1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ወደ ጫካ የሸሹ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ አልደረሳቸውም» 

ሐሙስ፣ መስከረም 27 2014

በቅርቡ በሴዳል እና ኦዳ ብልድግሉ ወረዳዎች በተስፋፋው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ13ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ዳላቲ በተባለ የአሶሳ ዞን አንድ ቀበሌ እንደሚገኙ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ጫካ የሸሹ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/41OZ8
Äthiopien | IDP’s aus Sedal, Benshangulu-Gumuz
ምስል Negassa Desalegn/DW

ከካማሺ ዞን የተፈናቀሉ ሰዎች አቤቱታ

የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በቅርቡ ከካማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ እና ኦዳ ብልዲግሎ  ወረዳ የተፈናቀሉ ከ13ሺ በላይ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የኮሚሽኑ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ለዶቸቨለ እንደተናገሩት በጸጥታ ችግር ምክንያት ከሚዘገዩት በስተቀር ለሁሉም ተፈናቃዩች እርዳታዎች  በጊዜው እየተሰጠ  ይገኛል፡፡ ከምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምበል ከተባለ ወረዳም ተፈናቃዩች ወደ ክልሉ እየመጡ እንደሆነም ገልጸው የተፈናቃዩች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ መሆኑንም አስረድተዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ490ሺ በላይ መድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡ በክልሉ ካማሺ ዞን ሴዳል ወረዳ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም በተከሰተው የታጣቂዎች ጥቃትም በርካቶች ተፈናቅለው በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ ተጠልለው እንዳሉም የኮሚሽኑ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ለዲ ደቢሊው ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሴዳል እና ኦዳ ብልድግሉ በተባሉ ወረዳዎች በተስፋፋው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ13ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ዳላቲ በተባለ የአሶሳ ዞን አነድ ቀበሌ ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አመልክተዋል፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎችም ሰብአዊ እርዳታ በመስጠት ላይ እንደሆኑ  አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል፡፡
በካማሺ ዞን ያሶ በተባለ ወረዳም ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ስፍራ የሸሹ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደተናገሩት ባለፉት ሰባት ወራት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጫካ የሸሹ ሲሆን ሰብአዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸውም ጠቁመዋል፡፡ በወረዳቸው በርካታ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ ከዚህ ቀደም በታጣዊዎች ጉዳት መድረሱንም አብራርተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ኮሚሽነር ኢንስፕክተር ምስጋናው እንጅፋታ የነዋሪዎች ቅሬታ ትክክል መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን በካማሺ ዞን ያሶ ወረዳ እና በዞኑ ስር በሚገኙ  የተለያዩ ወረዳዎች ፀረ ሰላም ባሏቸው ሀይሎች ጥቃት ሲፈጽሙባቸው እንደነበረና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጸጥታ ሀይል ወደ ስፍራው መሰማራቱንም አመልክቷል፡፤ 
የኢትጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት አርብ መስከረም 21/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው በካማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ  ከመስከረም 14 ጀምሮ ታጣቂዎች በወረዳው የሚኖሩ ህጻናትና ሴቶችና   ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆችን  ማገታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም በወረዳው በነበረው የታጣቂዎች ጥቃት ደግሞ 5ሺ የሚደርሱ ዜጎች ወደ አሶሳ ዞን መሸሻቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
 

Äthiopien | IDP’s aus Sedal, Benshangulu-Gumuz
ምስል Negassa Desalegn/DW