1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሮና ተሐዋሲ፣ የኦሮሚያ ክልል ጥቃትና የአባይ ግድብ

ዓርብ፣ ነሐሴ 1 2012

ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ታማሚዎች ቁጥር መጨመሩ፣ በኦሮሚያ ክልል ጥቃት የተፈጸመባቸው ወገኖችን ብሶት የሚያሳዩ መረጃዎች መውጣት እንዲሁም የአባይ ግድብ የእኔ ነው የሚለው ዘመቻና ግድቡን የሚመለከተው ድርድር መቅረጥን አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አካቷል።

https://p.dw.com/p/3gdSJ
Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

«የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት 01.12.2012»

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ መጨመሩ እየታየ ነው። በአንጻሩ ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ያገገሙ ሰዎችም እንዲሁ በርካቶች ናቸው። በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከት ያሳሰባቸው ወገኖች ዛሬም ማሳሰቢያ አዘል መልእክታቸውን በማሕበራዊ መገናኛው እያስተላለፉ ነው። ከእነዚህ መካከል በፌስቡክ ናቶሊ ናቶሊ ናቶሊ የተባሉ። «እንዴት አይበዛም በሰለፍ እያሳለፍን ነው፤ በችግኝ ተከላ እያሳለፍን ነው፣ ያለጥንቃቄ ገና ይጨምራል!!!» ሲሉ፤ ደምሰው በላይ በበኩላቸው፤ «የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሾፌር እና ረዳት ላይ ትልቅ ሥራ ሊሰራ ይገባል ማስክ አይጠቀሙም፤ የሚጠቀሙት ትራፊክና የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ሲያዩ ብቻ ነው።  እንዲሁም በሆስፒታል ካርድ ክፍል አካባቢ ፣ ላብራቶሪ አካባቢ፣ ራጅና አልትራሳውንድ አካባቢ ተራ አስከባሪ ቢመደብላቸው የተሻለ ነው።» በማለት ጥቆማና ምክር ለግሰዋል። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በተለይ በበዓል ሰሞን በነበሩ መዘናጋቶች እና ጥንቃቄ በጎደላቸው ህዝባዊ ሰልፎች የኮሮና ተሐዋሲ መስፋፋቱን የሚያመለክቱ ዘገባዎችን ካስነበቡ በኋላ፤ ሚፍታህ ሻሚል፤ «ከሀጫሉ ሞት በኋላ በተፈጠረው ግርግር ብትሉ ምን አለ!! እሱ አይብስም ለኮሮና መስፋፋት ለምን በበዓል እናሳብባለን?» በማለት ሲጠይቁ፤ አዲስ ቦና ደግሞ፤ «የሰው ልጆች ብንተባበር መፍትሄው እኛው እጅ ላይ ነውና ያለው እውቀታችንን አዋጥተንና አስተሳስረን ለዚህ ወረርሺኝ ፈውስ መድኃኒትና ክትባት ለማግኘት እንጣር። የተቀረነውም በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክሮች እየተገበርን በትዕግስትና በጥንቃቄ ኑሯችንን እንግፋ።» በማለት መክረዋል። አብርሃም አብርሽ፤ «ሁሉም እገዳ እንደገና ወደ ነበረበት ይመለስ ቅድሚያ ለጤና» ነው የሚሉት።  ሃቢባ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም « እኛ ከኮረና በላይ ዘረኝነትና ሃይማኖትን ወክሎ የመጣው ወረርሽኝ ነው የሚያሰጋን ኮሮና በዓለም የመጣ ነው ዘረኝነት ግን በጣም ፀያፍ ነው» ሲሉ ፍሬው ገሜ በቄ ደግሞ በእንግሊዝኛ ፤ «እና በሳኒታይዘርና በሳሙና ለሚሞት ተሐዋሲ መድኃኒት የለም?» በማለት የገረማቸውን ጥያቄ ጽፈዋል። 

Symbolbild | Forschung | Impfstoff | Covid-19
ምስል picture-alliance/ANE

ከሰኔ 23 ማለዳ ጀምሮ ለሳምንታት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦባት በሰነበችው ኢትዮጵያ በተለይ የሞባይል ዳታ ሥራ ከጀመረ ወዲህ በየማኅበራዊ መገናኛው የሚለጠፉ በኦሮሚያ ክልል የደረሱ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮና ፎቶዎች የብዙዎችን ስሜት መንካታቸውን የሚታዩት አስተያየቶች ያመለክታሉ። በግፍና ሰቅጣጭ መንገድ የተገደሉ ንጹሐን፣ በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ተገድለውም ለመቅበር አዳጋች ችግር የገጠማቸው የጥቃቱን ሰለባዎች እማኝነት ያደመጡ ወገኖች ከጻፏቸው  አስተያየቶች መካከል፤ አምባሳደር ሀሰን ታጁ በትዊተር፤ «በዚህ ቤተሰብና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ሰሞኑን የተፈጸሙ ግፎች ለጆሮ እንኳ የሚሰቀጥጡ እጅግ ሲበዛ አሰቃቂ ናቸው። አላህ ለተጎዱት ጽናቱን ይስጣቸው። ሀገራችንንም ከክፉ ነገሮች ሁሉ ይጠብቅልን።»ሲሉ ፍሬሕይወት መለሰ በፌስቡክ፤ «ይህ ግፍ የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። እግዚያብሄር ይፈርዳል።» ረቡኒ ረቡኒ የሚል የፌስቤክ ስም ያላቸው ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፤ «መቼም መንግሥት ተብዬው ይህንን ነገር ሳያይ ቀርቶ አይደለም ዕድሜው እንደገፋ ሽማግሌ ወሬና ተረት ይናገር እንጂ ፤ እንዴት ነው ከሀገሩ ሰው የሚሰደደው?» በማለት ጠይቀዋል። ሰፋ ያለ አስተያየት ያስነበቡት ደግሞ ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ የተባሉት ወደ አምስት ሺህ  ጓደኛ ያላቸው የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው፤ ሙክታሮቪች «እርቅ ከንሰሃ ይነሳል። ንሰሃ እውነትን ከማመን።» በማለት ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት ቀጠሉ፤ «ከሁለት አመት በፊት በህወሓት ጄነራሎችና ባለስልጣናት፣ በሶማሌ ክልል የወቅቱ ባለስልጣናት ሄጎ ተብለው በተደራጁ ወጣቶች በሶማሌ ክልል በዋነኝነት አማራውን፣ ክርስቲያኑን የጂጂጋ ከተማ ማዕከል ያደረገ እጅግ አሳማሚና ሰቅጣጭ ወንጀል ተፈፅሞ ነበረ። ይህ ተግባር ኢንተርኔት ዝግ ስለነበረ ብዙዎች ያላወቁትን እውነት እዚህ ፌስቡክ ላይ እውነቱን ያጋራሁት እንደምታስታውሱት እኔ ነበርኩ። የተደረገው ነገር የሚያሳፍር በመሆኑ በጣም አፍሬ ነበረ። ከተጎጂዎች ጎን በመቆም ተግባሩን አምርሬ አውግዤያለሁ። ሙስጠፌ ወደ አመራር ሲመጣ ተጎጂዎችን ሰብስቦ በማናገር በድርጊቱ አዝኖ፣ ሌላ ጊዜ እንደማይደገም ቃል በመግባት በተፈጠረው ነገር እጅግ ማዘኑን ገልፆ፣ በተቻለ አቅም ካሳ እንደሚከፍል ቃል ገባ። በቂም ባይሆን ካሳ ከፈለ። ቤተክርስቲያን አደሰ። የእርቅና መግባባት ኮሚቴ መስርቶ ማኅበረሰቡ ይቅር ለፈጣሪ እንዲባባል አደረገ። ከዚያ በኋላ አልተደገመም። በኦሮሚያ ይህ አይነት መንገድ ያስፈልጋል። ምንም ማለባበስ አያስፈልግም።» ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ይቋቋማል መባሉን ተከትሎ ቬሮኒካ ኑረዲን ደግሞ፤ «ከዚህ በፊት እንዲሁ በቡራዩ በተከሰተው እልቂት ግዜ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ እንዲደርስላቸው ተብሎ ተዋጥቷ እቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፤ አጥጋቢ ባይሆንም። አሁንም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን መርዳቱ እደተጠበቀ ሆኖ ተመሳሳይ ችግሮች እዳይከሰቱ መሥራት ይገባናል። ምክንያቱም ዝም ብሎ ውኃ ቅዳ ፥ ውኃ መልስ አይነት ነገር የሀገራችንን እድገት ወደ ኋላ የሚመል ስለሆነ ማለት ነው።» የሚል አስተያየት በፌስቡክ አጋርተዋል። አዎል አሎ ደግሞ በትዊተር፤ «ይህንን ሰቅጣጭ ድርጊት ሁላችንም በተቻለ መጠን አጠንክረን ማውገዝ አለብን። የዚህ ጨካኝና አስከፊ ወንጀል ፈጻሚዎች በጠንካራ የሕግ ችሎት መዳኘት አለባቸው። በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ካልሆነ በቀር በማንም ላይ ለሚፈጸም ጥቃት የሚደረግ ማብራሪያ ወይም ማስተባበያ የለም።» በማለት በእንግሊዝኛ አስተያየታቸውን አስነብበዋል።

Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል AFP/Maxar Tech

ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ እሁድ ዕለት የአባይ ግድብን አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛውም ሆነ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የድጋፍ መልእክቶች ተላልፈዋል። በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ግድቡን በሚመለከት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ድርድራቸውን መጀመራቸው ከተሰማ በኋላ ዳግሞ መቋረጡ ተነግሯል። ግድቡም ሆነ አባይ የእኔ ነው የሚለው እንቅስቃሴ ሳይገታ ይህ ዜና እንደተሰማ ቶሎሳ በጂጋ በፌስቡክ፤ « እንደውም መደራደርም አይገባንም፤ በገዛ ቤታችን፤ በገዛ ንብረታችን ድርድር? የተፈጥሮ ሀብት የጋራ ከሆነ ለወደብ ኪራይ መክፈል የለብንም። ነዳጅ በነፃ ከሱዳንም ይሁን ከሚቀርበን በነፃ መውሰድ አለብን ማለት ነው።» ይላሉ፤ ጌታቸው ደሜም ከእሳቸው የሚዛመድ አስተያየት ነው ያላቸው፤ «ቆይ እነዚህ ሰዎች ነዳጅ በነፃ የሚሰጡን አስመሰሉ እኮ፤  አባይ ከየት እንደሚነሳ ዛነጉት መሰለኝ።  ከፈለጋችሁ ተስማሙ፤ የሚያገባን ነገር የለም ። እኛ ግን ሥራችንን አናቆምም።» ዳኛቸው ገናናው በበኩላቸው፤ «ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ እስካሁን ብቻዋን ለተጠቀመችው ቅድሚያ ካሳ ሳትከፍለን መደራደር አያስፈልግም። የግብፅ ቀረርቶ ምንም አያመጣም። ምክንያቱም አባይ የኛ የራሳችን ነው።» ባይ ናቸው። ዩሲፍ አሊ ደግሞ በትዊተር፤ «ድምጻችንን እናሰማ፤ እኔ እያሰማሁ ነው። ድምጻችን ለግድባችን፤ ሁሉም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሁሉም።» ብለዋል። ሰሎሞን ካሣም በትዊተር ፤ «ደግሜ እላለሁ፤ የግድቡ ተዓምር ከሚሰጠን ኃይል በላይ ነው፤ ሀገራችንን አንድ የሚያደርግ ጉልበት አለው። ኢትዮጵያ! ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ግድቡ የእኔ ነው፣ አባይ፤ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ አባይ» ሲሉም በሃሽ ታግ አጅበው ሃሳባቸውን አጋርተዋል። ዳኒ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ አባይን አስመልክቶ ቴዎድሮስ ካሣሁን ቴዲ አፍሮ በዚሁ ሳምንት በዩትዩብ ያሰራጨውን ነጠላ ዜማ ጠቅሰው « አባይ የግሌን ባልኩኝ የጋራ ካቃራት ምስር ግፍም ሳትፈራ፤ ምስር አረቢኛ ሲሆን ሀገር ማለት ነው፤ በዚያም ላይ ጥንታዊ የግብፅ መጠሪያ ነው፣ ካሉ በኋላ «ቅኔ ትጠላለህ? » ሲሉ ጠይቀዋል። ድንቁ ደግሞ እንዲህ አሉ፤ «አባይ መመኪያችን ነው፤ ኢትዮጵያ የግብጾችና ሱዳኖች ዳቦ ናት። እነሱ ግን ካዷት ሆኖም አሁንም ሆነ ለመጪዎቹ ምዕተ ዓመታት ያለማቋረጥ ትመግባቸዋለች።» እኛም የዕለቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በዚሁ አበቃን። ጤና ይስጥልን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ