1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ወረርሽኝ

ሰኞ፣ መጋቢት 7 2012

የተከበራችሁ የማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን ተከታታዮቻችን የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝን የሚመለከቱ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ስርጭቱን ለመግታት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን በየጊዜው እና በፍጥነት የምናጋራችሁ ስለሚሆን ገፃችንን ቶሎ ቶሎ ጎብኙ።

https://p.dw.com/p/3ZWEZ
Symbolbild Corona-Virus
ምስል Reuters/D. Ruvic

•    በአማራ ክልል 925 የንግድ መደብሮች እና ሁለት የጤና ተቋማት መታሸጋቸውን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ አንደገለፁት 16 ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።

•    የኮረና ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል ያለመ የእጅ መታጠብ ዘመቻ በመቐለ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ ለዚህም በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በግዜያዊነት የእጅ መታጠብያ ስፍራዎች ተዘጋጅተው ይገኛሉ። የእጅ መታጠቢያ መሣርያው፣ ውሃና ሳሙና የቀረቡት በመንግስታዊ እና የግል ድርጅቶች ድጋፍ ተብሏል።

•    «አፍሪቃ ለክፉ ቀን መዘጋጀት አለባት» ሲሉ የዓለም የጤና ድርጅት ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የኮሮና ወረርሽን በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑን  አስጠነቀቁ። ዳሬክተሩ ዕሮብ ዕለት በሰጡት መግለጫ « አፍሪቃ ንቂ፣ አህጉሬ ንቂ» ሲሉ አፅዕኖት ሰጥተውም አሳስበዋል።  116 ታማሚዎች ላይ ተህዋሲውን ባረጋገጠችው ደቡብ አፍሪቃ ስድስት እድሜያቸው ከ 10 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ይገኙበታል። ከ 54ቱ የአፍሪቃ ሀገራት 30ዎቹ በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ያረጋገጡ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ጋምቢያ፣ ዛምቢያ እና ጅቡቲ እንዲሁ የመጀመሪያ ያሉትን ሰው አግኝተዋል።  በህጉሪቷ በጠቅላላው እስከ ዕሮብ አጋማሽ ድረስ 529 ሰዎች ላይ ተህዋሲው ተረጋግጧል።

•    ጀርመን ዕሮብ ዕለት ከ 10 000 በላይ ዜጎቿን ከግብፅ ፣ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ማስወጣቷን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀይኮ ማስ አረጋገጡ። አብዛኞቹ ጀርመናውያን በውጭ ሀገራት በጉብኝት ላይ የነበሩ እና መመለስ ያልቻሉ ነበሩ።  ሀገሪቱ በጠቅላላው 100 ሺ የሚሆኑ ዜጎቿን ወደ ሀገሯ እንዲመለሱ እንደምታግዝ አስታውቃለች። ጀርመን ውስጥ ከ 12,300 በላይ ሰዎች በትህዋሲው የተያዙ ሲሆን 28 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። 

• ደቡብ አፍሪቃ በተሐዋሲው መያዛቸው የተረጋገረጠ ሰዎች ቁጥር 116 ደርሰዋል። ስድስተኛው ሰው በተሐዋሲው መያዙ በተረጋገጠባት ኢትዮጵያም የተለያዩ ተቋማት የተሐዋሲውን ስርጭት ለመከላከል ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

• በተሐዋሲው ስርጭት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገችው አውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን እንዲህ ያለው አጋጣሚ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ አንደማይታወቅ በመጠቆም፣ ኅብረተሰቡ ከተባበረ ተግዳሮቱን መቋቋም እንደሚችል እምነታቸውን ገልፀዋል።

• ኮሮና ተሐዋሲ በቅድሚያ በተከሰተባት ቻይና ሕይወት ወደ ተለመደው ሂደት እየተመለሰ ነው። 80,894 ሰዎች በተሐዋሲው በተያዙባት ቻይና ከተጠቀሰው ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከህመሙ ማገገማቸው እየተነገረ ነው። 

• በኢትዮጵያ ከ ሶስት አመታት በፊት በተከናወነ ጥናት በትክክል እጅን የመታጠብ ልማድ ያለው ህዝብ ከ 25 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን በ UNICEF ኢትዮጵያ የጤና ልዩ ባለሙያ ዶክተር ደረጀ ሙሉነህ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። በሌላ በኩል የእጅን ንጽህና ለመጠበቅ መንግስት ሰፊ የውሃ አቅርቦት እንዲያደርግ የሚጠይቁ ኢትዮጵያኖች ቁጥር ጨምሯል።

• ቻይናዊው ባለሃብት ጃክ ማ የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪካ ሃገራት በፍጥነት መዛመቱን ተከትሎ አንድ ሚሊዮን የተዋህሲው መመርመሪያ ቁሳቁሶች ለጠቅላላው የአፍሪቃ ሀገራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታወቁ። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት ቀናት በፊት የአሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ ማ ለእያንዳንዱ የአፍሪቃ ሀገር ከ 10 ሺ እስከ 20 ሺ የሚደርሱ የኮሮና መመርመሪያ ኪቶችን እንደሚለግሱ አስታውቀው ነበር። 

•  የጀርመን አየር መንገድ ሉፍታንዛ ከነገ ዕሮብ አንስቶ እስከ ሚያዚያ አራት( ኦፕሪል 12)  ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ሙሉ በሙሉ ሰርዟል። የኢትዮጲያ አየር መንገድ ግን ለጊዜው በየእለቱ ወደ ፍራንክፈርት የሚያደርገውን ጉዞ እንደማያቋርጥ አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ለዜጎቹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

•  የአለም ጤና ድርጅት WHO በአዲሱ የኮሮና ተህዋሲ መያዛቸውን የሚጠረጥሩ ሰዎች ሀኪም ሳያማክሩ ኢቦፕሮፊን የተባለውን መድኃኒት እንዳይወስዱ አስጠነቀቀ።  
https://coronavirus.jhu.edu/map.html