1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኮሮና ተሐዋሲ በቀላሉ እንላቀቅ ይሆን?

ማክሰኞ፣ የካቲት 8 2014

ኮሮና ተሐዋሲ በዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ 19 ተብሎ በመላው ዓለም ወረርሽኝ መሆኑ ከተነገረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ነው። ስርጭቱ አሁንም ባለመገታቱ ብዙዎች ቢሰላቹም አስፈላጊውን ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታዎች በተለይ በስፋት በተዛመተባቸው ሃገራት አልቀነሰም። በዚህ ምክንያትም ይኽ ተሐዋሲ በቀላሉ የምንገላገለው አይደለም በሚለው ብዙዎች ይስማማሉ።

https://p.dw.com/p/4743K
Symbolbild Coronavirus Pandemie Illustration
ምስል Zoonar/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የነበረው ተመርምረው በኮቪድ 19 መያዛቸው የተረጋገጠ ወገኖች ቁጥር ከሰሞኑ ዝቅ ማለቱ ይታያል። ይኽ ምን ማለት ይሆን?  የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ ስልቱ እና አቅርቦቱ ውሱን በሆነባት ኢትዮጵያ የ24 ሰዓቱ በጤና ሚኒስቴር ይፋ የሚሆነው ቁጥር መቀነስ አዘናጊ ምልክት እንዳይሆን የሚያሳስቡ ጥቂት አይደሉም።

ክትባት በብዛት በተዳረሰባቸው ሃገራት በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙት ቁጥር እጅግ ከፍ በማለቱ በየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ለምሳሌ ጀርመን ምንም እንኳን ከ70 በመቶ በላይ ነዋሪዎቿ ክትባቱን ቢወስዱም ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በመቶ ሺህዎች በተሐዋሲው መያዛቸው በየቀኑ ይፋ እየሆነ ነው። እንደኢትዮጵያ ያሉ ከመቶ ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የሀገሪቱ ዜጋ በበቂ ሁኔታ የሚዳረስ የህክምና አቅርቦት እና አገልግሎት በሌለበት በየ24 ሰዓታት ይፋ የሚሆነው በተሐዋሲው መያዛቸው የተረጋገጠ ወገኖች ቁጥር ጥቂት ዕድሉን ያገኙን እንጂ ብዙሃኑን አያመለክትም እና ሊያዘናጋን አይገባም የሚሉ ጥቂት አይደሉም። በተከታታይ የወጡትን ቁጥሮች መሠረት በማድረግ ያነጋገርናቸው የውስጥ ደዌ የሳንባ እና ጽኑ ህክምና ባለሙያ ዶክተር አስቻለው ወርቁ ስለቁጥሩ መቀነስ ከመናገር አስቀድሞ የወረርሽኙን አካሄድ ማስተዋል ያስፈልጋል ይላሉ። ዶክተር አስቻለው የኅብረተሰቡን ጥንቃቄ እና መዘናጋትን ተከትሎ የሚኖረውን የወረርሽኙን ማዕበላዊ አካሄድ በሁለተኛው እና ሦስተኛው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት መስፋፋት ወቅት በከፍተኛ ህመም ምክንያት ሀኪም ቤት ይገቡ የነበረ ታማሚዎች ቁጥርን በማሳያነት በማቅረብ ያጠናክራሉ።

Symbolbild | Impfstoff Corona Omikron Variante
ምስል Fleig/Eibner-Pressefoto/picture alliance

እናም ይላሉ ዶክተር አስቻለው፤ የተሐዋሲው ስርጭት ካልተገታ፤ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እስካሌሉ፤ ከምንም በላይ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም የወረርሽኙ ስጋት ዝቅ ብሏል ብለው ቀጣይ ሊደረግ የሚገባውን ርምጃ የተመለከተ ውሳኔ ካልሰጡ ከፍ እና ዝቅ የሚለውን ቁጥር ተመልክቶ መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉ አሳስበዋል።

ከአፍሪቃ ሃገራት እና ከሌሎች የኤኮኖሚ አቅም ከሌላቸው ሃገራት ጋር ሲነጻጸር በጀርመን እና በሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከሁለት አልፎ ለሦስተኛ ጊዜ የኮቪድ 19 ክትባት አግኝቷል። ሆኖም የተሐዋሲው ስርጭት ተባብሶ መቀጠሉ ይታያል። በተሀዋሲው የተያዙት እንደሚገልጹት የህመም ስሜቱ ለአንዳንዱ ቀለል ለአንዳንዱ ደግሞ ማጠናከሪያ የተባለው ሦስተኛውን ክትባት ሁሉ ወስደው ከባድ ህመም የሚያጋጥምበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ጀርመን በየዕለቱ በተከታታይ በመቶ ሺህዎች መያዛቸው እየተነገረ ነው። ክትባቱ እየተዳረሰ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ የተሀዋሲው መዛመት እንዴት ነው በሚል የሚጠይቁ ጥቂት አይደሉም። ዶክተር አስቻለው ክትባቱ ተሐዋሲው እንዳይዘን ሳይሆን ቢይዘን ከፍተኛ ጉዳይ እንዳያስከትል የሚረዳ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

እናም ቀደም ሲል በጤና ችግር ምክንያት የነበረው ቅድሚያ የመስጠቱ ሂደት ቀርቶ አሁን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከ11 ዓመት ጀምሮ ክትባቱ እንደሚሰጥ በመግለጽ ሰዎች እንዲከተቡም መክረዋል። የአቅርቦቱን በተመለከተም ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ክትባት እንዳለ፤ በአሁኑ ጊዜም 20 ሚሊየን ሕዝብ ለመከተብ ዘመቻ መጀመሩንም አመልክተዋል። 

Coronavirus Spritze mit Corona-Impfstoff
ምስል Weber/Eibner-Pressefoto/picture alliance

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ከተነጋገረባቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ የኮሮና ተሐዋሲ ክትባትን አፍሪቃ ውስጥ ለማምረት አቅምን መገንባትን ይመለከታል። በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪቃ ቀዳሚ ስትሆን ሌሎች ሃገራትም ገብተውበታል። ኢትዮጵያም ዝግጅት ላይ በመሆኗ የክትባት አቅርቦት ችግር እንደማይኖር ነው ዶክተር አስቻለው አጽንኦት የሰጡት። እስካሁን በመላው ዓለም 10 ቢሊየን የኮሮና ክትባት መመረቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ክትባቱን በተወሰኑ ጊዜያቶች ልዩነት መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ እየታየ ነው። 

እንዲያም ሆኖ ምርምሩ ቀጥሎ መፍትሄ ሊገኝለት ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው። ዋናው ምክራቸውም ሰዎች አሁን ያለውን ዕድል ተጠቅመው ክትባቱን መውሰድ እና ራሳቸውን በተሐዋሲው ሲያዙ ከሚከተለው የከፋ ህመም እና ጉዳት ከመከላከል አይዘናጉ የሚል ነው። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፤ ሰዎች በሚበረክቱበት ስፍራ ርቀትን መጠበቅ እና ብዙ አለመቆየት፤ እጅንም በጥንቃቄ ማጽዳቱ የዘወትር ተግባር መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ለሰጡን ማብራሪያ የውስጥ ደዌ የሳንባ እና ጽኑ ህክምና ባለሙያ ዶክተር አስቻለው ወርቁን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ