1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወርርሽኙ በተማሪዎችና በመማር ማስተማሩ ያሳደረው ተጽዕኖ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 30 2012

በጥቂት ወራቶች ውስጥ ዓለምን ያዳረሰው የኮቪድ 19 ተህዋሲ አብዛኛውን ነዋሪ ዛሬም ድረስ ከቤት እንዲውል አድርጎታል፡፡ ወረርሽኙ ከባለፈው የመጋቢት ወር መግቢያ አንስቶ መከሰቱ በተረጋገጠባት ኢትዮጲያም ሠራተኞችን ከቤት አውሏል ፣ የትምህርት ተቋማትንም እንዳዘጋ ይገኛል፡፡

https://p.dw.com/p/3bxHZ
Das Südäthiopische Bildungsbüro
ምስል DW/S. Wegayehu

የኮሮና ወርርሽኝ በተማሪዎችና በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

በኢትዮጵያ የ Covid 19 ተህዋሲ መገኘቱ ይፋ ከሆነ ወዲህ የማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎችን እያስተጓጎለ  ይገኛል ። በዛሬው የወጣቶች ዝግጅታችን ወርርሽኙ በተማሪዎችና በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ተጽኖ ያስቃኘናል ። ዝግጅቱን አሰናድቶ የሚያቀርብልን የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ነው አብረን እንከታተል ።

በጥቂት ወራቶች ውስጥ ዓለምን ያዳረሰው የኮቪድ 19 ተህዋሲ አብዛኛውን ነዋሪ ዛሬም ድረስ ከቤት እንዲውል አድርጎታል፡፡ ወረርሽኙ ከባለፈው የመጋቢት ወር መግቢያ አንስቶ መከሰቱ በተረጋገጠባት ኢትዮጲያም ሠራተኞችን ከቤት አውሏል ፣ የትምህርት ተቋማትንም እንዳዘጋ ይገኛል፡፡

በተለይ የአገሪቱ መንግሥት በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩ ተማሪዎችን ከበሽታው ለመጠበቅ በቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ የሚያስችለውን ሥራ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

በእርግጥ ከትምህርታቸው ተለይተው የሚገኙ ተማሪዎች ውሳኔው ለጤና ሲባል የተደረገ በመሆኑ ተገቢ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁንእንጂ ለአብዛኞቹ ተማሪዎች በኮረና ጦስ ከቤት የመዋሉ ጉዳይ ፈተና የሆነባቸው ይመስላል፡፡ ያነጋገርኳቸው ተማሪዎች እራስን ለመጠበቅ በቤት ውስጥ ማሳለፉ ተመራጭ ቢሆንም የመሰላቸት ሥሜት እንደፈጠረባቸው ወይም በእነሱ አገላለጽ እንደደበራቸው ይናገራሉ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በደቡብ ክልል ብቻ ከ6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በኮረና ሳቢያ ከትምህርታቸው ተለይተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ በወረርሽኙ ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችን ለመድረስ ያስችለኛል ያለውን ኘሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ደረሰ ጋቲሶ በክልሉ ከ7ተኛ እስከ12ተኛ ክፍል  ለሚገኙ ተማሪዎች ቢሮው በራዲዮ አማካኝነት ለማጠናከሪያ የሚያግዙ ትምህርታዊ ሥርጭቶችን እያቀረበ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

Der stellvertretende Büroleiter Derese Gatiso im Südäthiopischen Bildungsbüro
ምስል DW/S. Wegayehu

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሚሠራጨው የራዲዮ ትምህርታዊ ዝግጅት ብዙዎች ተማሪዎች ቤት በመቀመጣቸው ምክንያት ከትምህርት እንዳይርቁ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ተማሪዎች በትምህርታዊ የራዲዮ ዝግጅቱ ዙሪያ ያላቸው አተያይ የዛኑ ያህል ለየቅል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የራዲዮ ሥርጭቱን እንደምትከታተል የምትናገረው ነሂማ ዝግጅቱ ጥሩ ነው የሚል እምነት እንዳላት ብትገልጽም ቸርነት ግን እንደመደበኛ የክፍል ውስጥ ገለጻ ብዙም ግልጽ ሆኖ እንዳላገኘው ይናገራል፡፡

በክልሉ እየቀረበ የሚገኘው ትምህርታዊ የራዲዮ ዝግጅት ተማሪዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተጀመረ ሥለመሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊው አቶ ደረሰ ያስረዳሉ፡፡ ዝግጅቱ ተማሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቤት በመዋላቸው ያጡትን ለማካካስ እንጂ ተቋርጦ የሚገኘውን መደበኛ ትምህርት ለመተካት ያለመ አለመሆኑንም ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ የራዲዮ ዝግጅቱ ተማሪዎች ከመቆዘም እንዲወጡና ዝግጅቶቹን  በማድመጥ ከወላጆቻቸው ጋር እንዲወያዩባቸው እድል የሚፈጥር ነው ይላሉ፡፡

በእርግጥ የራዲዮ ትምህርት ዝግጅት በወረርሽኙ ሳቢያ በመደበኛ ትምህርት ላይ ያገጠመውን መስተጓጎል ለማካካስ ይረዳል የሚለው የቡዙዎች እምነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያለው የራዲዮ የሥርጭት ሽፋን በሁሉም ሥፍራ ተደራሽ አለመሆን በተማሪዎች መካከል የዕውቀት ልዩነት እንዲኖር ሊያደረግ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደረሰ ግን ቢሮው በራዲዮ ሥርጭት ሽፋን ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚረዳ አሠራር ማዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡