1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ክብካቤ የምትሻው መሬት

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2018

የዓለም የመሬት ቀን ባለፈው ሳምንት ሲታሰብ ምድር የሰዎች ብቸኛ ቤት መሆኗን ያመለከተው የተመድ የትም ብንኖር እያንዳንዳችን ይህችን የጋራ ቤታችንን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበትን የሚያሳስብ መልእክት አስተላለፏል።

https://p.dw.com/p/5Cxqu
የዓለም የመሬት ቀን
የዓለም የመሬት ቀን በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ ቀመር ሚያዚያ 22 ቀን ላይ ይታሰባል (ፎቶ ከማኅደር)ምስል፦ Viktor Gladkov/Zoonar/picture alliance

ክብካቤ የምትሻው መሬት

 

በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ሚያዝያ 22 ቀን የዓለም የመሬት ቀን ይታሰባል። የሰው ልጅ መሬትን እያለማትና እየተከባከባት በምትሰጠው በረከት እንዲኖርባት መፈጠሩን መዛግብት ይጠቁማሉ። በተቃራኒው በተገኘባት መሬት ላይ የሚፈጽማቸው ጥንቃቄ የጎደላቸው እንቅስቃሴዎቹና የኑሮ ዘይቤው በሂደት ምድሪቱን ለብክለትና ጉዳት አጋልጧል። 

የምድር ማለትም የመሬት ቀንን መዘከር የሚለው ሀሳብ የተጠነሰሰው በጎርጎሪዮሳዊው 1970 ዓ.ም. በ ዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር ጌይሎርድ ኔልሰን እና በወጣቱ ተሟጋች ዴኒስ ሄይስ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ያኔ አሜሪካን ውስጥ ብቻ 20 ሚሊየን የሀገሪቱን ዜጎች ጎዳናዎች ላይ በማውጣት የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ንቅናቄን የጠነሰሰው እሳቤ ዛሬ በመላው ዓለም በ193 ሃገራት የአንድ ቢሊየን ሰዎችን ድጋፍ አግኝቶ በየዓመቱ እንዲታሰብ ምክንያት ሆኗል። ዛሬ የያኔው ወጣት ዴኒስ ሄይስ earthday.org የተሰኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ያገለግላሉ።

በ1960ዎቹ የወጣ በራቼል ካርሰን የተጻፈው «ሳይለንት ስፕሪንግ» የተሰኘ መጽሐፍ ዲዲቲ የሚባለው ተባይ ማጥፊያ ስላስከተለው ጠንቅ መረጃ አወጣ። መጽሐፉ ይህ ኬሚካል በምግብ ሰንሰልት ላይ ያስከተለውን ጉዳትና አሉታዊ ተጽዕኖ ዘርዝሮ ይፋ በማድረግ ለሰዎች ተፈጥሮ ጥንቃቄና ሚዛናዊ አጠቃቀምን እንደምትሻ በማመላከት እስከዛሬ ይጠቀሳል። መጽሐፉም በከፍተኛ ደረጃ የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ ተነባቢነትን አገኘ።

መጽሐፉ ለንባብ ከበቃ ከዓመታት በኋላ የአሜሪካዋ ዊስኮንሰን ግዛት ሴናተር ጌይሎርድ ኔልሰን በደቡብ ካሊፎርኒያ የባሕር ወደብ ላይ የፈሰሰው በሚሊየን ጋሎን የሚገመት ነዳጅ ዘይት በተፈጥሮ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ተገንዝበው በኋላ ኅብረተሰቡም ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖረው ጥረት አድርገዋል። ተባባሪያቸው ከነበረው የአካባቢ ተፈጥሮ ደኅንነት ተቆርቋሪ ዴኒስ ሄይስ ጋ በመሆንም ትምህርት ቤት በሚዘጋባቸው ወቅቶች ኅብረተሰቡ ውስጥ እየገቡ ቀሰቀሱ አነቁ። ጥረታቸውም የመንግሥት ባለሥልጣናትን አሳምኖ የንጹሕ አየር እና የንጹሕ ውኃን የሚመለከቱ ደንቦች አሜሪካ እንዲደነገጉ ምክንያት ሆኑ። 

የዓለም የመሬት ቀን
የዓለም የመሬት ቀን የምድራችንን የተፈጥሮ ሀብት አፈር እና ውኃው ያጋጠመው ብክለት እንዲጸዳ ማሳሰቢያ ይተላለፍበታል።(ፎቶ ከማኅደር) ምስል፦ Getty Images/J. Aznar

የዓለም የመሬት ቀን

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዓለም አቀፍ የመሬት ቀንን ስናስብ የምንኖርባት ምድር ጥንቃቄና ክብካቤ የሚያስፈልጋት ቤታችን መሆኗን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የተመድዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽ አስገንዝበዋል።

"የመሬት ቀን የዓለማችንን ደካማነት ያስታውሰናል። እያንዳንዱ ማመላከቻ ቀይ እያበራ ነው፤ የአየር ንብረት ቀውስ፤ የብዝኀሕይወት ውድመት፤ የ1,5 ዲግሪ የሙቀት መጠን ገደብ ሁሉ ገና እውን አልሆነም። ነገር ግን ምን መደረግ እንዳለበት እናውቃለን፤ ከቅሪተ አካል ለሚገኝ ነዳጅ ዘይት ያለንን ሱስ እናስወግድ። ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚደረገውን የለውጥ እንቅስቃሴ እናፋችን። ተፈጥሮን እንጠብቅ እንዲሁም እናድስ። የአየር ንብረት ፍትኅን በለውጡ ለተቸገሩ ተጋላጭ ለሆኑት እንስጥ።  ለሰዎች፤ ለመሬት እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ስንል አሁኑኑ እርምጃ እንውሰድ። » ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የታሰበው የዓለም የመሬት ቀን «የእኛ ኃይል፤ የእኛ ዓለም» የሚል መሪ ቃል ይዟል። ዓላማው ኀብረተሰብን በማነቃነቅ የመሬትን ተፈጥሮ እያበላሸ የመጣውን ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ብሎም ለመቀልበስ ትርጉም ያለው የጋራ ጥረት እንዲያደርግ መቀስቀስ ነው።

የመሬት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታሰብ ምን አብሮ መታሰብ አለበት? ያልናቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ሳይንስ ፕሬፌሰር የሆኑት ሸለመ በየነ መሬትና አፈር በጣም የተያያዙ በመሆናቸው ከምግብ ዋስትና ጋር በጣምራ መታየት እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት።

ከመሬት ጋር በተገናኘ የሰዎች የየዕለት እንቅስቃሴ ጥንቃቄ የታከለበት ካልሆነ የመሬትን ለምነት ሊያሳጣና ምርትና ምርታማነት ሊቀንስ እንደሚችል ያሳሰቡት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ትምህርት ክፍል ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት ዶክተር ማርቆስ ማቴዎስ ተባባሪ ፕሮፈሰር ናቸው። ባለሙያው የአፈርን ለምነትን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ነው ይላሉ።

ረቡዕ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የእናት ምድር ቀን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የጋራ የወደፊት ሕይወታችንን ለመጠበቅ የበለጠ ትልቅ የአየር ንብረት እርምጃ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ዕለቱ ባለፈው ሳምንት ሲዘከርም በመላው ዓለም ሚሊየኖች ቢያንስ ለአፍታ ቆም ብለው ስለምድራችን ደኅንነት ይዞታ ማሰባቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። 

አፈር ሕይወታችን ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ሸለመ ኅብረተሰቡ ይህ ግንዛቤ እንዲኖረው ከልጅነት ጀምሮ በትምህርት መልክ ሊሰጥ እንደሚገባና ዕለቱም በየዓመቱ ሊታሰብ ይገባል ባይ ናቸው። ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ማርቆስ በበኩላቸው አርሶ አደሩ የኅብረተሰብ ክፍል አፈር ለምነቱን እንዳያጣ ቢያደርግ ያሉትን ሃሳብ አጋርተዋል።

የግለሰቦች ተሳትፎ

እያንዳንዱ ግለሰብ በየአካባቢው ለውጥንለመፍጠር አቅም እንዳለው ይታመናል። በዚህ ረገድ ማኅበረሰቡ በሚያበረክታቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦዎች ማለትም አካባቢን በማጽዳት፤ ዛፎችን በመትከል፤ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ከሁሉም ይጠበቃል። ግለሰቦች እርምጃዎችን ሲወስዱ ማኅበረሰብ ይከተላል፤ ኅብረተሰቡ በጋራ ድምፁን ሲያሰማ ደግሞ የሚመለከታቸው መሪዎች እንደሚያደምጡ ይታመናል።

የአፈር ጉዳይ ተመራማሪ ባለሙያዎቹ ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ