፡፡ በቀጣይ አመታት ወባን ዜሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ ይህ ድጋፍ በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት እንዲሁም አጋሮቻችን ጋር በዚህ ረገድ የምንሰራው ስራ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

Äthiopien Adama | USAID Programm gegen Malaria
ምስል Seyoum Getu/DW

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በእቅዱ መሰረት በ2030 ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ዛሬ በአዳማ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የተመረቀው ማዕከል ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል ነው ያሉት፡፡  እንደ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ማብራሪያ ዛሬ በአሜሪካ መንግስት የተደረገው የ9.5 ሚሊየን ዶላር ቅኝት ለወባ ማስወገድ የተሰኘው ፕሮጀክት በ8 ክልሎች 54 ወረዳዎችን ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ይህም ወባን ለማጥፋት ትኩረት ውስጥ ከገቡ ከ560 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ሚካተትና የላቀ ተስፋ የተጣለበት ተብሏልም፡፡ የአሜሪካ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር የላቀ ገነዘብ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዮጵ አጋርነቱን አሳይቷልም ተብሏል፡፡ 
ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ