1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከእስር የተፈቱ የአፋር ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች  

ሐሙስ፣ ሐምሌ 19 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከአፋር ህ/ሰብ ክፍሎች ጋር ለመወያየት ባለፈው ሰኔ 21፣ 2010ዓም ወደ ሰመራ በሄዱበት ጊዜ ታስረው የነበሩ ወጣቶች ከትናንት በስቲያ ሀምሌ 16፣ 2010ዓም ተፈቱ። ጠ/ሚንስትሩ ወደሚወያዩበት አዳራሽ  ለመግባት በመጠየቃቸው ለአንድ ወር እስርና ለድብደባ የተዳረጉት ወጣቶች በሁለት ዙር ነው የተፈቱት።

https://p.dw.com/p/324VZ
Karte Äthiopien Afar-Region

«በሰመራ አሁንም ሰፊ የልዩ ፖሊስ እንቅስቃሴ ይታያል።»

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከአንድ ወር በፊት ወደ አፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ በመሄድ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ባካሄዱበት ዕለት 49  የአፋር ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች መታሰራቸው ይታወሳል። የክልሉ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉት ወጣቶቹ  ምንም እንኳን በውይይቱ እንዲሳተፉ ባይጋበዙም፣ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ባላቸው ቁርጠኝነት የክልሉ መስተዳድር አልሰራቸውም ያሏቸውን ጉዳዮች ለጠቅላይ ሚንስትሩ ለማቅረብ ወደ ውይይቱ አዳራሽ ለመግባት ቢጠይቁም፣ ጥያቄአቸው አዎንታዊ መልስ በማግኘት ፈንታ ችግር ነበራ ያጋጠማቸው።  ወጣቶቹ አልተጋበዛችሁም በማለት በክልሉ ፖሊስ ተደብድበው እስከ አንድ ወር ገደማ በመታሰር፣ የጠቅላይ ሚንስትሩን ውይይት አውካችኋል በሚል   ክስ እንደተመሰረተባቸው ከታሳሪዎቹ አንዱ አቶ እስማኤል መሀመድ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት።
የክሱ ሂደት ሳያበቃ በፊት ግን 23ቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት አስገራሚ በሆነ ሁኔታ መፈታታቸውን ከታሳሪዎች ጋር በቅርብ የሚንቀሳቀሱት አቶ አብዱ መሀመድ ገልጸዋል። የክሳቸውን ሂደት በመከታተል ላይ የነበሩት ቀሪዎቹ 26  ታሳሪ ወጣቶች ደግሞ ከትናንት በስቲያ በሁለተኛ ዙር ተፈተዋል።  ዓቃቤ ሕግ የመሰረተባቸው ክስ እየታየ ሳለ ከትናንት በስቲያ ድንገት ከእስር ቤት ውጡ መባላቸውን ግን መጀመሪያ ላይ የዋስትና መብት እንኳን ተከልክለው የነበሩት ታሳሪዎች ወዲያው እንዳልተቀበሉት አቶ እስማኤል በማስታወቅ፣  የመፈታቱን ውሳኔ ያጣጣሉት  ጥፋተኛ መሆናቸውን እንዲያምኑ ያረፈባቸውን ግዴታ ለመቀበል ዝግጁ ባለመሆናቸው እንደነበር አስረድተዋል።
የክልልሉ ባለስልጣናት 26ን ታሳሪዎች ጥፋተኛ እንደሆኑ ለማሳመን ቢሞክሩም፣ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ አድርጎ በነጻ እንዳሰናበታቸው አቶ አብዱ መሐመድ አረጋግጠዋል ። የአፋር ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች በተፈቱበት ባሁኔ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይስፈን መብታችን ይጠበቅ የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያስተጋቡ በራሪ ጽሁፎችን ከበተኑ ወዲህ በክልሉ በተለይ በሰመራ ሰፊ የልዩ ፖሊስ እንቅስቃሴ እንደሚታይ አቶ እስኤማል እና አቶ አብዱ ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ