1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶክተር ኪሩቤል ተስፋዬ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 23 2012

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ኪሩቤል ተስፋዬ የተባለ ኢትዮጵያዊ ሀኪም ነው። በአሁኑ ሰዓት ለቀጣይ ትምህርት በሄደበት ስጳኝ ሀገር እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በወጣ አዋጅ የተነሳ ቤቱ ውስጥ ይገኛል። ወጣቱ ሀኪም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ስለ ተህዋሲው «ጠቃሚ»የሚላቸውን መረጃዎች በፁሁፍ እና በቪዲዮ ያጋራል።

https://p.dw.com/p/3bcNX
Äthiopien | Dr. Kirubel Tesfaye arbeitet als Dozent an der Jimma Universität
ምስል Privat

ዶክተር ኪሩቤል ተስፋዬ

የ 27 ዓመቱ ወጣት ዶክተር ኪሩቤል ተስፋዬ ባለፈው ዓመት ነው ከጅማ ዩንቨርስቲ በህክምና የተመረቀው። በዚሁ ዮንቨርስቲ ለሰባት ወር ያህል ካገለገለ በኋላ በአሁኑ ሰዓት ለቀጣይ ትምህርት በሄደባት ስፔን ሀገር ይገኛል። እዛም የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በወጣ አዋጅ ምክንያት ትምህርቱ ስለተስተጓጎለና አብዛኛ ጊዜዉን ማለት ይቻላል እቤት ውስጥ ስለሚያሳልፍ ከተህዋሲው ጋር የተገናኙ መረጃዎችን እያሰባሰበ እና እየገመገመ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን በፁሁፍ እና በቪዲዮ በማጋራት ላይ ይገኛል። ኪሩቤል ለመጀመሪያ ጊዜ ቻይና ውስጥ የተከሰተዉ የኮሮና ተህዋሲ ወደ ስጳኝ እንደተዛመተም  በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት እና ቸልተኝነት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ይናገራል። እሱም «ይህ አመለካከት ስጳኝን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት እና ሁሉም ነገር እንደተዘጋጋ አይቻለሁ» ይላል። ስጳኝ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ በርካታ ሰዎች በትህዋሲው መያዛቸው የተረጋገጠባት ሀገር ናት። « ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ ዛሬ 48ኛ ቀኑ ነው። ይህን ያህል ጊዜ ተዘግቶም የተያዡ ቁጥር እየቀነሰ አይደለም።» ይላል ማድሪድ ከተማ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ።

Spanien Leganes | Coronavirus | Patient Notaufnahme
ስጳኝ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ በርካታ ሰዎች በትህዋሲው መያዛቸው የተረጋገጠባት ሀገር ናት። ምስል Reuters/S. Vera

ወጣቱ ሀኪም ስለተህዋሲው በተለይ ደግሞ የስጳኝ እና የኢትዮጵያ ተሞክሮዎቹን ለሌሎች ማካፈል ከጀመረ አንድ ወር አለፈው። የሚፅህፋቸውንም መረጃዎች ኢትዮጵያ የሚገኙ የ FM ሬዲዮ ጣሚያዎች፣ አንዳንድ ድረ ገፆች እና ግለሰቦች በማህበራዊ መገናኛ ገፆቻቸው ላይ ለሌሎች አካፍለዋል። እስካሁን ስለተህዋሲው መዛመቻ መንገዶች እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለሚሰጡ የተሳሳቱ አመከካከቶች ግንዛቤ የሚያስጨብጠው ኪሩቤል በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጲያ ውስጥ መጠናት ይገባቸዋል የሚላቸው ነገሮች አሉ። ኪሩቤል ኢትዮጵያ ውስጥ የተያዡ ቁጥር በንፅፅር አናሳ የሆነው ከሚወሰደው የጥንቃቄ ርምጃ አንፃር ሳይሆን በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ይችላል የሚል ዕምነት አለው። ይህን ጉዳይም የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት እንዲያጣሩ ይመክራል።
እንደ «ሀኪም» የተባለ የፌስ ቡክ ገፅ እና "ኢትዮጵያን ፊሲዢያን አሶሲዬሽን" የተባለ የቴሌግራም ግሩፕ ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች ጋር እንደሚወያይ የገለፀልን ኪሩቤል እዛ ላይ አዳዲስ መረጃዎችንም እንለዋወጣለን ይላል። 

Äthiopien Corona-Pandemie Dire Dawa Transport
ምስል DW/M. Teklu

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ አንስቶ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ዋጋ በአለማችን ላይ እጅጉን ጨምሯል።ጀርመን ዉስጥ ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው እንደ የትራንስፖርት እና የገበያ ስፍራዎች ጭንብል ማድረግ ከዚህ ሳምንት አንስቶ  ግዴታ ሆኗል። ይህ ምንም እንኳን እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ግዴታ ባይሆንም ኪሩቤል ታናሽ እህቱን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶችንም ጭምብል እንዲያደርጉ ይመክራል። እስካሁን ባለው ጥናት ወጣቶች በኮሮና ተህዋሲ ቢያዙ እንኳን በሽታውን የመቋቋም እድላቸው ሰፊ ቢሆንም ለሌሎች ሰዎች ሲሉ ጥንቃቄ መውሰዱን እንዳይዘናጉ ነው ወጣቱ ዶክተር የሚመክረው። «በማንበብ ላይ እንጂ በስሜት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማንም አይበጅም» የሚለው ኪሩቤል፣ ወጣቱ ከማድረግ መቆጠብ አለበት የሚለው ነገር አለ። ይህም ሺሻ ቤት መሄድን ነው። « ኮሮናን ለመከላከል እቤትህ ተቀመጥ ተብሎ ሺሻ ቤት ሲሄድ ምን ይባላል? ይሔን በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ነው የምለው» ይላል በአሁኑ ሰዓት ከኮሮና ተህዋሲ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በፁሁፍ እና በቪዲዮ እያዘጋጀ የሚያቀርበው ወጣት የህክምና ባለሙያ ዶክተር ኪሩቤል ተስፋዬ። 

ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ