1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካንኩ ሙሳ፦ የማዕድን ጌታ

Mahamadou Kane
ሐሙስ፣ መስከረም 7 2013

ካንኩ ሙሳ 10 ኛው የማሊ ሥርወ መንግሥት ንጉስ ነበሩ። በስልጣን ዘመናቸው ማንሳ ሙሳ ፤ “የዋንጋራ የማዕድን ጌታ” ተብለውም ይጠሩ ነበር። በወቅቱ የወርቅ እና የጨው ማዕድን ንግድን በማሊ በማሳደግ ብቻ ሳይሆን በግዙፍ ሀብታቸው ከግዛታቸው ውጪም ይታወቁ ነበር።

https://p.dw.com/p/3iXlw
African Roots | Kanku Musa

አንድ ሰው ስለ ካንኩ ሙሳ ሊያውቅ የሚገባው የመጀመሪያ ነገር ምንድን ነው?
ካንኩ ሙሳ እ.ጎ.አ. በ 1280 ዓ.ም አካባቢ በማንዴን ተወለዱ። ምንም እንኳን ብዙውን ጊዜ ስማቸው ካንካን ሙሳ የነበረ ቢሆንም ፣ “ካንካን”የሚለው ቃል መሠረቱ “ካንኩ” ነበር።  ይህ ከእናታቸው ያገኙት የሴት ስም ነው። በዚያን ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ትላልቅ ብሔሮች የእናት የዘር ሀረጋቸው ተከታይ ስለነበሩ ወንዶችም በእናታቸው ስም ይጠሩ ነበር። ታላቅ ወንድማቸው ዳግማዊ  አቡበክር ከሞቱ በኋላ 1313 ገደማ ካንኩ ሙሳ የማሊ ሥርወ መንግሥት መሪ ሆኑ። ለአስርተ ዓመታት በዘለቀው ረጅም የስልጣን ጊዜያቸውም የእስልምና ባህልን በማሊ እና አካባቢዋ አስፋፍተዋል። ግዛታቸውም በወቅቱ ከዓለም እጅግ ሀብታም አገራት አንዱ ነበር። 

African Roots | Kanku Musa

ካንኩ ሙሳ ለምን እንዲህ ዝነኛ ሆኑ?
ካንኩ ሙሳ ማሊን ለብዙ መቶ ዘመናት ያስተዳደረው የኬይታ ንጉሳዊ ቤተሰብ ተወላጅ ናቸው። በስልጣን ዘመናቸው ጠንካራና ውብ ግዛት የገነቡ እጅግ ሀብታም ንጉስም ነበሩ። በአፈ ታሪክ መሠረት አያታቸው ቀዳማዊ አቡበክር የማሊ ሥርወ መንግሥት መስራች የነበሩት የሱንጃታ ኬይታ ታናሽ ወንድም ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የካንኩ ሙሳ ዘመን የማሊ ሥርወ መንግሥት ወርቃማው ጊዜ ነበር ተብሎ ይጠራል።

ካንኩ ሙሳ፦ የማዕድን ጌታ

የካንኩ ሙሳ መንግሥት ለማሊ ህዝብ  የነበረው ምኞት ምን ነበር?
ማንሳ (“ንጉስ”) ሙሳ ፤“የጋናታ ድል አድራጊ” ወይም “የዋንጋራ ማዕድን ጌታ” ተብለው ይጠሩ የነበሩት ካንኩ ሙሳ የተፈጥሮ ሀብቶች ፍለጋ እጅግ ከፍተኛ በነበረበት ዘመን ገዝተዋል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሀብታሞች መካከል አንዱ ተደርገውም ይቆጠራሉ። አንዳንድ ምንጮች እንደሚናገሩት ሀብታቸው 400 ቢሊዮን ዶላር ይገመት ነበር ። በካንኩ ሙሳ የግዛት ዘመን የባህር ማዶ ንግድ ሊስፋፋ ችሏል። የወርቅ እና የጨው ማዕድን የሥርወ መንግሥቱ ዋና የሀብት ምንጮች ነበሩ። 

ካንኩ ሙሳ ሀብታቸውን እንዴት ያሳዩ ነበር?

በ 1324 ካንኩ ሙሳ ወደ መካ ተጓዙ። አብረዋቸውም 60 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ 12 ሺ የሚሆኑት አገልጋዮች እና አሽከሮቻቸው ናቸው። ወርቃማ ዱላ የያዙ እና ሐር ጨርቅ የለበሱት አገልጋዮች ፈረሶችን ይንከባከባሉ፣ ሻንጣዎችን ይጠብቃሉ። ይህ ረዥም ጉዞ በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ እና በመካከለኛው ምስራቅ ታዋቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ካንኩ ሙሳ በጣም ለጋሽ ስለነበሩ በጎበኙባቸው ከተሞች ሁሉ የተወሰነ ሀብታቸውን ለግሰዋል።  ይህ ደግሞ ለክልሉ ኢኮኖሚ እና ለዝናቸው ከፍተኛ አስተዋፅዎ ነበረው።

ሰዎች ስለ ካንኩ ሙሳ ድንቅ ስራዎች ምን ያስታውሳሉ?

ከ 1325 አንስተው ካንኩ ሙሳ ከፍተኛ ሀብታቸውን ተጠቅመው በርካታ ሐይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ ሕንፃዎች አስገንብተዋል። ከእነዚህም መካከል ቲምቡክቱ እና ጋኦ ውስጥ የሚገኙ መስጂዶች ፣ የእስልምና ሐይማኖት ትምህርት ቤቶች እና የንጉሳዊ ቤተ- መንግሥቶች ይገኙበታል። በቲምቡክቱ የሚገኘው የሳንኮሬ መስጊድ ድንቅ ስራቸው ሆኖ ቆይቷል። በማሊ እና በአረብ አገራት መካከል ፍሬያማ ባህላዊ ልውውጥ እንዲፈጠር አስችሏል። አንዳንድ የማሊ ተማሪዎች በግብፅ እና በሞሮኮ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ የሄዱ ሲሆን ሌሎች የግብፅ እና የሞሮኮ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ሳንኮሬ ዩንቨርስቲ እንዲሁ ሥልጠና ለመውሰድ ሄደዋል። በዚያን ጊዜ ስፍራው ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ለእስላማዊ ባህል የእውቀት ማዕከል ነበር።  

ካንኩ ሙሳ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።