1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካፋ ክልል የመሆን ጥያቄ

ዓርብ፣ ኅዳር 26 2012

በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች መስተዳድር  የሚገኘው የካፋ ዞን ቀደም ሲል አቅርቦ የነበረው ክልል የመሆን ጥያቄ መልስ እንዲሰጥበት ዛሬ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች እና በሁለት ከተሞች ሲካሄድ በዋለው ህዝባዊ ስብሰባ መጠየቁን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3ULWH
Karte Sodo Ethiopia ENG

     
ዞኑ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር የሚያስተባብረው ኮሚቴ ለዶቼቬለ በሰጠው ቃለ ምልልስ ክልሉን የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን ያደርጋል ያለውን ጥረት እንዲያቆም ጠይቋል።ዛሬ በቦንጋ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ደግሞ ከክልል እንሁን ጥያቄ ባሻገር በወታደራዊ ዕዝ መመራታቻን ያብቃልን ሲሉ ጠይቀዋል።

የካፋ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለደቡብ ክልል የቀረበበትን አንድ ዓመት ምክንያት በማድረግ የዞኑን መቀመጫ ቦንጋን ጨምሮ በዞኑ በሚገኙ 12ቱ ወረዳዎች ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ዳግም መጠየቁን የዞኑ አስተዳደር ገልጿል። የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ቀርቦ የነበረውን እና ዛሬ በካፋ ዞን ሁሉም ወረዳዎች በህዝባዊ ስብሰባ የቀረበውን  ይኽንኑ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ለሚጠይቀው ጥያቄ መንግስት ሂደቱን የጠበቀ መልስ እንዲሰጥ እንሰራለንም ብለዋል  አቶ በላይ ።

«የደቡብ ክልል ምክር ቤት የካፋን ክልል የመሆን ጥያቄ ተቀብሎ የማጽደቅ ሂደቱን ጠብቆ ለህዝበ ውሳኔ ያቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ እና ያ ሳይሆን በመቅረቱ» ህዝቡ በድጋሚ እንዲጠይቅ እንዳስገደደው የተናገሩት ደግሞ የካፋ ክልል የመሆን አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሀኑ ኃይሌ ናቸው። የፌዴራሉንም ሆነ የክልሉን ህገ መንግስት መሰረት ያደረገው ክልል የመሆን ጥያቄ ለክልሉ መንግስት ከቀረበ ዛሬ ህዳር 26 /2012 ድፍን  አንድ አመት እንደሆነው እና ይህንኑ አስመልክቶ ህዝቡ በድጋሚ ድምጹን እንዲያሰማ መገደዱን አቶ ብርሀኑ ገልጸዋል። በቅርቡ የደህዴን ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ወደ ዞኑ መጥተው የካፋ ህዝብ ያቀረበው ጥያቄ ወደፊት በጥናት ላይ ተመስርቶ መልስ እንደሚያገኝ እና  እስከዚያው በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ በሌላ መንገድ እንዳይንቀሳቀስ ጫና አሳድረውብን ነው የተመለሱት ሲሉ አስተባባሪው አቶ ብርሃኑ ቅሬታቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
ዛሬ በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ በዋለው «ክልል የመሆን ጥያቄአችን ይሰማ» ህዝባዊ ስብሰባ ላይ፣ ክልሉን የሚያስተዳድረው ደኢህዴን ፣እያደረገ ነው ያሉትን የህገ መንግስት ጥሰት እና አፈና ሊያቆም እንደሚገባ መጠየቃቸውን የካፋ ወጣቶች ተወካይ ወጣት አሳየ አለማየሁ ተናግሯል። የካፋ የክልልነት ጥያቄው መነሻው «የመልካም አስተዳደር ችግር » ተብሎ የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን የሚደረገው ጥረትም መቆም እንዳለበት ጠይቀናል ሲል አሳየ አስረድቷል።
የካፋ ዞን ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በወታደራዊ ዕዝ ስር መሆኑ እና ለወታደራዊው ዕዝ የሚመደበው በጀት ለልማት እንዲውል በዛሬው ህዝባዊ ስብሰባ ጥያቄ መቅረቡን ወጣት አሳየ ይናገራ። 
በደቡብ ክልል በህዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑን ያረጋገጠው የሲዳማ ዞን እንዳደረገው ሁሉ የካፋ ዞንን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ ዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄዎቻቸውን በየዞን ምክርቤቶቻቸው አጸድቀው ውሳኔ እንዲሰጥበት ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አቅርበው በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ